ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሶማሊላንድ በጋዛ ለሚሰማራው ዓለም አቀፍ ኃይል ወታደሮች ለማዋጣት ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንቱ ተናገሩ
የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብድራህማን መሐመድ አብዱላሂ መንግሥታቸው ሁለት ሺህ ወታደሮችን በጋዛ ይሰማራል ለሚባለ ዓለም አቀፍ የመረጋጋት ኃይል ለማዋጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም ይህ የሚፈጸመው በይፋ ጥያቄ ከቀረበላቸው ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን አስተያየት የሰጡት በዋሽንግተን በተካሄደው "የመካከለኛው ምሥራቅ – አሜሪካ " ጉባኤ ላይ በተሳተፉበት ጊዜ ለእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ነው።
ፕሬዝዳንቱ ዘ ታይምስ ኦፍ ኢዝራኤል ሲናገሩ "ስለዚህ ጉዳይ አልተጠየቅንም፤ ነገር ግን ከተጠየቅን [ወታደሮችን] ማቅረብ እንችላለን" ብለዋል።
ለጄሩሳሌም ፖስት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይም ሶማሊላንድ እስከ 2,000 ወታደሮች ልታዋጣ እንደምትችል ገልጸው፣ ነገር ግን መንግሥታቸው ወታደሮችን ወደ ጋዛ ለመላክ እየጠየቀ እንዳልሆነ አብራርተዋል።
እስካሁን ድረስ አሜሪካም ሆነች እስራኤል ከሶማሊላንድ ወታደሮች እንዲላኩ በይፋ መጠየቃቸውን በተመለከተ የታወቀ ነገር የለም።
ሶማሊላንድ ሶማሊያ የግዛቷ አካል አድርጋ የምትመለከታት ቢሆንም ነጻ አገርነቷን አውጃ የአገርነት ዕውቅና ለማግኘት ጥረት እደያረገች ነው።
ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይም እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
ነገር ግን ይህ የእስራኤል እርምጃ ከሶማሊያ፣ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከተለያዩ አገራት ተቃውሞ ቢገጥመውም ከወራት በኋላ ሁለቱም ወገኖች በየአገራቱ ኤምባሲዎቸቻውን ከፍተዋል።
የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ንግግር 'ካህ' ከተባለው የሶማሊላንድ ተቃዋሚ ፓርቲ በኩል ከባድ ትችት ቀርቦበታል።
የፓርቲው ቃል አቀባይ ሶማሊላንድ በውስጧ የደኅንነት እና የፖለቲካ ችግሮች እሉባት ለምን ወታደሮችን ወደ ውጭ መላክ አስፈለገ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
የፕሬዝዳንቱ ወታደሮችን ወደ ጋዛ የመላክ ሐሳብ የተሰማው ሶማሊላንድ እና እስራኤል ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ባሉበት ወቅት ነው።
ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ ሶማሊላንድ በጋዛ በሚቋቋመው ኃይል ውስጥ ብትሳተፍ ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር በደኅንነት መስክ ያላትን ግንኙነት ሊያጠናክር ይችላል፤ ነገር ግን በአገር ውስጥ ፖለቲካዋ ተቃውሞ ሊያስከትል ይችላል።
የቢቢሲ ሶማሊኛ ቋንቋ ክፍል ሶማሊላንድ ወደ ጋዛ ለመላክ ስላሰበችው ወታደራዊ ኃይል እና ስለቀረበበት ትችት ከሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።
ከጋዛ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊትም እስራኤል ለሶማሊላንድን እውቅና ከሰጠች በኋላ፣ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከጋዛ የሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ወደ ሶማሊላንድ የማስፈር ዕቅዶች መኖራቸውን እና በሶማሊላንድ የእስራኤል ወታደራዊ ሰፈር ሊቋቋም ይችላል የሚሉ ክሶች ሲያሰሙ ነበር።
ነገር ግን የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ሁለቱንም ክሶች ውድቅ በማድረግ ከጋዛ የሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ለመቀበል እና የእስራኤልን ወታደራዊ ሰፈር ለማስተናገድ ስምምነት እንዳልደረሱ አስተባብለዋል።
የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብድራህማን መሐመድ አብዱላሂ የጠቀሱት በጋዛ ይሰማራል የተባለው "ዓለም አቀፍ አረጋጊ ኃይል" ከጋዛ ጦርነት ማብቃት በኋላ አሜሪካ ባቀረበችው ዕቅድ ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ የሚቋቋም ነው።
የዚህ ኃይል ኃላፊነት ሲቪል ሰዎች እና የሰብአዊ እርዳታ ሥራዎችን መጠበቅ፣ የጋዛን ድንበሮች ማስከበር፣ የፍልስጤም ፖሊስን ማሠልጠን እና ጋዛ ሰርጥን ከታጣቂ ኃይሎች ነጻ ማድረግ ይገኙበታል።
በጋዛ የተካሄደውን የእስራኤል የሁለት ዓመታት ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃትን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጋዛ ባዘጋጁት ዕቅድ መሠረት ከተለያዩ አገራት በተወጣጡ ወታደሮች የሚቋቋም ኃይል ይሰማራሉ የተባለ ሲሆን፣ መልሶ ግንባታውም ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።