በኢቦላ የተያዘች የ6 ዓመት ሕጻን ከሕክምና ማዕከል ከእናቷ ጋር ተጠልፋ ተወሰደች

ሙሉ ሰውነትን የሚሸፍን መከላከዑኣ የለበሱ ሁለት ሐኪሞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኢቦላ እንዳለባት በምርመራ ተረጋግጦ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሕክምና ማዕከል ውስጥ የነበረች የስድስት ዓመት ሕጻን ተጠልፋ መወሰዷን የጤና ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ሰኞ ዕለት በሰሜናዊ ኪቩ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ቡቴምቦ ከተማ ወደ ሚገኝ ክሊኒክ ስለታማ መሳሪያዎችን ታጠቀው ጥሰው የገቡ ሰዎች ናቸው ታዳጊዋን እና እናቷን ጠልፈው የወሰዱት።

ይህንንም ተከትሎ እናትና ልጅ የሕክምና እንክብካቤ ከሚደረግበት ተቋም ውጪ የሚቆዩ ከሆነ የኢቦላ ቫይረስን ወደ ሌሎች ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ የጤና ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።

"እናትና ልጇን ለማግኘት እየፈለግን ቢሆንም እስካሁን አላገኘናቸውም። ወደ ማኅበረሰቡ ከገቡ ለራሳቸው ጤና አደገኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ወደ ሌሎች ሰዎች በሽታውን ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ በተቻለ ፍጥነት ወደ ኢቦላ ሕክምና ማዕከል እንዲሄዱ እንማጸናለን" ሲሉ በሰሜናዊ ኪቩ የኢቦላ ክስተትን የሚከታተለው ቡድን ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሉባምቦ ማቦኮ ጋስተን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ቢቢሲ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ ቢያቀርብም መልስ አላገኘም።

እናት እና ልጅ ከሕክምና ተቋም የተጠለፉበት ዜና የተሰማው ቡንዲቡጊዮ የተባለው አደገኛ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በከሰቱ ከተነገረ ሁለት ወራት ካለፉት በኋላ ነው።

የእርዳታ ድርጅቶች የቫይረሱን ማስፋፋት ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የተዛባ መረጃ ሥርጭት፣ የጤና ባለሙያዎች ላይ አለመተማመን እና በሽታውን ለመከላከል ለሚያስፈልጉ እርምጃዎች ተገዢ አለመሆንን ጨምሮ ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን የኢቦላ ሕክምና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ብሩኖ ሚቾን ባልደረቦቻቸው በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ለመለየት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከባድ ፈተና እደገጠማቸው ተናግረዋል።

የዲሞክራቲክ ኮንጎ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሠረት አሁን የኢቦላ ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ 837 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን አስከ ሰኞ ሰኔ 8 ድረስ 196 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ይህም በወረርሽኙ ከተያዙት መካከል ያጋጠመው የሰዎች ሞት 23.4 በመቶ ነው።

ባለሥልጣናት ጨምረውም ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል እስካሁን 49 ህሙማን ከበሽታው አገግመዋል። 376 ሰዎች ደግሞ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው ሕክምና እና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው።

አሁን ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ አብዛኛው የተመዘገበው ኢቱሪ በምትባለው ግዛት ውስጥ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ደግሞ ሰሜናዊ ኪቩ ግዛት ትገኛለች።