ኢትዮጵያ ቡክ ፎረም፡ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ለ17 ዓመታት እየተወያዩ ያሉት የመጽሐፍት ወዳጆች

የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ተወያዮች

የፎቶው ባለመብት, ARTS TV

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም እስካሁን ድረስ ከ200 በላይ መጻሕፍት ላይ ውይይት አካሂዷል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ፋሲካ ሲደልል ከአራት ዓመት በፊት "የሻምላው ትውልድ" የተሰኘውን መጽሐፋቸውን ሲያወጡ፤ 'የተጻፈ ይከርማል' የሚለውን ብሒል በመከተል ነበር።

በዚህ መጽሐፋቸው የኢኮኖሚ ጉዳይ ኃላፊ እስከ መሆን ስለደረሱበት የወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ከትበዋል።

የመጽሐፋቸው ታሪካዊ ፋይዳም የሚያጠያይቅ አልነበረም። ፋሲካ የከተቡት፣ የጻፉት ሁሉ ግን ከግድፈት የጸዳ አልነበረም። 'የሻምላው ትውልድ'፣ መጽሐፋቸው በርካታ የፊደል ግድፈቶች ነበሩበት። ኋላ ላይ ሲናገሩ "የፊደል ስሕተቱ ከልክ በላይ ነበር። በአንድ ገጽ ላይ ብቻ ሳይ ከ20 በላይ የፊደል ስሕተት አግኝቻለሁ" ብለዋል።

ይህንን ያህል ግድፈት መኖሩን እና አንዳንድ ወሳኝ ኹነቶችን ያላካተተ መሆኑን ጆሯቸው ያደረሰው በአንድ ዲጂታል የመጽሐፍት ክበብ ላይ የተነሳ የመረረ ትችት ነው። ይህ የውይይት ክበብ 'ኢትዮጵያ ቡክ ፎረም' ይሰኛል።

ከዲጂታል ክበቡ መስራቾች አንዱ የሆነው የአርትስ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳንኤል በላይነህ "ልዩ" ብሎ ከሚጠቅሳቸው ውይይቶች አንዱ የሻምላው ትውልድ ላይ የተደረገውን ነው።

ፋሲካ ምን ትችቱ ቢሰላ አልተቀየሙም። "በጣም፣ በጣም ነው የወደድኩት" ሲሉ ክበቡ ባዘጋጀው እና "ቆይታ ከደራሲያን ጋራ" በሚባል የአዳራሽ ውይይት ላይ ተናግረዋል።

ወቀሳውን ተቀብለው ብቻም አልቀሩም፤ የሻምላው ትውልድ ሁለተኛ ዕትም እነዚህን ግድፈቶች አርመዋል።

ንባብና መጻሕፍት ባሰባሰቧቸው ሰዎች የተመሰረተው ይህ የንባብ ክበብ፣ እስከ ሐምሌ 24፣ 2018 ዓ.ም 205 መጻሕፍት ላይ ውይይት አካሂዷል።

ኢትዮጵያ ቡክ ፎረምን እነማን ጀመሩት?

የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም መሠረቱን የተከለው በ2001 ዓ.ም. ገደማ ነው። ከዛሬ 17 ዓመት በፊት። ከመጻሕፍት ጋር ጥሩ ጉርብትና ከንባብ ጋር ጠንካራ ዝምድና ያላቸው ዳንኤል በላይነህ እና ማኀደር ገብረመድኅን የተባሉ ሁለት ሰዎች ናቸው በዋናነት የመሠረቱት።

ማኀደር መደበኛ ሞያው አርክቴክቸር ሲሆን የ'የማ አርክቴክቸር" ዋና አርክቴክት፣ በሸገር ራዲዮ "ከቤት እስከ ከተማ" ፕሮግራም አዘጋጅ እና ፤"ከቤት እስከ ከተማ፡ የከተማ ማዕከል" ዋና ዳይሬክተርም ነው።

ስለ ኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ጅማሮ ሲያስታውስ፤ ለእረፍት ከኢትዮጵያ ውጭ ወደሚኖሩት ወዳጆቹ ሲሄድ ዳጎስ ያሉ መጻሕፍትን በመሸመት ነበር ። ከአዲስ አበባ የሚሸምታቸው መጽሐፍት ካናዳ ለሚኖረው ወዳጁ ዳንኤል እና ለሌሎች አንባቢያን የሚሰጠው ነው።

እሱም እረፍቱን ጨርሶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም በተመሳሳይ መልኩ በርከት ያሉ መጻሕፍትን በመሸከም ነው።

በወቅቱ ካናዳ ይኖር የነበረው ዳንኤል በላይነህ ያነበባቸውን መጽሐፍት በተመለከተ ግምገማ (Review) እየፃፈ ማጋራት ጀመረ። ያ ጊዜ ደግሞ እነ ሻማ ቡክስ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ እና ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት በርከት ያሉ የአገር ውስጥ መጻሕፍትን ለአንባቢያን ያቀረቡበት ነበር።

በዚህ ሁኔታ ንባባቸውን ሲያሳልጡ፣ ባነበቧቸው መጽሐፍት ላይ ሃሳብ ሲለዋወጡ ዛሬ ላይ ቢሊዮን ሰዎች የሚጠቀሙት ፌስ ቡክ በተደራሽነቱ ሰፋ ላለ ቁጥር ለማዳረስ ቀላል አማራጭ ሆኖ ከች አለ። የንባብ ልምዳቸውን ለማካፈልም አዲስ ነገርን አከለ።

የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም የሚወያይባቸውን መጽሐፎች ማስታወቂያ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopia Book Forum

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም በይፋ መምረጫ ዘዴ አንባቢያንን ካስመረጠ በኋላ የሚወያይባቸውን መጽሐፍት በቅድሚያ ለተሳታፊዎች በማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ ያስተዋውቃል (የምዕራፍ 7 ማውጫ)

በእነዚህ አሳታሚ ድርጅቶች ለአባቢያን ከሚቀርቡ የመጽሐፍ ዓይነቶች ውስጥ ግለ ታሪክ እና በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ የታሪክ መጻሕፍት የእነ ማህደር ቀዳሚ ምርጫዎች ነበሩ።

አብዛኛውን ጊዜ ያነበባቸውን መጻሕፍት ላይ ግምገማ (Review) በመጻፍ በፌስቡክ የሚያጋራው፣ በአሁን ወቅት የአርትስ ቲቪ ሥራ አስፈጻሚው የሆነው ዳንዔል በላይነህ እንደነበር ማኀደር ያስታውሳል። "ከ90 በመቶ በላይ የግምገማ ጽሑፎችን ያዘጃገው ዳንኤል ነበር" በማለትም ይመሰክራል።

በጊዜ ሂደት በፌስቡክ የሚሰራጨውን የመጻሕፍት ግምገማ የሚከታተል ሰው ቁጥር እየጨመረ መጣ። ዳንኤል ያነበባቸው መጽሐፍት ላይ የተሰማውን ሃሳብ ፌስ ቡክ ላይ ማጋራት የጀመረው "እኔ ያገኘሁትን ደስታ፣ትምሕርት ጓደኞቻችንም ቢያገኙት ከሚል ሃሳብ በመነሳት" መሆኑን ይገልጻል። በኋላም ይህ ሙከራ የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ ገጽ እንድንከፍት አድርጓል በማለት ተናግሯል። የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም የፌስቡክ ገጹ ከተከፈተ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት 150 የሚሆኑ መጽሐፍት መገምገማቸውን (review) ያስታውሳል።

ዳንኤል ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ከማህደር ጋራ በመሆን በሚዘጋጁ የመጻሕፍት ምረቃ፣ ዐውደ ርዕይ፣ የውይይት መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፋቸው እንደ እነ አዳም ረታ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ ሌሊሳ ግርማ፣ ዘነበ ወላ ያሉ ደራሲያን ጋር በአካል ተዋወቁ።

ወደ 'ክለብ ሃውስ' የተደረገው ሽግግር

በንባብ ወዳጆች ተመስርቶ በፌስቡክ ሲንቀሳቀስ የቆየው "የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም"፤ የኮቪድ 19 ተከትሎ ከመጡ መተግበሪያዎች ለሥነ-ጽሑፍ ውይይት ይበልጥ ምቹ ወደሆነው "ክለብ ሃውስ" መተግበሪያ በነሐሴ 2012 ዓ.ም. ሽግግር አደረገ።

መተግበሪያው የውይይት ቡድን ለመመሥረት፣ ድምፅ ለመቅዳት፣ እንዲሁም የጽሑፍ መልዕክቶችን ለመላላክ የሚያስችል በመሆኑ መጻሕፍትን ማዕከል ላደረገው ውይይት እንደመረጡት ማህደር ያስረዳል። የዚህ አዲስ መድረክ ማሟሻ ይሆን ዘንድም፣ የመጀመሪያው ውይይት የተካሄደው በደራሲ አዳም ረታ "ግራጫ ቃጭሎች" መጽሐፍ ላይ ነበር።

በኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አባላት "በክለብ ሃውስ" ዘወትር እሑድ ከምሽቱ 2፡00 እስከ 4፡00 ሰዓት የሚደረገው ቋሚ የሥነ-ጽሑፍ ውይይት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ በርካታ አንባቢያንን በቀላሉ ለማሳተፍ መንገዱን አቅልሏል።

በበይነ-መረብ በሚካሄደው በዚህ ውይይት ላይ አንጋፋ ደራሲያን ይታደማሉ፤ ለሚነሳላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ይሰጣሉ።

"መደበኛ አንባቢዎች ነን የ ሂስም ሆነ ሥነ-ጽሑፍ ልምድ የለንም"

በክለብ ሃውስ መተግበሪያ ላይ ሦስት ዓመታትን ያሳለፈ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ከ5,300 በላይ አባላትን ያፈራ እና በፌስቡክ 15ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጸሐፍት ተዳስሰው ጠንካራ ትችቶችና አስተያየቶች ተንጸባርቆባቸዋል።

በዚህ የበይነ መረብ ውይይት ጥሩ የንባብ ልምድ ያላቸውና በውይይቶቹ ላይ ያለማቋረጥ ሲሳተፉ የነበሩ አባላት ቋሚ አሰናኞች ሆነው ዛሬ ድረስ ቀጥለዋል።

እያሰለሱ ከሚመጡት በርካታ አሰናኞች በተጨማሪ በየሳምንቱ የሚደረገውን የመጽሐፍ ውይይት በዋናነት የሚመሩት ማህደርን ጨምሮ ምሕረት ታየ፣ ስለሺ ይልማ፣ ዳዊት ብርሃኑ የተባሉ አራት አሰናኞች ሲሆኑ፣ በመደበኛ ሥራቸው አርክቴክቸር፣ የግራፊክስ ባለሞያ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን እንዲሁም የባንክ ባለሙያ ናቸው።

ይህንን የመጻሕፍት ውይይት ከዋና ሥራቸው ጎን በትርፍ ጊዜያቸው እንደሚያከናውኑት የሚናገረው ማህደር፤ "እኛ መደበኛ አንባቢዎች ነን እንጂ የሒስም ሆነ የሥነ-ጽሑፍ ሙያዊ ልምድ የለንም፤ ነገር ግን ሀሳባችንን በተረዳነው መልኩ እናጋራለን" በማለት የክበቡን መሠረታዊ መንፈስ ያስረዳል።

"ከአንዳንድ ደራሲያን መጽሐፍት አርትኦት ሥሩልን የሚል [ጥያቄ]" እንደሚመጣላቸው የሚያስረዳው ማህደር ጥያቄውን አርትኦት ለመሥራት ችሎታ እና ፍላጎት ላላቸው ባለሙያዎች እንደሚያስተላልፉ አስረድቶናል።

በኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ውይይት ከተደረገባቸው መጽሐፍት መካከል

የፎቶው ባለመብት, Ethiopia Book Forum

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ውይይት ከተደረገባቸው መጽሐፍት መካከል ጥቂቶቹ

ከበይነ-መረብ ውይይት እስከ "ቆይታ ከደራሲያን ጋር"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አባላት አሁን ላይ የክለብ ሀውስ መተግበሪያ ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ ተጠቃሚዎች እያስቸገረ በመምጣቱ ወደ ሌላ አማራጭ ለመኼድ በተሳታፊዎች ምርጫ ለውይይታቸው የቴሌግራም መተግበሪያ እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ሰዎች ውይይቱ ላይ መታደም ባይችሉ እንኳን መተግበሪያው እንደ "ክለብ ሀውስ" ድምጽን ቀድቶ የሚያስቀምጥ በመሆኑ በተመቻቸው ሰዓት እና ቀን ማድመጥ የሚያስችላቸው ነው።

በዘጠኝ ምዕራፍ ባደረጉት ውይይት እስካሁን በ205 መጻሕፍትን ዳሰሰዋል። ለምርጫ የሚቀርቡት ሁሉም መጽሐፍት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ዙሪያ ያተኮሩ በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተፃፉ ናቸው። ውይይት ከተደረገባቸው መጽሐፍት ውስጥ በስፋት የሚገኙት የግለ ታሪክ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ዳንኤል እነዚህ መጽሐፍት ላይ ትኩረት የተደረገበትን ምክያት ሲያስረዳ "የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ" እንደሚባለው።

እነሱን በደንብ ካልተረዳን የበፊቱን መገመት አንችልም የሚል ነገር ስላለኝ በአብዛኛው በጽሑፍ ሪቪው የተደረጉት መጽሐፎች ግለ ታሪክ በኢትዮጵያውን የተጻፉ የታሪክመጽሐፎች ላይ ነበር" ብሏል። ሆኖም ከሁለተኛው ምዕራፍ ጀምሮ ሁሉም አባላት ለውይይት እንዲቀርቡ የሚፈልጓቸውን መጽሐፍት እንደሚመርጡ ገልጿል። "በዚህ ምክንያት ነው ከግለታሪክ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ተሻግሮ ልብ ወለድ እና ትርጉም መጽሐፍት ላይ መወያየት የተጀመረው" ሲል የመጽሐፍት ዘውግ የሚመረጥበትን መንገድ አብራርቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበይነ መረብ ውይይቱ አንጋፋ እና ወጣት ደራሲያንም እየተሳተፉ ይገኛሉ።

"የጭድ እሳት ቆሳስለው የተረፉ ትዝታዎች" መጽሐፍ ደራሲ ፕሮፌሰር ጴጥሮስ ቶጃ መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አባላት ውይይት ከተደረገበት በኋላ የክበቡ ቤተኛ መሆናቸውን ነግረውናል።

ኑሮአቸውን በአሜሪካ ካደረጉ 46 ዓመት የሆናቸው ፕሮፌሰር ጴጥሮስ "ኩትዝታውን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ፔንሲልቬንያ" ውስጥ በ "ክሪሚናል ጀስቲስ" ትምሕርት ክፍል ውስጥ 27 ዓመታት በመምሕርነት አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አሰናኞች ከጄነራል መርእድ ንጉሴ ልጅ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Seleshi Yilma FB

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አሰናኞች ከጄነራል መርእድ ንጉሴ ልጅ ጋር (ከግራ ወደ ቀኝ) ዳዊት ብርሃኑ፣ ማህደር ገ/መድህን፣ አስተዋይ መርእድ፣ ምሕረት ታየ እና ስለሺ ይልማ

ከአራት ዓመት በፊት ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ የተደረገውን ውይይት "ግሩም እና አርኪ ነበር። በጣም ጠቅሞኛል" በማለት ይገልጹታል። በውይይቱ "በጣም ገንቢ እና ጠቃሚ" አስተያየቶች ተሰጥቶኛል ይላሉ ፕሮፌሰር ጴጥሮስ። ከመጽሐፉ ድህረ ቃል አንስቶ የሆሄያት ግድፈት እና ሌሎች ማሻሻያ ሀሳቦች ላይ የተሰጡ ትችቶችን በመቀበል ሁለተኛ እትም እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ከልጅነት ዕድሜያቸው አንስቶ ያላችው መጽሐፍት ፍቅር እና የኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ላይ የሚደረገው የመጽሐፍት ውይይቱ በበይነ መረብ መካሄዱ በተሳትፏቸው እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ ሌሎች ጸሐፍቶች ኢትዮጵያ ቡክ ፎረምን ተዛምደዋል።

በዚህ ረገድ "ደራሲያን የጻፏቸውን መጽሐፍት የሚያነቡ ጥልቅ አንባቢያን እንዳሉ በግልጽ እንዲያዩ" አድርጓል የሚል እምነት አላቸው የሚል እምነት እንዳለው ዳንኤል ይናገራል።

ሁሉም በሚባል ደረጃ ደራሲያን መጽሐፍቶቻቸው ላይ በሚደረገው ውይይት ደስተኞች ናቸው። "መጽሐፌን እንዳትተቹ" የሚሉ ደራሲያን አላጋጠሙንም ነገር ግን በኢትዮጵያ ቡክ ፎረም አባላት የተነሱ ትችቶች ቅር ያሰኛቸው ሁለት ጸሐፊዎች ስለመኖራቸው መስማቱን ማኅደር ይናገራል።

"አንዳንድ ደራሲያን ስትወያዩ "ቡክ ፎረም ፕሩፍ" ለማድረግ ተጨማሪ ጥንቃቄ እያደረጉ እንደሆነ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ማህደር አንስቷል።

ኢትዮጵያ ቡክ ፎረም ላይ የሚሳተፉ ደራሲዎች እያደገ መምጣቱ "ቆይታ ከደራሲያን ጋር" የተሰኘ መርሃ ግብር እንዲጀመር ምክንያት ሆናል።

በዚህ ዝግጅት ላይ በአካል ከተገኙት ተሳታፊዎች በተጨማሪ ውይይቱ ተቀርጾ በአርትስ ቲቪ መተላለፉን ተከትሎ በዩቲዩብ እና ፌስቡክ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ እና የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሌላ የመወያያ ዕድል በመፍጠሩ ከ160,000 በላይ ተመልካቾችን አግኝቷል።

ዝግጅቱ ደራሲያን እና ተደራሲያን በአካል ተገናኝተው ውይይት የሚያደርጉበት፣ የሚጠያየቁበት እና እውቀት እና ልምድ የሚቀስሙበት መድረክ ነው።

በስድስት መድረኮች በተካሔደው ፕሮግራም 20 አንጋፋ እና ወጣት ደራሲያን በዚህ ፕሮግራም ተጋብዘው ከአንባቢያን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

እስካሁን ውይይት ከተደረገባቸው መጽሐፍት ደራሲያን መኻል ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገበረወልድ፣ ሽብሩ ተድላ (ፕ/ር)፣ ታደለች ኃየለ ሚካኤል (አምባሳደር)፣ አንዳርጋቸው አሰደግድ፣ ይፍቱሥራ ምትኩ፣ ተካልኝ ገዳሙ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ አዜብ ወርቁ እና ሌሎች ደራሲያን ተሳትፈዋል።