ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኔቶን ዳግም በመተቸት ዋሽንግተን በአውሮፓ ያሏትን የወታደሮች እንቅስቃሴ ዳግም ታጤናለች አሉ
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት የአሜሪካ የኔቶ አጋራት ላይ የሰላ ትችታቸውን በማቅረብ በአውሮፓ በሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች ላይ የስድስት ወራት ግምገማ እንደሚያደርጉ አስታወቁ።
በብራሰልስ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) መከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ "አንዳንድ አገራት የሚወድቁበት ግምገማ ነው። ሌሎች ደግሞ በትልቅ ውጤት ያልፋሉ" በማለት አገራቸውን እየበዘበዙ ነው ያሏቸውን አጋራት ሳይጠቅሱ ተናግረዋል።
መከላከያ ሚኒስትሩ በኢራን ጦርነት ወቅት የአሜሪካ ወታደሮችን ላለማገዝ ገደብ ያወጁ የኔቶ አባል አገራትን ክፉኛ ተችተዋል።
'ኔቶ 3.0' የሚል ሥያሜ ያወጡለት ግምገማው ለአህጉሩ ደኅንነት "ኔቶ በፍጥነት እየተጓዘ እና ለአውሮፓ መሪነት እየተራመደ እንደሆነ ማረጋገጥ" ዓላማ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።
አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ምንም የተወሰነ ነገር የለም ብለዋል።
አሜሪካ የኔቶ አባል አገራት ለአውሮፓ የመከላከያ በጀት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ትፈልጋለች። አንዳንድ አባላት ከጠቅላላ ምርታቸው አምስት በመቶውን እንዲያዋጡ የተቀመጠውን ግብ እንዴት አድርገው እንደሚያሳኩ አላሳዩም ስትልም ትወቅሳለች።
የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩቴ የመከላከያ ወጪያቸው ባለፈው ዓመት 103 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን፤ ይህም የ20 በመቶ ጭማሪ መሆኑን ጠቅሰው አውሮፓዊያን አሜሪካ ያቋረጠቻቸውን ድጋፎች ለማሟላት እየተሯሯጡ ነው ብለዋል።
ሄግሴት ይፋ ያደረጉት ግምገማ አሜሪካ የጥምረቱ የዝግጁነት ኃይል ላይ የነበራትን ድግፍ ለመቀነስ ውሳኔ ላይ መድረሷን ተከትሎ የመጣ ነው።
ዋሽንግተን ድጋፏን እንዴት አድርጋ እንደምትቀንስ ዝርዝሮች እስካሁን ይፋ አልሆኑም። ይሁን እንጂ የአየር እና ባሕር ኃይል አቅሞችን እንደሚያካትት ተጠቁሟል።
ሄግሴት የኔቶ ዓመታዊ በጀት ሌሎች አገራት የመከላከያ ወጪ ግባቸውን መምታታቸው ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።
"አንዳንዶች የኔቶ ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ያላቸው፣ ባለ ፀጋ አገራት፣ ሕግን መሠረት ያደረገ የዓለም አቀፍ ሥርዓት እንዲቀጥል የሚፈልጉ አጋራት እና አንድ ላይ የቆሙ የመካከለኛ ኃያላን በነፃ ተጣብቆ የመጠቀም ዘመን እንደሚቀጥል አሁንም ያስባሉ" ብለዋል።
ሚኒስትሩ የትኞቹን አገራት ለመጥቀስ ፈልገው እንደሆነ ግን በሥም አልጠቀሱም።
አንድ ከፍተኛ የኔቶ ባለሥልጣን አሜሪካ የምታቋርጠው "ሁሉም ነገር" ሙሉ ለሙሉ ሊተካ ይችላል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። ነገር ግን ማክር ሩቴ አንዳንድ ሥራዎች እንደተሰሩ እና ቀጣይ ጥረቶች እንደተጀመሩ ተናግረዋል። ለውጡ ከአሁኑ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ኪንግደም አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ዳን ጃርቨስ ያለ ኢንቨስትመንት ዕቅድ ስበሳበሰውን የተካፈሉ ሲሆን፤ ዕቅዱን ለማጠናቀቅ ሌት ከቀን እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለፈው ግንቦት በኢራን ጦርነት ዙሪያ በአሜሪካው በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በጀርመኑ መራሄ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ መካከል ውጥረት ከተከሰተ በኋላ አሜሪካ 5,000 ወታደሮቿን ከጀመርመን እንደምታስወጣ አስታውቃለች።
ማድሪድ ኢራን ላይ ጥቃት ለመፈፀም የአየር ክልሏ ጥቅም ላይ እንዳይውል መከልከሏን ተከትሎ ትራምፕ ከስፔን ጋር የንግግድ ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ዝተዋል።
የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩቴ አባል አገራት ከጠቅላላ ምርታቸው ቃል የገቡትን የአምስት በመቶ ገንዘብ ያቀርባሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።