በዙሪያችን የሚፈጠሩ መጥፎ ሽታዎች የአካል እና የአእምሮ ጤናችንን እንዴት ይጎዳሉ?

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/ BBC/ Getty Images
መጥፎ ሽታ የመላው ሰውነትን እና የአንጎል ጤናን የሚያቃውስ ነው።
መንገድ ላይ የተጠራቀመ ቆሻሻ ወይም ከፋብሪካ የሚጣል ተረፈ ምርት የበርካቶችን የዕለት ከዕለት ሕይወት ያናጋል።
ቆሻሻ የሚያስከትለው የአየር ብክለት ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ብዙዎች ለዐይን፣ ለጆሮ፣ ለምላስ፣ እና ለመዳፍ የሚሰጡትን ትኩረት ለአፍንጫቸው አይሰጡም።
የአየር ብክለት ጤና ላይ የሚያሳድረውን ጉዳት ብዙዎች ትኩረት ይነፍጉታል። ጥናቶች እንደሚያሳዩትም አንዳንዶች ስልካቸውን ከማጣት የማሽተት ችሎታቸውን ማጣት ይመርጣሉ።
መጥፎ ሽታ የራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ለመተንፈስ መቸገር እና የእንቅልፍ መዛባት ያስከትላል።
አካላዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ ጫናም ያሳድራል። አፍንጫችን መጥፎ ሽታን እንደ ማስጠንቀቂያ ደውል ይወስደዋል።
እንዳንታመም ወይም ለኢንፌክሽን እንዳንጋለጥ የሚረዳ ማስጠንቀቂያ ነው።
ከመጥፎ ሽታ ጀርባ ባክቴሪያ ይኖራል። የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም እንዲነቃቃ መጥፎ ሽታ የራሱን ሚና ይጫወታል።
በስዊድን፣ ስቶኮልም የሽታ ሳይንስ ባለሙያ ዮሀን ሉንድስቶርም እንደሚሉት መጥፎ ሽታ አካባቢያችን ጤናማ አለመሆኑን መልዕክት ያስተላልፍልናል።
አንጎል ሽታ አፍንጫ ውስጥ ከገባ በኋላ በ300 ሚሊሰከንዶች ውስጥ እንደሚገነዘበው ባለሙያው ይናገራሉ።
በሠሩት ጥናት መሠረት መጥፎ ሽታ የገጠማቸው ሰዎች በፍጥነት ሰውነታቸው ላይ ምልክት አሳይተዋል።
ሽታው ከሚነሳበት አካባቢ መራቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
አፍንጫ መጥፎ ሽታን ለመራቅ ሲል አንዳንዴ ጥሩ የሆነ ጠረንንም የሚያውክ ብሎ ሊፈርጅ ይችላል።
"የማናውቀው ሽታ ሲገጥመን የመጀመሪያው ምላሽ መጥፎ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ነው" ይላሉ አጥኚው።
ሽታ ከመጥፎ ነገር ጋር ሲተሳሰር ሰውነት በፍጥነት ምላሽ ይሰጣል።
መጥፎ ሽታን ከኤሌክትሪክ ንዝረት ጋር በማስተሳሰር በሠሩት ጥናት መሠረት፤ ሰዎች በጣም በሩቅ ላለ መጥፎ ሽታ በፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጡ ተረድተዋል።
የተበላሸ እንቁላል የሃይድሮጅን ሰልፋይድ ሽታ ይሰጣል። በፍሳሽ መተላለፊያ ትቦ ውስጥ ያለው ሽታ ከአደገኛ ጋዝ ጋር የሚነጻጸር ሽታ አለው።
በተቃራኒው መልካም መዓዛ የሰዎችን ጤና የማደስ ሚና ይጫወታል። ጥሩ ነገር ሲሸተን አካላችን ብቻ ሳይሆን አንጎላችንም ይነቃቃል። መዓዛውን ከጥሩ ትውስታ ጋር ማስተሳሰርም የተለመደ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/ BBC/ Getty Images
መጥፎ ጠረን በሰውነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ላይ ሳይንቲስቶች ጥናት ማድረግ ቀጥለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2021 የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ራስ ምታት እና ማስመለስ በመጥፎ ሽታ ምክንያት ይከሰታሉ።
መጥፎ ሽታ አንጎልን ከአንጀት ጋር የሚያስተሳስረው ቫገስ ነርቭ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሰዎች መጥፎ ሽታ ሲገጥማቸው የሚያቅለሸልሻቸው ወይም የሚታመሙትም ለዚህ ነው።
መጥፎ ሽታ አንጎል ላይ የሚያሳድረውን ጫና በግልጽ ለመረዳት ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ።
መጥፎ ጠረን ጤና ላይ የሚያሳድረው ጫና ስለ ሽታው ከምንጨነቅበት መጠን ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው።
በፊላደልፊያ ሞኔል ኬሚካል ሴንስስ ሴንተር ውስጥ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ፓሜላ ዳልተን "አንድ ሰው ሽታውን የሚጠላበት ወይም የሚፈራበት መጠን ጠረኑ ከሚያሳድርበት ጫና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው" ይላሉ።
መጥፎ ሽታ ጤና ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለ32 ዓመታት ያጠኑት ባለሙያዋ እንደሚሉት፤ ጠረኑ ምን ያህል ያስጨንቀናል? የሚለው ተጽዕኖውን ይወስናል።
መጥፎ ጠረን አኗኗርን ለመለወጥ ምክንያት ይሆናል። ለውጡ ግን ውጤታማ የማይሆንበት ጊዜ አለ።
በአንድ ችግር ምክንያት ውጤታማ ያልሆነ የሕይወት ለውጥ ማድረግ ራሱን የቻለ ጉዳት ያስከትላል።
መጥፎ ሽታን በመፍራት መስኮት አለመክፈት፣ ከቤት ወጥቶ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ከሰዎች ጋር አለመገናኘት ተጠቃሽ ናቸው።
ፓሜላ እንደሚሉት መጥፎ ጠረን ማኅበራዊ መስተጋብርን ያውካል።
አንዳንድ ሰዎች በቀላሉ መጥፎ ጠረን ያውካቸዋል። ሌሎች ደግሞ በጉልህ የሚሰማ ካልሆነ በስተቀር እምብዛም ለውጥ አይታይባቸውም።
መጥፎ ጠረን ላይ ምርምር የሚያደርጉት ዳልተን እንደሚሉት ሽታ ሰዎች ላይ የሚያሳድረው ጫና በዕድሜ፣ በፆታ፣ በአኗኗር (ሲጋራ ማጨስን ጨምሮ) እንዲሁም አለርጂ ይወሰናል።
"አንዳንዶች አልፎ አልፎ ብቻ የሚሸታቸው እና ብዙም የማይረብሻቸው ነገር ይሆናል" ይላሉ።
ሰዎች መጥፎ ጠረንን በጊዜ ሒደት ይላመዳሉ የሚል ዕሳቤ ቢኖርም የተሳሳተ ነው።
ሰዎች ጥሩ ሽታ ወይም የማያውክ ጠረንን በፍጥነት ይላመዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, BBC/ Getty Images
በስቶኮልም የሽታ ሳይንስ ባለሙያ ዮሀን ሉንድስቶርም "የሆነ ጠረን ከሸተተን በኋላ የማይገድለን እንደሆነ ካወቅን በኋላ መልሰን ጠረኑን ላናስተውል እንችላለን" ይላሉ።
የሰው ልጆች አፍንጫ አንድ ትሪሊዮን ጠረኖችን ማሽተት ይችላል። ነገር ግን የማይጎዱ ሽታዎች ዝርዝርን ማንም አያውቅም።
በዕለት ከዕለት ሕይወታችን የተመለዱ የቡና ሽታን የመሰሉትን ሁሉም ሰው ላይለያቸው ይችላል። እንዲያውም ገሚሱ ሰዎች እነዚህን ሽታዎች አያስተውሉም።
በካናዳ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ብሪትሽ ኮሎምቢያ የአካባቢ ጥናት ባለሙያ አማንዳ ጊያንግ እንደሚሉት፤ አንዳንድ ጠረኖች መጣ ሄደት ስለሚሉ በተወሰኑ አካባቢዎች ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ትኩረት የሚሰጣቸው ይሆናል።
"በቅርቤ የሚገኝ ሕንጻ አካባቢ ያለውን ሽታ ላላውቀው እችላለሁ" ሲሉ ያብራራሉ።
መጥፎ ሽታ ሲኖር ግን ሁሉም ሰው አንድ ላይ ይሰማዋል።
በታዳጊ አገራት ብዙዎች በቆሻሻ ሥፍራ በሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ እንደሚኖሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
በዓሣ ማቀነባበሪያ እና ፍሳሽ መተላለፊያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በሚያሰሟቸው ቅሬታዎች ለውጥ ያገኙባቸው አጋጣሚዎች አሉ።
መጥፎ ጠረን የሚያስከትለውን የአየር ብክለት ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ከአገር አገር ይለያያል።
መጥፎ ጠረን ባለባቸው አካባቢዎች ኑሮ ፈታኝ ነው። አፍንጫችንም ስለ ሽታው ለሰውነት እና አንጎል መልዕክት ያስተላልፋል።
የተሻለ የማሽተት ብቃት ያላቸው ሰዎች በምግብ እና በግብረ ሥጋ ግንኙነትን በተሻለ መጠን ደስተኛ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።
በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ በ70 ሰዎች የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ጥሩ የማሽተት አቅም ያላቸው ሰዎች የተሻለ የወሲብ ሕይወት አላቸው።
በዓለም ላይ አምስት በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የማሽተት አቅም ማጣት አለባቸው።
እነዚህ ሰዎች ምግብን የሚያጣጥሙት በውስን መጠን ስለሆነ የጤና እክል ይገጥማቸዋል።
"ማሽተት የማይችል ሰው የምግብ ፍላጎቱም ይዳከማል" ሲሉ የሽታ ሳይንስ ባለሙያ ዮሀን ይገልጹታል።
የማሽተት አቅም ውስንነት በ10 ዓመታት ውስጥ የመሞት ምጣኔን ወደ 46 በመቶ ከፍ ያደርጋል። ሳይንቲስቶች ከዚህ ጀርባ ያለውን ምክንያት ለማወቅ ጥናቶች እየሠሩ ነው።
የመተንፈሻ አካል እንዲሁም እንደ አልዛይመርስ እና ፓርኪንሰንስ ያሉ ሕመሞች ለብዙዎች ኅልፈት ምክንያት ናቸው።
ዳልተን በበኩላቸው "ሽታን ለዓመታት አጥንቻለሁ። መጥፎ ነገር ሲሸተኝ አፍንጫዬ እየሠራ መሆኑን ያረጋግጥልኛል" ይላሉ።















