የኢራን ፓርላማ አሜሪካ እና እስራኤል በሆርሙዝ ወሽመጥ እንዳያልፉ የሚከለክል ረቂቅ ሕግ አቀረበ
የኢራን ፓርላማ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እና በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ላይ ያለውን ቁጥጥር የሚያጠብቅ ረቂቅ ሕግ ላይ ተወያየ።
ረቂቅ ሕጉ ከአሜሪካ፣ እስራኤል እና ቴህራን ጠብ አጫሪ ናቸው ስትል ከምትፈርጃቸው አገራት ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦችን ማገድ እንደሚያካትት ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
ታስኒም የፓርላማ አባል የሆኑትን አባስ ሳሊሚን ጠቅሶ እንደዘገበው የፓርላማው ብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኮሚቴ በወሽመጡ እና በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ ላይ አገሪቱ የሚኖራትን ቁጥጥር በሚመለከት ተወያይቷል።
በረቂቅ ሕጉ መሠረት አሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን ጠብ አጫሪ ብላ ከፈረጀቻቸው ሌሎች አገራት ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች በወሽመጡ እንዳያልፉ ይከለከላከሉ።
በረቂቅ ሕጉ በተጨማሪም ከእስራኤል ገር ግንኙነት ያላቸው ወታደራዊ እና የሲቪል የጭነት መርከቦች እንዲሁም በኢራን ላይ በተከፈተው ዘመቻ ድጋፍ ያደረጉ እንዳያልፉ ይከለከላሉ።
በተጨማሪም በኢራን ላይ ጉዳት በማድረስ ረገድ ኃላፊነት አለባቸው ተብለው የሚታመኑ አገራትና ግለሰቦች፣ ካሳ እስኪከፍሉ ድረስ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ በኩል የማለፍ ፈቃድ አይሰጣቸውም።
ረቂቅ ሕጉ ለሚፈጸሙ ጥሰቶች ከባድ ቅጣቶችን፤ ከእነዚህም መካከል በመርከብ ላይ የተጫነው ሸቀጥ ካለው ዋጋ እስከ 20 በመቶ የሚደርስ የገንዘብ ቅጣትን አካትቷል።
በሕጉ መሠረት፣ መንግሥት በፋርስ ባህረ ሰላጤ ውስጥ የአሰሳ ስራን ለመቆጣጠር፣ የመርከቦችን እንቅስቃሴ ለመከታተል እንዲሁም ደህንነትን እና የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ ከጦር ኃይሎች ጋር በጋራ እንዲሰራ ይጠበቅበታል።
ሳሊም ሕጉ በባለሙያዎች እየታየ መሆኑን እና ከመጽደቁ በፊት የማሻሻያ ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ይጠበቃል ብለዋል።
የኢራን ፓርላማ ረቂቅ ሕጉ ላይ የተወያየው አገሪቱ ከኦማን ጋር በወሽመጡ አስተዳደር ላይ እየተነጋገረች ባለችበት እና ከሥምምነት ይደረሳል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።