የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ሳዑዲ ውስጥ 73 ሰዎች መጎዳታቸው ተገለጸ
በየመን የሚገኘው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ ጥምር ጦር፣ በኢራን የሚደገፈው የየመን ታጣቂ ቡድን ሁቲ ተዋጊዎች በሳዑዲ ላይ በፈጸሙት ጥቃቶች ቢያንስ 73 ሰዎች መጎዳታቸውን አስታወቀ።
ጥቃቶቹ መቼ እንደተፈጸሙ በግልጽ ባይነገርም የጥምረቱ ጦር ለእነዚህ የሁቲ ታጣቂዎች ጥቃቶች ጠንካራ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።
በየመን በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸውን አካባቢዎችን እንዲሁም የአገሪቱን ሰሜናዊ አብዛኛውን ከፍል የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች፣ ሐምሌ ወር በሳዑዲ ላይ የባሕር ላይ እንቅስቃሴ እገዳ መጣላቸውን ካስታወቁ በኋላ ጥቃቶችን ሲፈጽሙባት ቆይተዋል፤ በቀይ ባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦቿንም ዒላማ አድርገዋል።
በየመን በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ቱርኪ አል ማሊኪ በቅርቡ የተባባሰውን ግጭት “አደገኛ” ሲሉ ገልጸው፣ ሁቲዎቹ በዓለም ትልቋ የነዳጅ ላኪ እና በኦፔክ ውስጥ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነችውን የሳዑዲ አረቢያን ሲቪል እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ዒላማ እንዳደረጉ ገልጸዋል።
ሁቲዎቹ በሳዑዲ ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች ጂዛን እና ናጅራንን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ያሉ ዒላማዎችን ማጥቃታቸው ተዘግቧል።
ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው፣ በጂዛን የሚገኙ የአራምኮ የነዳጅ ተቋማት በአዲስ ጥቃት ዒላማ የተደረጉ ሲሆን፣ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ እየተገመገመ ነው። አራምኮ በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
የሳዑዲ ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በሁቲዎች የተፈጸሙት ጥቃቶች "በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት" ማድረሳቸውን እና ጥቃቶቹ ባስነሱት የእሳት ቃጠሎም "በበርካታ ስፍራዎች ላይ ሥራዎች እንዲቋረጡ" ምክንያት ሆኗል ብሏል።
የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁቲዎች የፈጸሙትን እና "በይ ባሕር ላይ የንግድ መርከቦችን ዒላማ በማድረግ" የቀጠሉትን ጥቃቶች አውግዟል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተገቢውን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን ተግባራዊ በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።