የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ 'አጋጥሞ የማያውቅ' የበይነ መረብ ጥቃት ማድረሱ ተነገረ

በስልክ ላይ የሚታይ የቻት ጂፒቲ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኦፕንኤአይ እጅግ ዘመናዊ የሆኑት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎቹ የደኅንነት ፍተሻ እየተደረገ በነበረበት ወቅት ከቁጥጥር ውጭ በመሆን እና አጋጥሞ የማያውቅ ባህሪ በማሳየት የበይነ መረብ ጥቃት መፈጸማቸውን ይፋ አደረገ።

የቻትጂፒቲ አምራች የሆነው ኩባንያ የሰው ልጅ መመሪያ ከሰጠው በኋላ ብቻውን ሊሠራ የሚችል የኤአይ ሥርዓት ቁጥጥር በሚደረግበት አካባቢ ፍተሻ እየተደረገለት ሳለ ድክመቶችን በማግኘቱ ከሙከራ ገደቦቹ ማምለጥ ችሏል።

ጥቃቱ የደረሰበት በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ የሰው ሠራሽ ሞዴሎች አምራች የሆነው ሀጊንግ ፌስ (Hugging Face) የኮምፒውተር ሥርዓቱ ውስጥ ዘልቀው መግባት ችለዋል።

ኦፕንአይ (OpenAI) ክስተቱ "ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ" እንደሆነ እና ከሀጊንግ ፌስ ጋር በመሆን ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ተናግሯል።

የኩባንያው ኃላፊ ክሌመንት ዴላንጌ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ይህ ሁሉ በራሱ መከሰቱ በጣም አስደንጋጭ ነው" ብለዋል።

"ምርመራ በመካሄድ ላይ ነው፤ እና ይህ በዓይነቱ የመጀመሪያ ከሆነ ክስተት ያገኘነውን ትምህርት እናካፍላችኋለን" ሲሉ ዴላንጌ አክለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት ቃል አቀባይ እንዳሉት የዩኬ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ደኅንነት ተቋም በክስተቱ ውስጥ የታየውን የኤአይ ሥርዓት ባህሪን እያጠና ሲሆን፣ ጥበቃዎችን ለማሻሻል ከኦፕንአይ እና ከሌሎች ላቦራቶሪዎች ጋር መሥራቱን ቀጥሏል።

ድርጅቶች በመንግሥት በሚደገፈው የሳይበር ኢሴንሻልስ ሰርተፊኬት መርሃ ግብር ውስጥ በመመዝገብ የሳይበር መከላከያዎቻቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ክስተት የተራቀቁ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች አቅም እና ቴክኖሎጂው የበለጠ እያደገ ሲሄድ አሁን ያሉት መከላከያዎች በቂ ናቸው ወይ የሚለውን በተመለከተ አዳዲስ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

የሶኒክዎል የበይነ መረብ ደኅንነት ተቋም ሥራ አስፈፃሚ ስፔንሰር ስታርኪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ ክስተት ተቋማት የራሳቸውን መከላከያ "ማጠናከር" እና "የሳይበርን ጥቃትን የመቋቋም አቅም እንደ ዋና ሥራ ቅድሚያ መስጠት" እንዳለባቸው ግልጽ አድርጓል።

"በጣም የሚያሳዝነው እውነታ ግን ብዙ ድርጅቶች አሁንም በሰው ኃይል ላይ ብቻ እየተማመኑ ሲሆን፣ ተገዳዳሪዎቻቸው ደግሞ ወደ ማሽን ፍጥነት እየተሸጋገሩ ነው" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሳይበር ደኅንነት አማካሪ ድርጅት ዋና የደኅንነት መሐንዲስ የሆኑት ትራቪስ ሌሌ፣ የማዘመኑ ሂደት "በሳይበር ደኅንነት ውስጥ አሳሳቢ ጊዜ" መሆኑን ተናግረዋል።

"ይህ በግልጽ የሚታይ አለመመጣጠንን ያጎላል" ብለዋል።

"የጥቃት ኃይሎች ያልተገደቡ ሲሆኑ፣ ምርጥ የመከላከያ መሣሪያዎች ደግሞ አውዱን መረዳት የማይችሉ የጥበቃ መከላከያዎች ናቸው።"

ነገር ግን በኢኤስኢቲ የዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ጄክ ሙር፣ ይህ ዜና የፉክክር ገጽታ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል።

ተቀናቃኙ አንትሮፒክ ለክላውድ ሚቶስ (Claude Mythos) ሞዴሉ እየጨመረ የመጣውን ትኩረት ስለሚስብ ኦፕንአይ የራሱን የኤአይ አቅሞች ለማጉላት እየፈለገ ሊሆን እንደሚችል ተከራክሯል።

"ይህም ኦፕንኤአይ በቅርብ ጊዜ የአንትሮፒክን የግብይት ፍላጎት እየተከታተለ ነው የሚለውን ጥያቄ ይጭራል" ብለዋል።

ይህ የሆነው የቻይናው የአይቲ ኩባንያ የሆነው ሙንሾት ኪሚ ኬ3 የተባለውን ግዙፍ አዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴል ይፋ ካደረገ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው፤ ይህም ከአሜሪካ ከፍተኛ ኩባንያዎች ጋር ሊወዳደር እንደሚችል ተናግሯል ።