"የዓለም ዋንጫው የእኛ አይደለም" - አሜሪካ ቪዛ የከለከለቻቸው ተመልካቾች

የፎቶው ባለመብት, Julien Kouadio Adonis
የአይቮሪ ኮስት ደጋፊዎች ማኅበር አባል የሆነው ጁሊያን ኮዋዲዮ አዶኒስ "ስሙን የማንጠራው ዓይነት የማግለል አካሄድ ነው። የትኛውም የአውሮፓ አገር የቪዛ ክልከላ አልተጣለበትም፤ ለምን አፍሪካ ብቻ?" ይላል።
ማኅበራቸው ደጋፊዎችን ለዓለም ዋንጫ ሲልክ ቢቆይም በዚህኛው የዓለም ዋንጫ ጥረት ማድረግም እንደማያወጣ አምነዋል።
የትኬት ዋጋ ከ300 እስከ 5,000 ዶላር እንደሚደርስ የሚናገረው አብዱላ "ደጋፊዎችን መቀበል የማይፈልግ አገር የዓለም ዋንጫን እንዲያስተናግድ ሊፈቀድለት አይገባም" ይላል።
"እግር ኳስ ትዕይንት ነው። ትዕይንት ደግሞ ተመልካች ይፈልጋል። አሜሪካ ይሄንን አላሳካችም" ሲልም ያክላል።
42 ሃብታም አገራት ያለ ቪዛ የመታደም ዕድል ቢሰጣቸውም አንድም የአፍሪካ አገር በዝርዝሩ አልተካተተም።
ቪዛ የሚጠይቁ ሰዎች 185 ዶላር ከፍለው ውድድሩ ሲያበቃ ከአሜሪካ ለመውጣት ስላላቸው ዕቅድ እና ለቆይታቸው የሚበቃ ገንዘብ እንዳላቸው ለማሳየት በአካል ቃለ ምልልስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ለዓለም ዋንጫ ያለፉ አገራት (አልጄሪያ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሴኔጋል እና ቱኒዝያ) ዜጎች ለዓለም ዋንጫ ትኬት እስከገዙ ድረስ ቪዛ ሲጠይቁ የሚጠበቅባቸውን 15,000 ዶላር ማስያዝ እንደማያስፈልጋቸው ይፋ ተደርጓል።
ቢቢሲ ከተለያዩ አገራት ያነጋገራቸው እግር ኳስ ወዳጆች በገጠሟቸው መሰናክሎች ቁጣና ብስጭት ገብቷቸዋል።
በትራምፕ የጉዞ ክልከላ ውስጥ የገቡ በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ አገራት ሄይቲ፣ ኢራን፣ ሴኔጋል እና አይቮሪ ኮስት ናቸው። ስለዚህም ዜጎቻቸው የቱሪስት ቪዛ ማግኘት አይችሉም።

የፎቶው ባለመብት, Aliou Ngom
ሴኔጋላዊው አሊዎ ንጎም ያለፉትን ሁለት የዓለም ዋንጫዎች በኳታር እና ሩሲያ ታድሟል።
"የመላው ዓለም ባህሎች አንድ ላይ ሲመጡ ማየት ትልቁ አስደሳች ቅጽበት ነው" ይላል።
አምና የሴኔጋል የሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድን ብዙ አባላት ቪዛ ተከልክለዋል።
አሊዎ ቪዛ ማመልከት ትርጉም እንደሌለው ተሰምቶታታል።
ቢቢሲ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ላይ ያደረገው ቅኝት እንደሚያሳየው፤ ለዓለም ዋንጫ ካለፉ 48 አገራት ውስጥ 11 በሚሆኑት የቪዛ ክልከላ መጠን ከ40 በመቶ በላይ ነው።
የቢዝነስ ተጓዦች የሚጠይቁት ቢ1 እና ቱሪስቶች የሚጠይቁት ቢ2 ቪዛ ላይ ያለው የክልከላ መጠንም ከዚህ ጋር ተቀራራቢ ነው። የሁሉም አገራት የቪዛ ክልከላ መጠን 34 በመቶ ይደርሳል።
መረጃው የተሰበሰበው ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2024 ጀምሮ እስከ መስከረም 2025 ድረስ ነው።
11ዱ አገራት ኢኳዶር፣ ግብፅ፣ ሄይቲ፣ አልጄሪያ፣ ኡዝቤኪስታን፣ ኬፕ ቬርዴ፣ ዮርዳኖስ፣ ኢራን እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናቸው።
ከእነዚህ አገራት ቪዛ የሚያመለክቱ ዜጎች የመከልከል ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ገንዘባቸውን ማባከን አይፈልጉም።
ትኬት የገዙት በቀጥታ ከፊፋ ከሆነ በይፋዊ የፊፋ ድረ ገጽ ላይ ገንዘብ ከፍለው ትኬቱን መልሰው መሸጥ ይችላሉ።
የቪዛ ሒደትን ለማፋጠን ፊፋ የይለፍ ሥርዓት ዘርግቷል።
አሜሪካ የሚገኘው የስደተኞች ጥብቅና ተቋም ኃላፊ ሴሊን አታላህ "የፊፋ የይለፍ ሥርዓት የቪዛ ቃለ መጠይቅን ለማፋጠን ያግዛል" ትላለች።
የይለፍ ሥርዓት ሒደቱን ቢያፋጥንም የቪዛ ጥያቄ አወንታዊ መልስ ማግኘቱን አያረጋግጥም።
"የቪዛ ሒደት የእጅ አዙር ክልከላ ሥርዓት ነው። ፊፋ ትኬት ቢሸጥም ቪዛ ለማን ይሰጣል የሚለው የሚወሰነው በአሜሪካ መንግሥት ነው። የድንበር ጥበቃ ደግሞ ማን ወደ አገሪቱ መግባት እንደሚችል ይወስናል" ስትል ሴሊን ታስረዳለች።
ቪዛ ያላቸው ሰዎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ በድንበር ጥበቃ ባልደረቦች ሊከለከሉ ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Abdulla Adnan
ኢራቅ ለዓለም ዋንጫ ስታልፍ ከኖርዌይ እና ከፈረንሳይ ጋር የምታደርገውን ግጥሚያ ለመመልከት አብዱላ አድናን ትኬት ቆረጠ።
ኢራቅ ጨዋታውን የምታደርገው በአሜሪካዎቹ ከተሞች ቦስተን እና ፊላዴልፊያ ውስጥ ነው።
"ጨዋታውን ስቴድየም ገብቼ ለማየት፣ ከሕዝቡ ጋር አብሬ ቡድኔን መደገፍ ትልቅ ነገር ነው። እንደዚህ ዓይነት ስሜት የሚሰጠኝ ሌላ ነገርም የለም" ይላል።
ከአውሮፓውያኑ 1986 ወዲህ ኢራቅ ለዓለም ዋንጫ ስታልፍ ሁለተኛ ጊዜዋ ነው።
ሆኖም የዓለም ዋንጫ ተመልካቾች ቪዛ ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል።
ቪዛ የተከለከለው አብዱላ ብቻ አይደለም። ቢቢሲ የሠራው የጉዞ ዳሰሳ እንደሚያሳየው፤ በዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉ አገራት ሩብ ያህሉ ከጉዞ ዕገዳ ጋር በተያያዘ ዜጎቻቸው ቪዛ ማግኘት አልቻሉም።
ኢራቅ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጉዞ ዕገዳ ከጣሉባቸው አገራት መካከል ባትሆንም ቪዛ ማግኘት አልተቻለም።
የኢራን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በኢራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።
ስለዚህም አብዱላ እና ሌሎችም ኢራቃውያን የቪዛ ቃለ መጠይቅ የሚያደርጉበት ሥፍራ የለም።
ለቃለ መጠይቅ ዮርዳኖስ ቢሄድም የአገሪቱ ዜጋ ስላለሆነ የአሜሪካ ኤምባሲ ሊያስተናግደው አልቻለም።
ለዓለም ዋንጫ ትኬት የገዛበት ገንዘብ እና ዩርዳኖስ የሄደበት ወጪ ሲደማመር 1,800 ዶላር ይደርሳል።
ቱርክ ካለው የአሜሪካ ኤምባሲ ለማመልከት አስቦ ነበር። ነገር ግን ሒደቱ ሁለት ሳምንት የሚወስድ ከመሆኑም በላይ ላይሳካ ስለሚችል ተስፋ ቆረጠ።
የዩርዳኖስ እግር ኳስ ማኅበር ኃላፊ አቡ ካስ እንደሚለው በዚህ ዓመት አሜሪካ 57 በመቶ የቪዛ ጥያቄዎችን ውድቅ አድርጋለች።
"ላለፉት ሦስት እና አራት ወራት ቪዛ እየከለኩ ነበር። አንድም ቪዛ የተሰጠው ደጋፊ አላውቅም" ይላል።
ማኅበሩ ለቢቢሲ እንደገለጸው አንድ ዮርዳኖሳዊ ብቻ ቪዛ አግኝቷል።
አቡ እንደሚለው፤ በዮርዳኖስ አማን ለቪዛ ቀጠሮ ከ42 በላይ ሰነዶች ይዞ ቢሄድም ጥያቄው ውድቅ ተደርጓል።
አሜሪካ የቪዛ ጥያቄን ውድቅ የምታደርግበትን ምክንያት የማሳወቅ ግዴታ የለባትም።
"የዓለም ዋንጫ የኛ አይደለም። አረቦች የሉበትም። እናም የእነሱ የዓለም ዋንጫ ነው። የደጋፊዎች ማኅበር ኃላፊ ቪዛ ከተከለከለ ማን ይሰጠዋል?" ሲል ይጠይቃል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአሜሪካ የስደተኞች ጉዳይ አገልግሎት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ድንበር ስለሚሻገሩ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ይገልጻል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ባወጣው መረጃ መሠረት ከጥቅምት 2023 እስከ መስከረም 2024 ድረስ ከ538 ሺህ በላይ ሰዎች የቪዛ ቆይታ ጊዜያቸውን አልፈው አሜሪካ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስደተኞችን ዒላማ አድርገው እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት 14 ሚሊዮን ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ በአገሪቱ ይኖሩ እንደነበር ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በፊፋ ታሪክ ትልቁ ለሆነው የዓለም ዋንጫ ከመላው ዓለም ታዳሚዎችን ለመቀበል ዝግጁ ነን" ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።
"አብዛኞቹ የውጭ ጎብኚዎች ከካናዳ ወይም ያለ ቪዛ መጓዝ ከሚችሉት 42 አገራት ዜጎች ስለሆኑ የፊፋ የይለፍ ሥርዓት አላስፈለጋቸውም" ሲልም አክሏል።
እያንዳንዱ ቪዛ አመልካች "ለአሜሪካ ደኅንነት አደጋ እንደማይሆን ጊዜ ወስደን እንፈትሻለን" ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ "እያንዳንዱን የቪዛ ጥያቄ ለየብቻ ለይተን አይተን በአሜሪካ ሕግ ተቀባይነት ያላቸውን እንወስናለን" ሲልም ጨምሮ ገልጿል።
ያለፉትን አራት የዓለም ዋንጫዎች ያስተናገዱ አገራት ለተመልካቾች የቪዛ ሥርዓት ዘርግተዋል።
በ2022 ኳታር 'ሀያ ካርድ' በሚል ለደጋፊዎች የቪዛ ማግኛ ሰነድ አዘጋጅታ ነበር።
በ2026 በሩሲያም ተመሳሳይ አሠራር ተተግብሯል። የደጋፊዎች መለያ ካርድ የገዙ ተመልካቾች ያለ ቪዛ መግባት ይችሉ ነበር።
በ2014 በብራዚል እና በ2012 በደቡብ አፍሪካ ደጋፊዎች በቀላሉ ቪዛ የሚያገኙበት መንገድ ተመቻችቶ ነበር።
ካናዳ እና ሜክሲኮ የተወሰኑ ጨዋታዎችን ቢያስተናግዱም የዋንጫ ፍልሚያውን ጨምሮ ከ104 ግጥሚያዎች 78 የሚሆኑት አሜሪካ ይካሄዳሉ።
ካናዳ እና ሜክሲኮ እንደ አሜሪካ የቪዛ ክልከላ አላደረጉም። ለዓለም ዋንጫ ካለፉ አገራት ውስጥ ካናዳ የቪዛ ማስተናገጃ ማዕከል የሌላት በኢራን እና ኬፕ ቨርዴ ብቻ ነው።
ካናዳ በቪዛ ዓይነት ላይ የሚወሰን የክልከላ አካሄድ ባይኖራትም በ2025 አጠቃላይ የቪዛ ክልከላ 54% ነበር።
ሜክሲኮ ቪዛ የሰጠችበትን እንዲሁም የከለከለችበትን መረጃ ይፋ አታደርግም።
ለዓለም ዋንጫ ካለፉ አገራት በስምንቱ ውስጥ ሜክሲኮ ዲፕሎማሲያዊ መቀመጫ የላትም።















