
የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, በየመን የሚገኙት የሁቲ ታጣቂዎች ለባብል መንደብ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉአሜሪካ ለ12 ተከታታይ ሌሊቶች ኢራን ላይ ድብደባ ስትፈጽም የየመን ሁቲዎች ሁለት የሳዑዲ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማጥቃታቸውን
ተናገሩ።
የኢራን መገናኛ ብዙኃን ረቡዕ ዕለት አሜሪካ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ ፈንጂ በተቀበረበት የውሃ ክፍል ላይ የሚያልፍ ነዳጅ ጫኝ
መርከብ በእሳት መያያዙን ዘግበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ከቀጠለች
ድልድዮቿን ወይንም የኃይል ማመንጫዎቿን እንደሚያወድሙ ዝተው ሁቲዎች የቀይ ባሕርን የሚዘጉ ከሆነ ደግሞ “እርምጃ እንደሚወስዱ”
አስጠንቅቀዋል።
ሁቲዎች ያሉት እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ በኢራን የሚደገፈው ቡድኑ በሳዑዲ አረቢያ ላይ “የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ገደብ”
ከጣለ በኋላ የተፈጸመ የመጀመርያው ጥቃት ነው የሚሆነው።
በሁቲዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው መርከቦቹ ስም ኢንሴሊያ እና ላይላ እንደሚባል ቢጠቅሱም ላይላ ላይ የተፈጸመው ጥቃት አልተረጋገጠም።
የቡድኑ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ መርከቦቹ የተጣለባቸውን እገዳ በመጣሳቸው በድሮን እና በሚሳኤሎች ጥቃት መፈጸማቸውን
አስታውቀዋል።
የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ በበኩሉ ሐሙስ ዕለት ኢንሴሊያ የተባለችው መርከብ “በቀይ ባሕር ላይ እየቀዘፈች ሳለ” ጥቃት እንደተፈጸመባት
እና እሳት ተነስቶ እንደነበር ዘግቧል።
በአገሪቱ ትራንስፖርት ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጭ ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው
ማለታቸው ተጠቅሷል።
የመርከቧ ሁሉም ሠራተኞች ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ጨምሮ የዜና ኤጀንሲው በዘገባው ላይ አስታውቋል።
የዩኬ ባሕር ትራንስፖርት እና ንግድ ባለሥልጣን በበኩሉ የሳዑዲ ነዳጅ ጫኝ መርከብን “ምንነቱ ያልታወቀ ተወንጫፊ” እንደመታት
አስታውቋል።
ሰኞ ዕለት የሁቲ ታጣቂዎች “የባሕር ላይ ትራንስፖርት እገዳ” የጣሉ ሲሆን የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልናት ደግሞ በቀይ
ባሕር ደቡባዊ መግቢያ ላይ የሚገኘውን ባብ አል ማንዳብን ለሳዑዲ
መርከቦች ዝግ ሊያደርጉ መሆኑን ዘግበዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ ቀይ ባሕር ቁልፍ የነዳጅ
መተላለፊያ በመሆን እያገለገለ ነው።
የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር ላይ የሚደረገውን የመርከቦች እንቅስቃሴ ማወካቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ
ከፍተኛ ጭማሪ መታየት ጀምሯል።
ሰኞ ዕለት እገዳው ከተጣለ ጊዜ አንስቶ ዘጠኝ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ወደ የመን ሲቃረቡ ወደ መጡበት ለመመለስ ተገድደዋል።
ቃል አቀባዩ ሳሬ “በግምት አስር መርከቦች እንዲያፈገፍጉ እና እንዲመለሱ ማድረግ ችለናል” ሲሉ ተናግረዋል።