
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, የኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃ በኢራን ድሮኖች ጥቃት ተፈጽሞበት በርካታ መንገደኞች ጉዳት ደርሶባቸዋልየኢራን ድሮኖች የኩዌት አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ረቡዕ ማለዳ ጥቃት መፈጸማቸውን
ተከትሎ በረራዎች መቋረጣቸው ተገለጸ።
በኩዌት የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት የተፈጸመው ቴህራን እና ዋሺንግተን አንዳቸው
በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ሲሆን በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውም ተገልጿል።
ሁለት የኢራን ዜና ወኪሎች ቴህራን የተኩስ አቁሙን ለማራዘም ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን
ንግግር ማቋረጧን ማክሰኞ ዕለት ዘግበዋል።
ትራምፕ ግን ዘገባውን አጣጥለው ንግግሮች እየተካሄዱ ናቸው ብለዋል።
የኩዌት መከላከያ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል ሳዑድ አብዱላዚዝ አል ኦታእቢ
“በርካታ ጥቃት ፈጻሚ ድሮኖች” የኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃን ዒላማ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በጥቃቱ የመንገደኞች ማስተናገጃው ክፉኛ መጎዳቱን የገለጹ ሲሆን “በርካታ ሰዎችን” አቁስሏል
ብለዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው በኢራን ጦርነት ምክንያት ተዘግቶ ከቆየ በኋላ ለአገልግሎት
ክፍት የሆነው ከሁለት ቀናት በፊት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. ነበር።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የአሜሪካ ጦር ኢራን በኩዌት እና ባህሬን ላይ ጥቃት መፈጸሟን
ጠቅሶ በወታደራዊ ተቋማቷ ላይ የአጸፋ ምላሽ ድብደባ ማካሄዱን አስታውቋል።
የአሜሪካ ጦር አክሎም በኩዌት የሚገኙ የጦር ሰፈሮቹን ዒላማ ያደረጉ “በርካታ
ድሮኖችን መትተን ጥለናል” ሲል አስታውቋል።
የኢራን ፈጥኖ ደራሽ አብዮታዊ ዘብ በባህሬን የሚገኝ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ዋና
ማዘዣ እና ኩዌትን በስም ሳይጠቅስ ሌላ አገር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
አክሎም ጥቃቱን የፈጸመው የአሜሪካ ጦር የጣለውን እገዳ ለማለፍ እየተንቀሳቀሰች
የነበረች ነዳጅ ጫን መርከብ ሞተር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎመሆኑን ጠቅሷል።
አብዮታዊ ዘቡ በመግለጫው “ከዚህ በፊት ለማንኛውም ጥቃት የምንሰጠው ምላሽ
የተለየ እና የከፋ እንደሚሆን ተናግረን በነበረው መሠረተ እረምጃውን ወስደናል” ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, reuters