ሶማሊላንድ በእስራኤል እውቅና ከተሰጣት በኋላ በእየሩሳሌም ኤምባሲዋን ከፈተች

የፎቶው ባለመብት, Prime Minister of Israel's Office
ከሶማሊያ የተነጠለችው ሶማሊላንድ በእስራኤል የመጀመሪያዋን እውቅና ካገኘች ከስድስት ወር በኋላ በእየሩሳሌም ኤምባሲዋን ከፈተች።
የዲፕሎማቲክ ተልዕኮው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ባሉት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዲርሀማን መሐመድ አብዱላሂ በምዕራብ እየሩሳሌም ተመርቆ ተከፍቷል።
ከፕሬዝዳንቱ ጋር የተነጋገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ "በሕዝቦቻችን መካከል ጥልቅ መንፈሳዊ ግንኙነት" አለ ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትመለከታት ሞቃዲሾ "በሰሜን ሶማሊያ ከተገንጣይ አስተዳደር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ሉዓላዊነቴን እንደመጣስ ይታያል" ብላለች።
ባለፈው ታኅሳስ እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠቷ አወዛጋቢ ነበር።
ቻይና፣ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በርካታ አገራት እና ድርጅቶች እውቅናውን ተችተዋል።
ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ እስራኤል እና ሶማሊላንድ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ነው።
በጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት ጅማሮ አካባቢ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል።
ሶማሊላንድ አብዛኞቹ የውጭ አገራት ኤምባሲዎች ካሉበት ከቴል አቪቭ ይልቅ የዲፕሎማቲክ ተልዕኮዋን በእየሩሳሌም ለመክፈት መወሰኗ በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ተወድሷል።
እስራኤል እአአ በ1967ቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነበር ምሥራቅ እየሩሳሌምን የወረረችው። አካባቢውን በ1980 ገንጥላ የወሰደች ሲሆን፤ ይህ እርምጃዋ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ያላገኘ ነው። እስራኤል ሁሉንም የእየሩሳሌም አካባቢ "ዘላለማዊ እና ያልተከፋፈለ" ዋና ከተማዋ እድርጋ ታያለች።
ፍልስጤማዊያን ምሥራቅ እየሩሳሌምን ወደፊት ለመመስረት ተስፋ ላላቸው አገራቸው ዋና ከተማቸው እንዲሆን ይፈልጋሉ።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ አገራት ኤምባሲያቸው በቴል አቪቭ ሲሆን፤ አሜሪካ ግን በ2018 በዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ወደ እየሩሳሌም አዛውራለች።
ጓቲማላ፣ ሁንዱራስ፣ ኮሶቮ፣ ፓፓ ኒው ጊኒ፣ ፓራጓይ እና ፊጂ በከተማው ኤምባሲ ያላቸው አገራት ናቸው።
የፍልስጤም አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በተወረረው እየሩሳሌም 'ሶማሊላንድ' በተባለ አገር ተከፈተ የተባለውን ኤምባሲ" አውግዟል።
"ይህ እርምጃ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዓለም አቀፍ ቅቡልነት ጋር የተያያዙ ደንቦችን በግልፅ የሚጥስ ነው" ብሏል።
ነገር ግን ኔታኒያሁ "በጥንታዊ መዲናችን" ባሏት እየሩሳሌም ኤምባሲው መከፈቱን አመስግነዋል።
የእየሩሳሌም ሁኔታ ከሶማሊላንድ የእውቅና ጥሪ ጋር ተመሳሳይነት አለውም ሲሉም ጠቁመዋል።
"አገራት ሉዓላዊነታችሁን፣ መብቶቻችሁን፣ የራሳችሁን አገር መብቶች እውቅና እንዲሰጧችሁ እየጠበቃችሁ ነው። እኛም በዋና ከተማችን ይህኑ እየጠበቅን ነው። ከንጉስ ዳዊት ጀምሮ የአይሁድ ሰዎች ብቸኛ ዋና ከተማ ነው። ይህ ከ3,000 ዓመት ወዲህ ማለት ነው። ስለዚህ ለአንድ አገራት የዘገየ እውቅና ነው። ለእናንተ ግን ወዲያው አድርጋችሁታል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት አብዱላሂ በበኩላቸው ኔታኒያሁ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት ላሳዩት ቁርጠኝነት አሞካሽተዋቸዋል።
በዋናነት በቀይ ባሕር አፍንጫ ላይ የሚገኙ የሶማሊላንድን የተፈጥሮ ኃብት በተለይም እንቁ ማዕድናት እና ነዳጅ ለማልማት በትብብር የመስራት እድልን አንስተው አጋርነቱን "ስልታዊ" ሲሉ ገልፀውታል።
ለእስራኤል አጋርነቱ በቁልፍ ቀጣናው የተረጋጋ አጋር እንድታገኝ ያደርጋታል።
ጉብኝቱን አስመልክቶ ምላሽ የሰጠው የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሶማሊያን አንድነት እና መረጋጋት የሚያኮስስ ብሎታል።
ሶማሊላንድ የሞቃዲሾ ማዕከላዊ መንግሥት ከወደቀ እአአ ከ1991 ወዲህ ራሷን እያስተዳደረች ትገኛለች። የራሷ ምርጫ፣ ገንዘብ እና የደኅንነት ኃይል ያላት እንዲሁም ከሰሜን ሶማሊያ አንፃር የተረጋጋች ናት።
ይሁን እንጂ አገር የመሆን ፍላጎቷ ከእስራል በቀር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና አላገኘችም።















