የሰው ሠራሽ አስተውሎት እድገት ፍጥነት በሰው ልጅ ላይ የፈጠረው ስጋት ቁጥጥር እንዲደረግበት ጥያቄ አስነሳ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የዓለማችን ሦስት ዋነኛ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተቋማት መሪዎች ኤአይ በሰው ልጅ ደኅንነት ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል በሚለው ስጋት ምክንያት ዘርፉ እየተጓዘ ያለበት ፍጥነት መቀነስ አለበት ሲሉ አሳሰቡ።

አንትሮፒከል የተባለው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሪዮ አሞዴይ የቴክኖሎጂው እድገት ፍጥነቱ እየጨመረ ከቀጠለ፣ ከቁጥጥር ውጭ የሚሆኑ የኤአይ ሞዴሎች በይነ መረቡን ሊቆጣጠሩ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሃብት እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለቤት ኢላን መስክ እና የኦፕንኤአይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳም አልትማም ሰው ሠራሽ አስተውሎት ደቅኖታል በተባለው የስጋት ግምገማ እንደሚስማሙ ተናግረዋል።

ከቀናት በፊት ከአንትሮፒክ ሥራውን የለቀቀው ተመራማሪ ጄኮብ ኮክሰን ለቢቢሲ በሰጠው ልዩ ቃለ ምልልስ፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ልማት ፍጥነት ካልቀነሰ "ሁላችንም በቅርብ ጊዜ ልንጠፋ እንችላለን" የሚል ስጋቱን ከገለጸ በኋላ ጉዳዩ ትኩረት አግኝቷል።

አሁን ደግሞ የቀድሞ አለቃው እና የአንትሮፒክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሪዮ አሞዴይ፣ ከኤአይ ጋር የተያያዙ አደጋዎች ከባድ በመሆናቸው እና ኩባንያዎችም ሆኑ መንግሥታት እነዚህን አደጋዎች ለመፍታት ጊዜ እንዲያገኙ፣ የኤአይ ሞዴሎች የልማት ፍጥነት "እንዲቆም ወይም እንዲዘገይ" ጥሪ አቅርበዋል።

በተለያዩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተቋማት ውስጥ የሠራው ተመራማሪ የ27 ዓመቱ ወጣት ጄኮብ ኮክሰን ለቢቢሲ እንደተናገረው የኤአይ የእድገት ፍጥነትን መግታት የአሜሪካ ጉዳይ ባቻ ሳይሆን ከቻይና ጋር በመቀናጀት ተግባራዊ መሆን አለበት ብሏል።

ጄኮብ ኤአይ እየተጓዘበት ባለው ፍጥነት ከቀጠለ በቀጣይ አሥር ዓመታት ውስጥ ሁሉንም የሰው ልጅ የማጥፋት አቅሙ ከ10 በመቶ በላይ ይሆናል በማለት ሥራውን መልቀቁን አሳውቋል።

ኮክስ ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ መጠይቅ፣ እሱ እና ሌሎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች በቴክኖሎጂው እየታየ ባለው ፈጣን ለውጥ ምክንያት "በእውነት ፈርተዋል፣ የሰው ዘር ዕጣ ፈንታ በእጅጉ አሳስቧቸዋል" ብሏል።

እነዚህ ባለሙያዎች "ወደፊት ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚመሩ እያቀዱ እና ሥራቸው በዓለም ላይ ሊያሳድረው ስለሚችለው ተጽእኖ እያሰቡ" መሆኑን ገልጿል።

ጨምሮም በኤአይ ፈጣን እድገት ምክንያት ሊፈጠር የሚችለው አለመረጋጋት በጣም ስለሚያስፈራቸው "ቴክኖሎጂውን በሚያበለጽጉበት ጊዜ ሁሉ፣ በየቀኑ ስጋታቸውን በአእምሯቸው ይዘው ነው የሚሠሩት" ብሏል።

በተመሳሳይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ተቋም የሆነው አንትሮፒክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳሪዮ አሞዴይም የቴክኖሎጂው ሞዴሎች ልማት ፍጥነት እንዲቀንስ እና በጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ጥሪ አቅርቧል።

አሞዴይ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው ጽሑፍ፣ ኤአይን ማሳደግ በራሱ ችግር እንዳልሆነ ጠቅሶ፣ ከቴክኖሎጂው ጋር የተያያዙ አደጋዎች ግን "ከባድ" መሆናቸውን አስጠንቅቋል። በመሆኑም ኩባንያዎች እና መንግሥታት እነዚህን ስጋቶች ለመቆጣጠር በቂ ጊዜ ሊያገኙ እንደሚገባ ገልጿል።

አሞዴይ ያቀረበው ባለ ሦስት ነጥብ ዕቅድ፣ በልማት ሂደታቸው ወቅት የአኤይ ሞዴሎች በገለልተኛ አካላት ቁጥጥር እንዲደረግባቸው፣ ለዘርፉ የጋራ ሕግ እና ደንብ እንዲወጣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋትን ያካትታል።

በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ታላቅ ዕመርታን እያስመዘገበ ያለው ኤአይ ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስጋት እየጨመረ ሲሆን፣ ከሁሉ የከፋው ግምት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ "ሁሉንም የሰው ልጆች ለማጥፋት ከ10 በመቶ በላይ ዕድል አለው" መባሉ ደግሞ ትኩረትን ስቧል።

ባለፉት ቀናትም አንትሮፒክ የኤአይ ሞዴሉን ለመጠቀም የባዮሎጂካል የጦር መሣሪያዎችን ለመሥራት የተደረጉ "አደገኛ እንቅስቃሴዎች" እና ሙከራዎችን ደርሶቸባው እንዳስቆመ አስታውቆ ነበር።

ከዚህም የበለጠ አሳሳቢው ማስጠንቀቂያ የተሰማው በቅርቡ ከአንትሮፒክ የደኅንነት ቡድን ሥራቸው የለቀቁ ሁለት ሠራተኞች፣ የኤአይ ኩባንያዎች ከሰው በላይ ብልህ ማሽኖችን ለመፍጠር በሚያደርጉት ፉክክር ውስጥ የሰው ዘር ሊጠፋ እንደሚችል የሰጡት ማስጠንቀቂያ ነው።

የአንትሮፒክ ሥራ አስፈጻሚ አሞዴይ በኤአይ ልማት ሂደት ውስጥ የሞዴሎችን ደኅንነት የሚገመግሙ ገለልተኛ ተቆጣጣሪዎች መኖራቸው እንደሚጠቅም ከገለጸ በኋላ ተፎካካሪ ኩባንያዎችም ጭምር ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው።

የኦፕንኤአይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳም አልትማን የቀረበውን ሐሳብ ደግፎ በኤአይ "ልማት ፍጥነት ላይ መጠንቀቅ እንዳለብን አምናለሁ" በማለት የገለልተኛ ተቆጣጣሪዎችን መኖር አስፈላጊነት ደግፏል።

ኢላን መስክ በበኩሉ በኤአይ ላይ ሊደረግ ስለሚገባው ቁጥጥር የቀረቡትን ሐሳቦች ደግፏል።

ነገር ግን ስጋቶች እና ማስጠንቀቂያዎች እየተሰሙ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስጋቶቹን ውድቅ በማድረግ "በኤአይ ውድድር ካላሸነፍን በጣም መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንገባለን" ሲሉ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የተራቀቁ የመረጃ መረብ ጠለፋ ችሎታዎችን የሚያሳዩ አዳዲስ ሞዴሎች ሲወጡ፣ የሳይበር ደኅንነት ስጋቶችም ተጨምረዋል።

አንትሮፒክ በቅርቡ እንዳስታወቀው እየዳበረው ያለ አንድ የኤአይ ሞዴል ከሙከራ ቦታው በራሱ ሊወጣ እንደሚችል ስለታወቀ ለሕዝብ እንዳይቀርብ አድርጎታል።

በተመሳሳይ ኦፕንኤአይ አስትራ የተባለው ሞዴሉን ይፋ ለማድረግ ሲዘጋጅም፣ በሳይበር ደኅንነት ስጋቶች ምክንያት ለጊዜው እንዲቆም መደረጉን ገልጿል።