ዋይት ሐውስ ላይ በስናይፐር እና በድሮን ጥቃት ለመፈጸም ያለመ ቡድንን መያዙን ኤፍቢአይ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤፍቢአይ እሁድ ዕለት በዋይት ሐውስ ተዘጋጅቶ የነበረ ስፖርታዊ ውድድር ላይ ለመፈጸም ታቅዶ የነበረን ጥቃት ማክሸፉን እና አምስት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።
ከዕቅዱ መካከል በአቅራቢያ የሚገኙ ሕንጻዎችን በድሮኖች መምታት እንዲሁም "ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ዒላማ" ማድረግ እንደነበር አቃቤ ሕግ አስታውቋል።
አንዱ ተጠርጣሪ ባለፈው ሳምንት በኦሃዮ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን መርማሪዎች አብሮት ካሴረ ግለሰብ ጋር የተለዋወጣቸውን እንዳይነበብ የተደረገ መልዕክትን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
አቃቤ ሕጎች በክስ መዝገቡ ላይ "ዋልታ ረገጥ የሃይማኖት አስተሳሰብ እና ጸረ መንግሥት አመለካከት" እንደታየባቸው ገልጸዋል።
የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፕቴል "ታቅዶ የነበሩት ጥቃቶች በበርካታ የመንግሥት አካላት ጥረት ከሽፈዋል" ሲሉ በማኅበራዊ ሚደያ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።
በኦሃዮ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ የ19 ዓመቱ ታይሲን ሲ ፕሮፐር፣ የ24 ዓመቱ ብራያን ኦማር ሮአ ናቸው።
በካሊፎርኒያ ደግሞ የ32 ዓመቱ ማይክል አለን ቶማስ፣ ሚዙሪ ውስጥ የ32 ዓመቱ ዳንኤል ኬ ኢስክሪጅ፣ ከነበራስካ የ31 ዓመቱ አብርሃም ሄርሞሲሎ አልቫሬዝ በፖሊስ ተይዘዋል።
በአራት የአሜሪካ ግዛቶች በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ግድያ ለመፈጸም በማሴር መከሰሳቸውን የአገሪቱ ፍትህ ቢሮ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
ተጠርጣሪዎቹ ጥቃቱን ለመፈጸም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ውዥንብር ለመፍጠር እና ሰዎችን በስናይፐር ዓልሞ ወደሚመታው ቡድን ለመምራት አቅደው ነበር ተብሏል።
"ሁለተኛው ቡድን" ወደ ዋይት ሐውስ በሮች በማምራት ዒላማዎች ላይ ጥቃት ለማቀድ ተዘጋጅቶ ነበር ተብሏል።
እሁድ ዕለት በተዘጋጀው ስፖርታዊ ውድድር ላይ 4,300 ሰዎች የተጋበዙ ሲሆን ውድድሩን ከቅርበት የሚመለከቱ ተጨማሪ 85,000 ሰዎች ደግሞ ነበሩ።
በአልቫሬዝ ላይ የቀረበው ክስ ቡድኑ ዶናልድ ትራምፕን፣ ምክትላቸው ጄዲ ቫንስን፣ ምንም እንኳን በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ባይሆንም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን እና ኤለን መስክን እና ሌሎች የምክር ቤት አባላትን ዒላማ ለማድረግ አቅዶ እንደነበር ያስረዳል።
ቡድኑ ጥቃት ለመፈጸም ማቀዱ የተደረሰበት በፕሮፐር በኩል ነው።
እአአ ሰኔ 10 ስጋት የገባት የፕሮፐር እናት ለፖሊስ በመደወል ልጇ ጦር መሣሪያዎችን እየገዛ መሆኑን እና በኦንላየን ከቀድሞ የሠራዊቱ አባላት እና ክርስትያን መሆናቸውን ከሚገልጹ ሰዎች ጋር ላይ የሚያደርጋቸውን ውይይቶችን መመልከቷንም አስታውቃለች።
ቡድኑ ፖለቲከኞች እና ሃብታሞች ናቸው ተብሎው የተለዩ "ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው አካላትን" በመግደል አብዮት የመቀስቀስ ዓላማ ነበረው ተብሏል።
ቡድኑ "በመንግሥት ሙሰኝነት ላይ ስላላቸው ብስጭት፣ ኢፕስቴን ሰነድ ስለተያዘበት መንገድ፣ በርካታ ውሃ ስለሚጠቀሙ የዳታ ማዕከላት፣ እና ሌሎች የመንግሥት ተግባራት ላይ" መወያየታቸውን አቃቤ ሕግ አስታውቋል።
የቡድኑ አባላት "ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየሄደች ነው ብለው የሚያምኗትን ዩናይትድ ስቴትስን መከላከል" እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን የኤፍቢአይ ሰነዶች ያሳያሉ።
ሰነዱ አክሎም "የቡድን አባላቱ ዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ በሙሉ ፈርሳ ዳግም መገንባት አለባት የሚል እምነት አላቸው" ይላል።
ፕሮፐር ሰኔ 11 ከኤፍቢአይ ለቀረበለት ጥያቄ የቡድኑ አባል መሆኑን አምኖ ከሌሎች ጋር መነጋገር የጀመሩት በመጋቢት ወር "ቫንጋርድ ኦፍ ዘ ኦልድ" በተባለ የቲክቶክ ገጽ አማካነት መሆኑን ተናግሯል።
ቡድኑ ከሌላ ግዙፍ አካል ጋር ግንኙነት ያለው ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም፤ ነገር ግን ፕሮፐር የቡድን አባላቱ የተመለመሉት በቲክቶክ አማካኝነት መሆኑን ተናግሯል።
በሌላ የቡድን አባላት የተጠቆሙ ሰዎች በሲግናል የመልዕክት መለዋወጫ በኩል እንዲወያዩ ይደረጋል ሲል አቃቤ ሕግ አስታውቋል።
አክሎም የመልዕክት መለዋወጫው ላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ 19 ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል።
ማክሰኞ ዕለት የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ማት ክዊን ስለ ከሸፈው ጥቃት ተጠይቀው "አሳሳቢ ስጋት ነው" በማለት ጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተደረገ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል።















