ቀጥታ, ትራምፕ አሜሪካ የተተኳሾች እጥረት እንደገጠማት መረጃ ያወጡት ከባድ እስር ይጠብቃቸዋል ሲሉ ዛቱ

ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረገውን የመርከቦች ጉዞ በተመለከተ ከኦማን ጋር ስምምነት ላይ መድረሷን ገለጸች። የቀረበው ስምምነት ቴህራን ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚገቡ መርከቦች ጉዞ ላይ ቁጥጥር እንዲኖራት እንደሚያደርግ ተዘግቧል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በፊፋ ፕሬዝዳንት ላይ ዕምነት እደሌለው አሳወቀ

    ጂያኒ ኢንፋንቲኖ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ተቃውሞ የበረታባቸው የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ

    የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ድርሻን ለግል ባለሀብቶች አሳልፎ የሚሰጠውን ዕቅዳቸውን ካሳወቁ በኋላ ውዝግብ ውስጥ የገቡት የፊፋ ፕሬዝዳንት ሃሳባቸውን ቢሰርዙም የአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበራት አሁንም ተቃውሞ እያሰሙ ነው።

    አውሮፓውያኑ በፊፋው ፕሬዝዳንት ላይ ዕምነት እንደሌላቸው በመግለጽ እራሳቸውን የዓለም ዋንጫን ጨምሮ በፊፋ ከሚዘጋጁ ውድድሮች እንደሚያገሉ እየዛቱ ነው።

    የአውሮፓ አገራት የእግር ኳስ ማኅበር (ዩኤፋ) ምንም እንኳን የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የዓለም ዋንጫ ድርሻን የመሸጥ ዕቅድ ቢሰረዝም ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ አለመሟላታቸውን በመግለጫው አመልክቷል።

    "የዩኤፋ አባል ማኅበራት በፊፋ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ካለመሳተፋቸው ጋር በተያያዘ ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ግልጽ ናቸው” ብሏል።

    "የመጀመሪያው የዓለም ዋነኛው የእግር ኳስ ውድድርን ድርሻ የመሸጡ ሃሳብ እንዲቀር፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ የዓለም ዋንጫን ገጽታ የሚያበላሽ ማንኛውም ዓይነት ሙከራ በድጋሚ ፈጽሞ እንደማይደረግ ማስተማመኛ ማግኘት ነው” ያለው ማኅበሩ፤ ነገር ግን እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች “አልተሟሉም” ብሏል።

    የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ላይ እምነት እንደሌለው በመግለጽ የፊፋን አዲስ ዕቅድ ግልጽነት የጎደለውና ደካማ በማለት አጣጥሎታል።

    ዩኤፋ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ "በጂያኒ ኢንፋንቲኖ ፕሬዝዳንትነት ላይ እምነት እንደሌለው እና ይህ አቋሙም አልተቀየረም” በማለት በያዘው አቋም መጽናቱን ገልጿል።

  2. ሁቲዎች በየመን መንግሥት ኃይሎች ካምፕ ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካቶችን መግደላቸው ተዘገበ

    ሁቲ ታጣቂዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty

    የሁቲ ታጣቂዎች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው የየመን መንግሥት ቁጥጥር ሥር በሚገኝ ካምፕ ላይ ፈጸሙት በተባለ የሮኬት እና የድሮን ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ።

    የየመን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ጥቃቱ የተፈጸመው ማሪብ እና ሃድራማውት በተባሉት ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ የታጣቂዎች የመጠለያ ካምፕ ላይ ነው።

    የየመን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ኃይሎች ካምፖች ላይ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ በንብረትም ላይ ከባድ ውድመት መድረሱ ተነግሯል።

    ለዓመታት በሁቲ ኃይሎች እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው የየመን መንግሥት መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለችው አገሪቱ በሁለቱ ወገኖች ቁጥጥር ስር ትገኛለች።

    ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ጋብ ብሎ የቆየ ቢሆንም አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

    ካለፈው ሐምሌ ወር ወዲህ በሁቲዎች እና በየመን መንግሥት መካከል የሚደረገው ግጭት በመባባሱ በሁለቱም ወገን የተሰለፉ በርካታ ተዋጊዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    የኢራን ወዳጅ የሆኑት ሁቲዎች ከአውሮፓውያኑ 2014 ወዲህ ዋና ከተማዋ ሰነዓን እና በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኙ ሌሎች የአገሪቱን ክፍሎች ተቆጣጥረው ይገኛሉ።

    መቀመጫውን አንደን ያደረገው የየመን መንግሥት የሳዑዲ አረቢያ ድጋፍ ያለው ሲሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅናንም አግኝቷል።

    ነገር ግን ሁቲዎች ከየመን መንግሥት በበለጠ በቀጣናው ከፍተኛ ተጽእኖ ያላቸው ሲሆን፣ ከኢራን በሚያገኙት ድጋፍ በቀይ ባሕር ላይ በሚተላለፉ መርከቦች እንዲሁም በሳዑዲ ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን በመፈጸም ይታወቃሉ።

  3. ዩክሬን በሩሲያ ላይ በፈፀመችው የድሮን ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ 15 መቁሰላቸው ተገለፀ

    የአደጋ ጊዜ ሠተራኞች በፈራረሰ ቤት ውስጥ

    የፎቶው ባለመብት, State Emergency Service Of Ukraine

    የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ እና ዩክሬን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ በፈፀሙት ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል

    ዩክሬን ምሽቱን በሩሲያ የተለያዩ ከተሞች ላይ በፈፀመችው ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ 15 መቁሰላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    ጥቃቱ የተፈፀመው በብያንስክ፣ ኒዢኒይ ኖቭጎርድ፣ እና ኩርስክ ከተሞች ውስጥ ሲሆን ከተጎዱት መካከል አንድ ሕፃን ይገኝበታል።

    የብርያንስክ ከተማ ተወካይ አስተዳዳሪ ይጎር ኮቫልቹክ እየተጓዘ ባለ ተሽከርካሪ ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት አሽከርካሪው መገደሉን ገልጸዋል።

    ሌላ ግለሰብም በኖቮዝይብኮቭ ከተማ መገደሉ የተዘገበ ሲሆን፣ ሌሎች አምስት ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

    በሌላ በኩል የሩሲያ አምስተኛ ትልቅ ከተማ የሆነችው የኒዢኒይ ኖቭጎሮድ አስተዳዳሪ ግሌብ ኒኪቲን፣ ድሮኑ የመገናኛ መስመሩ እክል ከገጠመው በኋላ ዛፍ ላይ በመውደቁ አንድ ሕፃንን ጨምሮ አራት ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጸዋል።

    በአቅራቢያው ባለ ቦታ እሳት መነሳቱን የገለፁት ኒኪቲን፣ የደረሰባቸው ጉዳት “ለሕይወታቸው የሚያሳጋ እንዳልሆነ” ተናግረዋል።

    በሩሲያ ኩርስክ ከተማም አንድ ግለሰብ እንደተገደለ የአካባቢው አስተዳዳሪ ተናግረዋል። በዚህ ጥቃት ስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እና የሦስቱ ከባድ ጉዳት መሆኑን አስተዳዳሪው አሌክሳንደር ኪንሽቴን ገልጸዋል።

    የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጦሩ በረዥም ርቀት ጥቃት ሁለት የሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያን መምታቱን ገልጸዋል።

    "በባሽኮርቶስታን እና ያሮስላቪል የሚገኙ የነዳጅ ማጣሪያዎች ተመትተዋል" ብለዋል ዘሌንስኪ።

    የያሮስላቪል ሰማይም በጥቁር ጭስ ተሸፍኖ ታይቷል።

    የአካባቢው አስተዳዳሪ የተፈፀመውን ጥቃት “በጠላት ድሮኖች የተፈፀመ ሰፊ ጥቃት” ሲሉ የገለፁት ሲሆን 93 ድሮኖች ተመትተው መውደቃቸውን እና በስብርባሪያቸው የነዳጅ ማከማቻ ታንከሮች መመታታቸውን ተናግረዋል።

    የሩሲያ ጦርም በበርካታ አካባቢዎች 605 የዩክሬን ድሮኖችን ማክሸፉን ገልጿል።

    ዩክሬን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የሩሲያ መሠረተ ልማት ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን እየፈፀመች ሲሆን ሩሲያም ምላሽ እየሰጠች ነው።

    የዩክሬን ባለሥልጣናት በሩሲያ የድሮን ጥቃት ስድስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

  4. ትራምፕ አሜሪካ የተተኳሾች እጥረት እንደገጠማት መረጃ ያወጡት ከባድ እስር ይጠብቃቸዋል ሲሉ ዛቱ

    ተወንጫፊ ተተኳሾችን የሚያንቀሳቅሱ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ እና የተተኳሽ ክምችቷ ተመናምኗል መባሉን ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተባብለው ይህንን በተመለከተ የሐሰት መረጃ የሚያሠራጩት ከባድ እስር ይጠብቃቸዋል ሲሉ ዛቱ።

    ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ የመሳሪያ ክምችት ቀንሷል በሚል የቀረቡ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን አጣጥለው “በተለይ የተወሰኑ ዓይነት ጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሾች በከፍተኛ መጠን” እንዳሏቸው ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    "በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያላቸው ተተኳሾች እየተመረቱ እንደ አስፈላጊነታቸው ወደ አሜሪካ ይጓጓዛሉ። የመከላከያ ተቋማት በአሜሪካ ታሪክ ግዙፍ የሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፋብሪካዎች እና ማምረቻዎችን እየገነቡ ነው” ብለዋል ትራምፕ።

    የተተኳሾችን እጥረት በተመለከተ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የመከላከያ ሚኒስትሩን ፔት ሄግሴትን ባለፈው አርብ በተካሄደው የካቢኔ ስብሰባቸው ላይ መጠየቃቸውን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዘግቦ ነበር።

    ጋዜጣው ስማቸው ያልተገለጹ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በስብሰባው ላይ ለመከላከያ ሚኒስትሩ የተተኳሾች እጥረቱ “ተፈትቷል” ብለው አስበው እንደነበር እንደነገሯቸው ዘግቧል።

    በዘገባው የተቆጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ “እንዲህ ያለውን በአገር ክህደትነት የሚቆጠር መረጃን አሾልከው የሰጡ ተከስሰው ከፍተኛ የእስር ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ሲሉም ዝተዋል።

    የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎች እና የአየር መከላከያ ሚሳዔሎች እጥረት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ በሚከተሉት ፖሊሲ ላይ ተጽእኖ እንደፈጠረ እና የአሜሪካ ሠራዊት ወደ 80 በመቶ የሚጠጋውን ፀረ ሚሳዔል ክምችቱን ጥቅም ላይ እንዳዋለ ሲኤንኤን ዘግቧል።

    ዋሽንግተን ፖስት በተጨማሪም የተተኳሽ እጥረቱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ሊፈጽሙ ሲዝቱበት የነበረውን “በጣም ከባድ” ጥቃት ለመሰረዝ እንዳስገደዳቸው ዘግቧል።

    የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቬት ፕሬዝዳንቱ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ተጨቃጭቀዋል መባሉን “ሐሰተኛ ዜና” በማለት ይህ እንዳልሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር - ፔንታገን ቃል አቀባይ ሾን ፓርኔል የጦር መሳሪያ እጥረት መከሰቱን በተመለከተ የቀረቡትን ዘገባዎች “ሙሉ ለሙሉ የፈጠራ” ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።

  5. ዩክሬን ሁለት የሩሲያ ነዳጅ ማጣሪያዎች ላይ ጥቃት ፈጸመች

    ጥቃት ደረሰበት ነዳጅ ማጣሪያ

    የፎቶው ባለመብት, Social media

    የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የአገሪቱ ጦር በፈጸመው ጥቃት በሩሲያ ትልቁ የሆነውን የነዳጅ መሠረተ ልማት ጨምሮ ሁለት ማጣሪያዎች መመታታቸውን ተናገሩ።

    በዚህ ጥቃት የተመቱት በያሮስላቭል ከተማ የሚገኘውን የስላቭኔፍት ያኖስ ማጣሪያ እና በባሽኮርቶስታን ከተማ ያለው ባሽኔፍት ኖቮይል ማጣሪያ መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል።

    በያሮስላቭል የሚገኘው ነዳጅ ማጣሪያ በዓመት 15 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማጣራት አቅም ያለው ግዙፍ መሠረተ ልማት እንደሆነ ተገልጿል። ስፍራው የሚገኘው ከዩክሬን ድንበር 280 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው።

    በጥቃቱ በተፈጸመበት ያሮስላቭል ከተማ ከፍተኛ ጭስ ታይቷል።

    የያሮስላቭል ክልል ዋና አስተዳዳሪ “በጠላት ድሮን የተፈጸመ ትልቁ ጥቃት” ሲሉ የገለጹት ሲሆን 93 ድሮኖች እንዲወድሙ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ ስብርባሪዎች የነዳጅ ማጠራቀሚያን መምታታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል።

    በከተማው በደረሰው ጥቃት አራት ሰዎች እንደተጎዱም ተገልጿል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እሳቱን ለማጥፋት እየተረባረቡ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ሌላ ስጋት አለመኖሩን ተናግረዋል።

    እንደ የሩሲያ ጦር ገለጻ፤ ዩክሬን ያሮስላቭልን ጨምሮ በመላው አገሪቱ የላከቻቸው 605 ድሮኖች እንዲጠለፉ እና እንዲወድሙ ተደርጓል።

    ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ዩክሬን ነዳጅ ማጣሪያዎች እና መጋዘኖችን ጨምሮ የተለያዩ የሩሲያ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ስታደርስ ቆይታለች።

  6. እስራኤል ከሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃት ፈጸመች

    ለሊባኖስ ተራራማ ስፍራ ላይ ጭስ ወደላይ ሲወጣ ይታያል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል 12 ሰዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር አስታወቀ።

    እስራኤል ይህንን ጥቃት ያደረሰችው በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ፈጽሞታል ላለችው “ግልጽ የተኩስ አቁም ጥሰት” ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ገልጻለች።

    ሞት እና ጉዳት ያጋጠመው በቲብኒን ከተማ ውስጥ የጸሎት ስፍራ ጣርያ በመመታቱ እንደሆነ የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የእስራኤል ጦር ከአንድ ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ትዕዛዝ ባወጣባት በምዕራባዊቷ ማንሱሪ ከተማም ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

    የእስራኤል ጦር የአረብኛ ቋንቋ ቃል አቀባይ ረቡዕ ዕለት ነዋሪዎች በአካባቢው “የኃይል እርምጃ” ከመወሰዱ በፊት ለቅቀው እንዲወጡ አዝዘው ነበር።

    ከ30 ደቂቃ በኋላ ደግሞ ዋናው ቃል አቀባይ የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ “ዒላማ ተኮር ጥቃቶችን” ማድረስ መጀመሩን አስታውቀዋል።

    የእስራኤል ጦር ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደጣሰ ከመግለጽ ውጪ ዝርዝር መረጃ አላቀረበም።

    እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙት የእስራኤል እና ሊባኖስ ባለሥልጣናት በአሜሪካ አደራዳሪነት የተደረሰውን ተኩስ አቁም ለማጽናት ያለመ ንግግር ሮም ውስጥ እያካሄዱ ባለበት ወቅት ነው። ሄዝቦላህ ክስተቶቹን በተመለከተ አስተያየት አልሰጠም።

    ሁለቱ አገራት፣ ሄዝቦላህ ትጥቁን እንዲፈታ፣ በምላሹ ደግሞ እስራኤል ወርራ ከያያዘቻቸው የደቡባዊ ሊባኖስ ግዛቶች እንድትወጣ የሚያደርግ የስምምነት ማዕቀፍ ሰኔ ላይ ተፈራርመው ነበር።

    የእስራኤል መውጣት ከትጥቅ መፍታት ጋር መያያዙ “ሁሉምን ቀይ መስመሮች” የጣሰ እንደሆነ የገለጸው ሄዝቦላህ፣ ስምምነቱን ውድቅ አድርጎታል።

  7. ኢራን በሆርሙዝ ጉዳይ ከኦማን ጋር የምታደርገው ድርድር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መሆኑን አስታወቀች

    መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረገውን የመርከቦች ጉዞ በተመለከተ ከኦማን ጋር ስምምነት ላይ መድረሷን ገለጸች።

    የቴህራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋኢ "የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ" እንደሆነ ስለገለጹት ስምምነት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ይሁን እንጂ ከኦማን የተደረሰው ስምምነት በወሽመጡ የሚደረግ ጉዞ ደኅንነቱ የተጠበቀ ለመሆኑ ዋስትና እንዳልሆነ አንስተዋል። ቃል አቀባዩ ይህንን ያሉት አሜሪካ የኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ የወሽመጡ የደኅነት ሁኔታን ተፅዕኖ ውስጥ እንደከተተው በመጥቀስ ነው።

    አሜሪካ እና ኦማን የስምምነት ዕቅዱን በተመለከተ አስተያየት አልሰጡም።

    ቴህራን በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች ላይ እጥለዋለሁ የምትለው ክፍያ ኢራን እና አሜሪካን ካላስማሙ ጉዳዮች አንዱ ነው።

    ኢራን በወሳኙ የባሕር መስመር የሚያልፉ መርከቦች ከሚይዙት ጭነት ዋጋ ውስጥ ከ5% እስከ 7% ክፍያ መሰብሰብ እንደምትፈልግ አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ኦማን ከኢራን ጋር በምታደርገው ንግግር የክፍያ መጠኑ 3% ገደማ እንዲሆን ጠይቃለች። የአሜሪካ ፍላጎት ደግሞ ምንም አይነት ክፍያ እንዳይኖር ነው።

    የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ የቀረበው ስምምነት ቴህራን ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚገቡ መርከቦች ጉዞ ላይ ቁጥጥር እንዲኖራት ያደርጋል።

    የካቲት ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ጥቃት ከከፈቱበት ጊዜ አንስቶ ቴህራን ከዓለም አቀፉ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ውስጥ 20 በመቶ ገደማው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች።

    ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወሽመጡ “በቅርቡ” የማይከፈት ከሆነ ኢራን “እጅግ በከባዱ እንደምትመታ” አስጠንቅቀዋል።

    ትራምት ማስጠንቀቂያውን የሰጡት፣ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከኢራን ጋር የሚደረጉ ንግግሮች በዚህ ሳምንት መጨረሻ በሆርሙዝ የሚደረግ ጉዞን በድጋሚ ለማስጀመር በሚያስችል ደረጃ ማሻሻል እንዳሳዩ ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ኢራን ግን ከአሜሪካ ጋር እየተነጋገረች እንዳልሆነ እና ለመደራደርም እቅድ እንደሌላት በተደጋጋሚ ገልጻለች።

    ሁለቱ አገራት እና አሸማጋዮች በሚያደርጓቸው ውይይቶች ውስጥ አንዱ ቁልፍ ጉዳይ የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት ነው።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፣ በሆርሙዝ የሚያልፉ መርከቦች የሚከተሉትን ትክክለኛ “መስመር” በተመለከተ ከኦማን ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

    “በአሜሪካ በኩል ሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነቱ ያልተጠበቀ የሚያደርጉት ምክንያቶች አሁንም አሉ” ያሉትን ቃል አቀባዩ የዋሽንግተንን ”የባሕር እገዳ እንዲሁም በኢራን እና በጥቅሞቿ የሚቃጡት ሌሎች ተንኳሽ እና ዛቻ የተሞላባቸው እርምጃዎችን” በዋነኝነት ጠቅሰዋል።

    ስምምነት የተደረሰበት የባሕር መስመር ጊዜያዊ እና ከሁለት እስከ አራት ወራት ክፍት ሆኖ ሊቆይ የሚችል መሆኑን የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ ‘ኢርና’ ለተሰኘው ለኢራን መንግሥት ዜና ወኪል ተናግረዋል።

  8. ኢራን በአራት ወራት ውስጥ ቢያንስ 56 ሰዎችን በሞት ቀጣች

    የኢራን ተቃዋሚዎች በምሽት

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ባለሥልጣናት በርካታ ተቃዋሚዎችን በሞት ቀጥተዋል

    በኢራን ውስጥ ከመጋቢት ወር ወዲህ ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ ክስ የቀረበባቸው ቢያንስ 56 ሰዎች በሞት መቀጣታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

    ኮሚሽነሩ ቮልከር ተርክ ባወጡት ይፋዊ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው በሞት ከተቀጡት መካከል 27ቱ በጥር ወር ላይ በመላዋ ኢራን ተቀስቅሶ በርካታ ሰዎች ከተገደሉበት ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው።

    የመንግሥታቱ ድርጅት የመብቶች ኮሚሽን በመግለጫው ላይ ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር የገባችበት ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የሚተላለፉት የሞት ቅጣት ውሳኔዎች እና ግድያዎች መጠናቸው ጨምሯል ብሏል።

    ኮሚሽነር ተርክ ጨምረውም የኢራን ባለሥልጣናት የሞት ቅጣት ፍርድን እንዲያቆሙ እና በሞት መቅጣት እስከወዲያኛው እንዲያበቃ ጠይቀዋል።

    ነገር ግን የኢራን የፍትህ ተቋማት የበላይ ባለሥልጣን በተቃውሞዎች ላይ በተሳተፉ እና ከአሜሪካ ጋር ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ በተያዙ ተከሳሾች ላይ የሞት ቅጣት እንዲተላለፍ እና ፍርዱም “በአስቸኳይ” እንዲሁም “ያለምህረት” እንዲፈጸም በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።

  9. ሜክሲኳዊው ቲክቶከር በቀጥታ ሥርጭት ላይ ሳለ በጥይት ተገደለ

    ሴዛር ጋስታሊየም

    የፎቶው ባለመብት, Instagram/César Gastélum

    ሜክሲኳዊው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴዛር ጋስታሊየም በቲክ ቶክ የቀጥታ ሥርጭት እያስተላለፈ ሳለ በተተኮሰበት ጥይት ተገደለ።

    ማክሰኞ ዕለት በሰሜን ሜክሲኮ፣ ትሪስ ሪዮስ ስለሚገኝ የፈጣን ምግብ ሬስቶራንት ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን አስተያየት እየሰጠ ባለበት ወቅት ነው የተገደለው።

    ቀረጻውን እያካሄደ ሳለ ሞተር ሳይክል እየነዱ የነበሩ ሁለት ወንዶች በቅርብ ርቀት ሆነው ተኩሰውበታል።

    ቲክቶክ ላይ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት። በብዛት የሚያስተላልፈው ቀልድ አዘል ይዘቶችን ነበር።

    በሜክሲኮ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሲገደል የመጀመሪያው አይደለም።

    አምና የ23 ዓመቷ ቫለሪያ ማርከዝ በውበት ሳሎን ውስጥ ሆና በቀጥታ ቲክቶክ እያሠራጨች ሳለ በተተኮሰባት ጥይት ተገድላለች።

    ሴዛር ጋስታሊየም ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ እየቀረጹ ሳለ ምግብ አመላላሽ ሠራተኞች የሚለብሱት ብርቱካናማ ቀለም ያለው ልብስ አድርገው ነበር።

    የሜክሲኮ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ፤ በዚህ ልብስ ምክንያት ፖሊሶች ምግብ አመላላሽ ሠራተኛ የተገደለ መስሏቸው ነበር።

    ፖሊሶች የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ ይገኛሉ። ሁለቱ በሞተር ሳይክል ላይ የነበሩ ግለሰቦች ወዲያውኑ ከአካባቢው የሸሹ ሲሆን፤ ፖሊስ ከግድያው ጋር በተያያዘ እስካሁን ማንንም በቁጥጥር ሥር አላዋለም።

  10. የየመን ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ የሳዑዲ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በባሌስቲክ ሚሳዔል መምታታቸውን ገለጹ

    የተወነጨፈ ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የየመኑ ሁቲ ረቡዕ ዕለት በሰሜናዊ ቀይ ባሕር ያንቡ የባህር ዳርቻ የሳዑዲ የነዳጅ ማጓጓዣ መርከብን በበርካታ ባሌስቲክ ሚሳዔሎች መምታቱን አስታወቀ።

    የቡድኑ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባወጡት መግለጫ ሚሳዔሎቹ መርከቧን "በትክክል" መምታታቸውን ገልጸዋል።

    ሳሪ እንደገለጹት ጥቃቱ ቡድኑ በሳዑዲ አረቢያ ላይ በጣለው የባህር ላይ እገዳ ስልት አካል ነው።

    ቃል አቀባዩ ጨምረው እንዳስታወቁት እግዱ እአአ ከሐምሌ 22 ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቡድኑ ዒላማ የተደረጉ እና ጥቃት የተፈጸመባቸው የሳዑዲ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ቁጥር ወደ ስምንት ከፍ ብሏል።

    ሳሪ በተጨማሪም 29 የሳዑዲ የነዳጅ ማጓጓዣ መርከቦች በቀይ ባህር እና በአረብ ባህር እንዳያልፉ መከልከላቸውን ወይም ወደኋላ እንዲመለሱ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

    ቡድኑ በባብ አል ማንዳብ የባህር ወሽመጥ ላይ የጣለውን “እግድ” በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ካደረገ በኋላ ሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማጓጓዣ መርከቦቿን ወደ ሰሜናዊው የቀይ ባህር ክፍል ማዞሯን ገልጸዋል።

    ሳሬ የባሕር መስመሮቹን ለመዝጋት “ውጤቱ ምንም ይሁን ምን” በሰሜን ቀይ ባህር በሳዑዲ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዝተዋል።

    የሳዑዲ ባለሥልጣናት ደረሰ ስለተባለው ጥቃት ያሉት ነገር የለም።

  11. አሜሪካ በኢራን ጦርነት ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳዔሎቿን ተጠቅማ ጨርሳለች ተባለ

    የአሜሪካ ወታደር መሣሪያ እየጫነ

    የፎቶው ባለመብት, Centcom/Reuters

    አሜሪካ ከኢራን ጋር በምታደርገው ጦርነት ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ እና ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ ሚሳዔሎቿን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ መጠቀሟን ሁለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮችን ጠቅሶ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘገበ።

    ምንጮቹ አክለውም አሜሪካ ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ እና ዘመናዊ ምድር ለምድር የሚወነጨፉ የሮኬት ሚሳዔሎቿን ተጠቅማለች ብለዋል።

    አሜሪካ ያሏትን የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎቿን በሙሉ ተጠቅማ ማጠናቀቋን ቀድሞ የዘገበው ሮይተርስ የዜና ወኪል ነው።

    ሲቢኤስ ከዚህ ቀደም የረዥም ርቀት ሚሳዔሎች እና ከምድር ወደ ኤር ተምዘግዝገው ዒላማቸውን በመለየት የሚመቱ መሣሪያዎች ክምችት በመቀነሱ የትራምፕ አስተዳደር ከኢራን ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለማቆም መገደዱን ዘግቦ ነበር።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት በመጋዘን ውስጥ የሚገኙት ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ እና ዘመናዊ ምድር ለምድር የሚወነጨፉ የሮኬት ሚሳዔሎች ቁጥር ውስን መሆኑን ገልፀዋል።

    ባለሥልጣናቱ አክለውም ፓትሮይት እና ተርሚናል ሃይ አልቲትዩድ ኤሪያ ዲፌንስ (ቲኤችኤኤዲ) የሚባሉት መሳሪያዎች በፍጥነት አምርቶ መተካት አንደማይቻል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    ሐምሌ ወር ላይ አንድ የምርምር ቡድን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አሜሪካ 2330 ፓትሮይት ሚሳዔሎች የነበራት መሆን ገልጾ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ግን ከ827 እስከ 759 መካከል ብቻ ቀርተዋታል ብሏል።

    ይኸው ጥናት ከጦርነቱ በፊት 452 ቲኤችኤኤዲ የተባለው መሣሪያ እንደነበራት አስታውሶ በሐምሌ ወር መጨረሻ ግን ከ278 እስከ 234 ባለው ውስጥ ብቻ እንደቀራት መዝግቧል።

    ሌላ በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት አሜሪካ ያሏትን የመሣሪያ ክምችቶች ከጦርነቱ በፊተ ወደነበረው ለመመለስ እስከ 2029 አጋማሽ ድረስ እንደሚወስድባት ይፋ አድርጓል።

    የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሼን ፓርኔል ለሲቢኤስ ኒውስ በሰጡት ምላሽ “የአሜሪካ ጦር በዓለም ላይ ከፍተኛ አቅም ካላቸው መካከል ነወ። ፕሬዚዳንቱ ባዘዙ ሰዓት የሚሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም አለው” ብለዋል።

    አክለውም “ውጤታማ ዘመቻዎችን አድርገናል” በማለት “ሕዝባችንን እና ፍላጎታችንን ለመከላከል የሚያስችል በቂ መሣሪያ ታጥቀናል” ብለዋል።

    ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ፒት ሄግሴት የጦሩ የመሣሪያ ክምችት ቀንሷል የሚለውን አስተያየት ውድቅ አድርገው ነበር።

  12. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በቅርቡ ካልከፈተች “በጣም ከባድ ጥቃት” ይደርስባታል ሲሉ ትራምፕ አስጠነቀቁ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ "በቅርቡ" ይከፈታል አለበለዚያ ኢራን "በጣም ከባድ ጥቃት ይደርስባታል" ሲሉ ዛቱ።

    በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት ሊፈረም ይችላል የሚለው ተስፋ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቅናሽ አሳይቷል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ ስኮት ቤሴንት መርከቦች ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በወሽመጡ በኩል ያለ ምንም ችግር ማለፍ እንዲችሉ የሚያደርግ ውይይት መካሄዱን እና አንዳንድ ለውጦች መታየታቸውን ከገለጹ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ለፎክስ ኒውስ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል።

    የዓለም ነዳጅ አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚችል ዜና ከተሰማ በኋላ የአንድ በርሜል የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ5 በመቶ ገደማ ቀንሶ 80 ዶላር (60 ፓውንድ) ተሽጧል።

    ነገር ግን ባለፉት ወራት የተደረጉት ውይይቶች ግጭቱን ለማርገብ አለመቻላቸው የነዳጅ ገበያው እንዲዋዥቅ አድርጎታል፣ በዚህም ምክንያት አሽከርካሪዎች በነዳጅ ዋጋ መጨመር ተጎድተዋል።

    ትራምፕ ትናንት በካሊፎርኒያ ጉብኝት እያደረጉ በነበረበት ወቅት "በጣም ጥሩ ውይይት እያደረግን ነው" ሲሉ ኢራን ለወራት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) "በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ደቡባዊ ክፍል ባለው ዓለም አቀፍ የውሃ መስመር በኩል ለማለፍ ለሚፈልጉ የንግድ መርከቦች ሁሉ ነፃ እና ክፍት ነው" ብሏል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢራን እና ኦማን ጋር ተጨማሪ መርከቦችን በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ስለማሳለፍ የሚደረጉት ውይይቶች ለውጥ መታየት ጀምረዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

    ማርኮ ሩቢዮ ለጋዜጠኞች “በእነዚያ ውይይቶች ላይ መሻሻሎች ታይቷል፤ ግን እስካሁን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረስንም። ይህ በቅርቡ እንደሚከናወን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    ቤሴንት በበኩላቸው የሆርሙዝን የባሕር ወሽመጥ እንደገና ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ማክሰኞ ወይም ረቡዕ ሊደረስ ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል።

    "ዛሬ [ማክሰኞ] ወይም ነገ [ረቡዕ] ወሽመጡን ለመክፈት እና ግጭቱን አርግቦ ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመሸጋገር ስምምነት ላይ ልንደርስ እንችላለን" ሲሉ ለሲኤንቢሲ ተናግረዋል።

    ኢራን በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ቀረጥ እንድታስከፍል ይፈቀድ እንደሆን ተጠይቀው "የመንቀሳቀስ ነፃነት ይሆናል" ሲሉ መልሰዋል።

    የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ቢገልጹም፣ሊፈረም የሚችለው ስምምነት ምን ሊመስል እንደሚችል ዝርዝር መረጃ አልወጣም።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር እንዳልተቀመጠች እንዲሁም ምንም ዓይነት ዕቅድ እንደሌላት ገልጻ በምትኩ ከኦማን ጋር እየተነጋገረች መሆኑን አስታውቃለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል ለሚያልፉ መርከቦች አዲስ አሰራር መዘርጋትን በተመለከተ ከኦማን ጋር የተደረጉት ውይይቶች አዎንታዊ ነበሩ ብለዋል።

    በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል ቁልፍ አሸማጋይ የሆነችው ኳታር ከሌሎች አደራዳሪዎች ጋር በመሆን ለጦርነቱ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጻለች። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ውይይት እንዳልታቀደች አስታውቃለች።

    ግጭቱ እየገፋ ሲሄድ አሜሪካ ዒላማውን ለይቶ የሚመቱ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎቿን ክምችት በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ተጠቅማለች ሲሉ ለጉዳዩ ቀጥተኛ ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ የዜና አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚደረገው ድርድር ማዕከላዊ ነጥብ ነው።

    ግጭቱ በየካቲት ወር መጨረሻ ከመጀመሩ በፊት በወሽመጡ በኩል አንድ አምስተኛ የሚሆነውን የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦቶችን ይጓጓዙ ነበር።

  13. የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ከኢራን ጋር ረቡዕ ሊፈረም ይችላል ተባለ

    የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ማክሰኞ ወይንም ረቡዕ ዕለት ሊፈራረሙ እንደሚችሉ የገንዘብ ሚኒሲትሩ ስኮት ቤሴንት አስታወቁ።

    ቤሴንት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ ምልልስ ወቅት ከስምምነት ላይ ከተደረሰ የንግድ መርከቦች በነጻነት መንቀሳቀስ ይችላሉ ብለዋል።

    የገንዘብ ሚኒስትሩ ለሲኤንቢኤስ እንደተናገሩት “ከኢራናውያን ጋር እየተነጋገርን ነው፤ ወሽመጡን ለመክፈት እና ግጭቱን ለመቀነስ ዛሬ ወይንም ነገ ከስምምነት ላይ የመድረስ ዕድል አለን” ብለዋል።

    ኢራን በወሽመጡ ከሚያልፉ መርከቦች ቀረጥ መሰብሰብ ይፈቀድላት እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱ “በነጻነት መንቀሳቀስ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

    ቤሴንት በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ ቆመው የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ማለፍ ከቻሉ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በፍጥነት እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

    "ጉዳዩ የኤነርጂ ብቻ አይደለም፤ ማዳበሪያን፣ የተጣሩ ምርቶችን እና የተለያዩ የኢንዱስትሪ ጋዞችንም ያካትታል" ብለዋል።

    "የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ሲቀንስ ግዙፍ የተረጋጋ የንግድ እንቅስቃሴ ልናይ እንችላለን።"

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ሆርሙዝን እንደገና ለመክፈት የሚያስችል ድርድር እንዲኖር በማሰብ በኢራን ላይ ሊያደርጉት የነበረውን ከፍተኛ ጥቃት ሰርዘዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደም ግጭቱን ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት እንደሚኖር በተደጋጋሚ ቢጠቁሙም፣ ከቴህራን ጋር ያለው ውጊያ ግን እንደገና እየተባባሰ መምጣቱ ይታወሳል።

    አሜሪካ እና ኢራን ሰኔ 10 2018 ዓ.ም. የሆርሙዝ ወሽመጥን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ነበር።

    ስምምነቱ ከመፍረሱ በፊት የተወሰኑ የንግድ መርከቦች መተላለፍ ችለው ነበር።

    በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደው ጦርነት ዳግምበማገርሸቱ በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ተስተጓጉለዋል።

  14. ኳታር በኢራን እና አሜሪካ መካከል የሚደረገው ንግግር ለውጥ ማሳየቱን ገለጸች

    ኢራን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኳታር አደራዳሪዎች በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት ውጤት እያገኙ መሆናቸውን አስታወቀች።

    ኳታር ይህንን ካለች በኋላ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በፍጥነት ቅናሽ አሳይቷል።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት ከቴህራን ጋር ንግግር መጀመሩን ተናግረው ኢራን ከእውነተኛ ስምምነት ላይ ለመድረስ ይህ “የመጨረሻ ዕድሏ” ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት ግን ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እየተካሄደ አለመሆኑን በመናገር ያስተባብላሉ።

    ቴህራን ከኦማን ጋር በሆርሙዝ ወሽመጥን በሚመለከት እየተነጋገረች መሆኗን በመግለጽ በዚህ ሳምንት ሌላ ምንም ዓይነት ውይይት እንደሌለ ጠቅሳለች።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት በኦቫል ኦፊስ ለተገኙ ጋዜጠኞች “ድርድሩ እየተካሄደ ነው” ብለው ንግግሩ የተጀመረው በኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ኳታር ጥያቄ መሠረት መሆኑን አስታውቀዋል።

    “ስምምነቱን ለመፈረም ይህ [ለኢራን] የመጨረሻ ዕድል ነው" ብለዋል።

    የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጄድ አል አንሳሪ ዲፕሎማቶች “በጣም ጥሩ ደረጃ” ላይ ደርሰዋል ብለዋል።

    አንሳሪ ማክሰኞ ዕለት ኳታር፣ ፓኪስታን እና ኦማንን ጨምሮ አደራዳሪዎች በዋሺንግተን እና ቴህራን መካከል ረቂቅ የሰላም ዕቅድ ለማለዋወጥ እየሠሩ መሆኑን አብራርተዋል።

    አንድ ከፍተኛ የፓኪስታን ባለሥልጣን “ከጀርባ ብዙ ነገር እየሆነ ነው. . . ሁለቱም ወገን እያነጋገርን ነው። አሁን ዋነኛ ግባችን ሁለቱም አካላት ቢያንስ ንግግር እንዲጀምሩ ማድረግ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት ከቴህራን ጋር ንግግር እንደተጀመረ በመጥቀስ ለመፈጸም አስበውት የነበረውን “መጠነ ሰፊ ጥቃት” መሰረዛቸውን ተናግረዋል።

  15. የኢራን ፕሬዝዳንት ከሥልጣን ስለመልቀቃቸው የተሰራጨውን ዘገባ አስተባበሉ

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ከአሜሪካ ጋር እየተባባሰ ባለው ወታደራዊ ውጥረት መካከል የሥልጣን መልቀቂያ አቀረቡ ተብሎ የተሰራጨውን ዘገባ አስተባበሉ።

    ፕሬዝዳንቱ በቴሌቭዥን በተላለፈ ማብራሪያቸው "ከኃላፊነት የምለቅ ከሆነ ለሕዝብ አሳውቃለሁ። ከሥልጣን አለቅቅም ትግሉን እቀጥላለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ​ ከከፍተኛው መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ እና ከጦር ኃይሎች ጋር አለመግባባት ተፈጠረ የሚሉትን ዘገባዎች አስተባብለው፣ “በሙሉ ስምምነት እና ቅንጅት እየሠራን ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

    ​“ማንኛውም አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን የጦር ኃይሉ ከኻሜኒ ጎን እንደሚቆም ሁሉም ያውቃል” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢራን ተቃዋሚ የመገናኛ ብዙኃን ከዚህ ቀደም ፔዜሽኪያን ለኻሜኒ የሥልጣን መልቀቂያቸውን በተደጋጋሚ አቅርበዋል ሲሉ ዘግበው ነበር።

    ዋሽንግተን እና እስራኤል በቴህራን ላይ የጋራ ጥቃት ካደረሱበት ከየካቲት ወር ጀምሮ ኢራን ከአሜሪካ ጋር በግጭት ውስጥ ትገኛለች።

    ኢራን የአሜሪካ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ባላቸው የባህረ ሰላጤው አገራትን በድሮን እናበሜሳይል በመደብደብ የአፀፋ ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።

    አሜሪካእና ኢራን በሚያዚያ ወር ላይየተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

    ሁሉቱ ሀገራት ጦርነት ለማስቆም እና ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ በፓኪስታን አሸማጋይነት የተዘጋጀ የመግባቢያ ሰነድ በሰኔ ወር ተፈራርመው እንደነበር አይዘነጋም።

    ሆኖም ስምምነቱ ባለፈው ወር የፈረሰ ሲሆን፣ ግጭቱን ለመፍታት ንግግሮች እየተደረጉ ነው በሚሉ ዘገባዎች መካከል የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕየቦንብ ድብደባውን በድንገት ከማቆማቸው በፊት ሁለቱ ሀገራት ለሁለት ሳምንታት ያህል ጥቃት ተለዋውጠዋል።

  16. የየመን ሁቲዎች የሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ፈጽመናል አሉ

    የመን ተጣቂዎች በመኪና ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሁቲ ቃል አቀባይ የሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታወቁ።

    የየመን ታጣቂዎች ማክሰኞ ዕለት በደቡባዊ ሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው በናጅራን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

    የሁቲዎች ወታደራዊው ቃል አቀባይ የሆኑት ያህያ ሳሬ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጥቃቱ ዒላማውን መምታቱን ተናግረዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት እስካሁን ድረስ ሁቲዎች ፈጸምነው ስላሉት ጥቃት ያሉት ነገር የለም።

    የሁቲ ቃል አቀባይ የሳዑዲ ድሮኖች የየመን ግዛቶች በሆኑት ሳዳ እና ሃጃህ አየር ክልል ላይ ጥሰው በመግባታቸው የአጸፋ ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

    ሳሬ ወደፊት የመንን አየር ክልል ጥሶ መገኘት “ምላሽ ሳይሰጠው እና ቅጣት ሳይቀበሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።

  17. በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የተጋረጠው ስጋት መባባሱን ተንታኞች ተናገሩ

    መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በአሁኑ ወቅት የተጋረጠቸባው ስጋት የኢራን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ከታዩት የከፋው መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ።

    ባለሙያዎቹ ይህን ያሉት ሌላኛው ወሳኝ የቀጣናው የባሕር መስመር በሆነው ቀይ ባሕር ላይ ድንገተኛ ጥቃቶች ከተፈፀሙ በኋላ ነው።

    ቀይ ባሕር ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ከዘጋች በኋላ አንዳንድ መርከቦች ሲጠቀሙበት የነበረ አማራጭ መሥመር ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደገና ለመክፈት ከኢራን ጋር ንግግር እየተደረገ ነው ቢሉም ኢራን ይህንን አስተባብላለች። ይሁን እንጂ የመስመሩን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከኦማን ጋር እየተነጋገረች እንደሆነ ገልጻለች።

    ኬፕለር በተባለው የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚከታተል ተቋም ተንታኝ የሆኑት ማቲው ራይት ፣ “የድፍድፍ ነዳጅ ንግድ ቀውሱ ከጀመረ ወዲህ እጅግ አስከፊው ጊዜ ላይ ይገኛል” ብለዋል።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ አስንቶ በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

    ቅዳሜ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለፉት መርከቦች ቁጥር 11 ሲሆኑ እሑድ ማለፍ የቻሉት ስምንት መርከቦች ብቻ ናቸው።

    እንደ ኬፕለር ከሆነ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በቀን ከ100 በላይ መርኮቦች ያልፉ ነበር።

    20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ በወሽመጡ በኩል ነበር የሚተላለፈው።

    ሰኔ ወር ላይ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት የመርከቦቹን ቁጥር ከፍ አድርጎት የነበረ ቢሆንም ግጭቱ ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ እንቅስቃሴው እንደገና በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

    በርካታ መርከቦችም በቀላሉ እንዳይለዩ ወሽመጡን በሚያቋርጡበት ጊዜ መልዕክት መቀበያ እና ማስተላለፊያ መሣሪያቸውን (ሲግናላቸውን) ለማጥፋት ተገደዋል።

    ከሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ የጫኑ አንዳንድ መርከቦች አማራጭ በሆነው እንዲሁም ሳዑዲ እና ሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ መካከል በሚገኘው የቀይ ባሕር መስመር አልፈዋል።

    ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የየመን ሁቲ ተዋጊዎች በሳዑዲ መርከቦች ላይ በፈፀሟቸው ድንገተኛ ጥቃቶች ምክንያት ስጋቱ ተባብሷል።

    የሁቲ አማጺያን የሳዑዲ መርከቦች በቀይ ባሕር ላይ እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ መጣሉን ከሁለት ሳምንት በፊት ያስታወቀ ሲሆን የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ትራንስፖርት ተቋም ባለፈው ሳምንት በርካታ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ገልጿል።ተጨማሪ ያንብቡ፦ ኢራንን በመደገፍ በቀይ ባሕር ላይ መርከቦችን እንደሚያጠቁ ያሳወቁት የየመን ሁቲዎች እነማን ናቸው?

  18. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሁኑ ድርድር ኢራን “ ጥሩ ሰነድ መፈረም የምትችልበት የመጨረሻው ዕድል ነው” አሉ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከቴህራን ጋር 'ድርድር ተጀምሯል' በሚል አቋማቸው የጸኑት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሁን የሚደረገው ንግግር ኢራን “ጥሩ ሰነድ መፈረም የምትችልበት የመጨረሻው ዕድል” መሆኑን ተናገሩ።

    ኢራን በበኩሏ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከብ ጉዞን ለማስጀመር የሚያስችል ጊዜያዊ መስመርን በተመለከተ ከኦማን ጋር እየተደራደረች መሆኑን አስታውቃለች።

    ቴህራን ይህንን ያስታወቀችው ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን ጦርነት ለመቋጨት የሚካሄደው ንግግር ሰኞ ዕለት እንደሚጀመር እና ለድርድርሩ ሲባል አገሪቱ ላይ ሊፈጸም የነበረ "ከባድ" ጥቃት እንዲቆም ማድረጋቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።

    ትራምፕ ድርድሩ ላይ የትኛዎቹ አካላት እንደሚሳተፉ በግልጽ አልተናገሩም። ኢራን ግን ከአሜሪካ ጋር እየተደራደረች እንዳልሆነ፣ ለድርድር የመቀመጥም እቅድ እንደሌላት ገልጻለች።

    ኢራን ተሳትፎ እንደሌላት መግለጿ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ያስቆጣ ይመስላል። ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ የኢራን አመራር "ለማመን በማይቻል ደረጃ ቀጣፊ ነው” ሲሉ ዘልፈዋል።

    ቆይቶም በዋይት ሀውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ንግግሩ እየተካሄደ ነው በሚለው አቋማቸው ጸንተው ታይተዋል።

    “እየተነጋገርን ካልሆነ ስትጠይቁኝ ‘እየተነጋገርን አይደለም’ እላለሁ። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት እየተነጋገርን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

    “እየተነጋገርን ያለነውም በኢራን ጥያቄ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና "በርካታ አገራት" ለድጋፍ እንደሚያደርጉ አንስተዋል።

    እነዚህ አገራት ለኢራን “የመጨረሻ ዕድል” መስጠት እንደሚፈልጉ ተናግረዋም። ኢራኖች “ጥሩ ሰነድ መፈረም የሚችሉበት የመጨረሻ ዕድል ይህ ነው" ብለዋል።

    አሜሪካ ኢራን ለመውሰድ ካቀደችው እርምጃ ከመተግበሯ በፊት የቀረበ “የመጨረሻ ዕድል” መሆኑንም አክለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የስምምነቱን “ወሰኖች” በተመለከተ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረው ነበር።

    የሚደረገው ስምምነት በኢራን የተዘጋው እና የነዳጅ ዋጋ እንዲንር ምክንያት የሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ መልሶ እንዲከፈት እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።

    ትናንት ሰኞ ቴህራን ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ ግን አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ንግግር እያደረገች አለመሆኑን ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ በሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ እንዲደረግ የሚያስችል “ጊዜያዊ የባሕር መጓጓዣ መስመር” የሚመሠረትበትን መንገድ በተመለከተ ከኦማን ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል።

    ትራምፕ ድርድር እየተካሄደ መሆኑን በድጋሚ ከተገናሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ መለኪያ የሆነው ብሬንት ዋጋው በ4.5 በመቶ ወርዶ በበርሜል 83.98 ዶላር ተሽጧል።

  19. የአሜሪካ ጦር ኢራንን ለመቅጣት “ያልተለመዱ ሐሳቦች” እንዳሉት ተዘገበ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, AP

    የአሜሪካ ጦር ኢራንን ለመቅጣት እና ጫና ለማሳደር “በፈጠራ የተሞሉ እና ያልተለመዱ” ሐሳቦችን እየተመለከተ እንደሚገኝ ሲኤንኤን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።

    በአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) አመራር የሆኑ የሲኤንኤን ምንጭ እንደጠቆሙት፤ “ኢራን ላይ ጫና ለማሳደር እና ለመቅጣት አዳዲስ መንገዶች እየተመለከትን ነው” የሚል ኢሜል ተልኳል።

    የአሜሪካ ጦር ስትራቴጂውን መለወጥ ስላለበት ሁሉንም ዓይነት መንገዶችን እየተመለከተ መሆኑን ሌላ የሲኤንኤን ምንጭ ጠቅሰዋል።

    የአሜሪካ ጦር ሐሳቦች በኢሜል እንዲላኩለት መጠየቁ የተለመደ አሠራር እንዳልሆነ ወታደራዊ ባለሥልጣን መናገራቸው በዘገባው ተጠቅሷል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ብራድ ኩፐር በበኩላቸው “በፈጠራ የተሞሉ መንገዶች ማሰብ እና መተግበር በጦሩ ታሪክ የተለመደ ነው” ብለዋል።

    “ከፍተኛ የኦፕሬሽን ውጤት ለማግኘት” በየትኛውም ወታደራዊ ማዕረግ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ወታደሮች ሐሳብ እንደሚሰበስቡ ገልጸዋል።

    የሲኤንኤን ምንጭ “በስተመጨረሻ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። ስለዚህም ጫና ማሳደሪያ እና ከዚህ ሁኔታ መውጫ መንገድ ይፈልጋሉ። አንዳንዴ የተለመደው አካሄድ ሲሟጠጥ በፈጠራ የተሞላ አስተሳሰብ ያስፈልጋል” ብለዋል።

  20. የፍርድ ሒደት እየተካሄደ ሳለ የሱዳን ጦር ባደረሰው የድሮን ጥቃት 35 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    የሱዳን ሰንደቅ አላማ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    በሰሜን ሱዳን ዳርፉር ግዛት ባህላዊ የፍርድ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ሳለ የሱዳን ጦር በፈጸመው የድሮን ጥቃት 35 ሰዎች መገደላቸውን የመብት ተሟጋች ተቋም አስታወቀ።

    ትናንት እሑድ ከሰዓት በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የሱዳን የመብት ተሟጋች ተቋም ገልጿል።

    በንጹኃን ላይ የሚፈጸም ጥቃትን የሚከታተለው ‘ዘ ኢመርጀንሲ ሎየርስ ግሩፕ’ እንዳለው የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው ጋህራ አል-ዛዊያ በተባለ መንደር ነው።

    መንደሩ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ነው። ስለተፈጸመው የድሮን ጥቃት የሱዳን ጦር አስተያየት አልሰጠም።

    አርኤስኤፍ አብዛኛውን የዳርፉር አካባቢ ይቆጣጠራል።

    ለሦስት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።

    ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው የዐይን እማኝ “የእሑዱ የፍርድ ሥነ ሥርዓት የማኅበረሰብ መሪዎች በተገኙበት ዛፍ ሥር እየተከናወነ ነበር” ብለዋል።

    አራት የጎሳ መሪዎች እና ሁለት የአርኤስኤፍ ኮማንደሮች በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል እንደሚገኙበት የዐይን እማኙ ገልጸዋል።

    የግል ሚዲያ የሆነው ዳርፉር 24 ድረ ገጽ አንድ ነዋሪን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሁለት ድሮኖች በአካባቢው በርረው “ከአራት ሚሳዔል በላይ” ተኩሰዋል።

    የመብት ተሟጋች ቡድኑ የድሮን ጥቃቱን አውግዞ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።

    ንጹኃን ዜጎችን እና መሠረተ ልማትን ዒላማ ማድረግ “ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጋር የሚጻረር” እንደሆነም ገልጿል።