ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በርካሽ እየቀረቡ ያሉት የውፍረት መቀነሻ መድኃኒቶች አጠቃቀም ለምን አሳሳቢ ሆነ?
በዴንማርክ የመድኃኒት አምራች ኖቮ ኖርዲክስ ስር የሚገኘው የዌጎቪ እና ኦዜምፒክ የክብደት መቀነሻ መድኃኒቶች የፈጠራ ባለቤትነት መብት አብቅቷል።
ይህም የተለያዩ አገራት የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች መድኃኒቶቹን በመሥራት በርካሽ ለገበያ እንዲያቀርቡ በር ይከፍታል። ይህም የዋጋ ፉክክር ስለሚፈጥር ዋጋውን ከግማሽ በላይ በመቀነስ ለሕንድ እና ለሌሎች አገራት በፍጥነት ሊዳረስ የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራል።
የኢንቨስትመንት ባንኩ ጄፈሪስ ይህንን አጋጣሚ ለሕንድ "አስማታዊ ጊዜ ነው" ሲል ጠርቶታል። በትክክለኛው ዋጋ እና አጠቃቀም ከተመራ ሴማግሉቲድ የተባለው የክብደት መቀነሳ መድኃኒት የአገር ውስጥ ገበያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተንብይዋል።
ወደ 50 የሚጠጉ የተለያየ የምርት ስያሜ ያላቸው የሴማግሉቲድ መድኃኒቶች በወራት ውስጥ ወደ ገበያ እንደሚገቡ ተንታኞች ይጠብቃሉ።
ይህ አካሄድ ከፍተኛ ፉክክር ባለበት የሕንድ የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ውስጥ የተለመደ አሠራር ነው። ሲታግሊፕቲን የተሰኘው የስኳር በሽታ መድኃኒት በ2022 የፈጠራ ባለቤትነት መብቱን ሲያጣ፣ በአንድ ወር ውስጥ ወደ 30 የሚጠጉ የምርት ስያሜ ያላቸው ወደ ገበያ ሲገቡ ይህ ቁጥር በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 100 ደርሷል።
በአሁኑ ጊዜ ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው የሕንድ የመድኃኒት ኢንዱስትሪ በ2030 በእጥፍ እንደሚጨምር ይጠበቃል። ኢንዱስትሪው በአብዛኛው የተገነባው ርካሽ መድኃኒቶችን (ጄኔሪክ) በማምረት ሲሆን አሁን ደግሞ በሴማግሉቲድ ላይ ከባድ ውድድር እንደሚኖር ይጠበቃል።
መጀመሪያ ላይ የስኳር በሽታን ለማከም የተዘጋጁት እነዚህ መድኃኒቶች አሁን ክብደት በመቀነስ ረገድ ጨዋታ ቀያሪ ተደርገው እየተወሰዱ ነው። ሴማግሉቲድ የምግብ ፍላጎትን እና የደም ስኳርን የሚቆጣጠር ሆርሞንን የመሰለ ሚና ያለው ሲሆን ጂኤልፒ-1 በመባል በሚታወቁ የመድኃኒት ክፍሎች ውስጥ ይመደባል።
መድኃኒቱ የኢንሱሊን ልቀትን በማሳደግ እና የሆድ ባዶነትን በማዘግየት፣ ሰዎች እንዲጠግቡ እና ረዘም ላለ ጊዜ እንዳይራቡ ያደርጋል። በዓለም ላይ በጣም ከሚፈለጉ የክብደት መቀነሻ ሕክምናዎች መካከል ሆኗል።
በርካታ የሕንድ የመድኃኒት አምራቾች ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው። ፋርማክራክ የተባለው የምርም ተቋም ምክትል ፕሬዝዳንት ሺታል ሳፓሌ እንደገለጹት ከሆነ ሲፕላ፣ ሰን ፋርማ፣ ዶ/ር ሬዲስ ላቦራቶሪስ፣ ባዮኮን፣ ናትኮ፣ ዚደስ እና ማንዳይማርክ ፋርማ ያሉ ዋና ዋና ኩባንያዎች የታወቁ ጄኔሪክ መድኃኒቶችን እያዘጋጁ ሲሆን፣ ብዙዎቹም ተመሳሳይ እርምጃ የመውሰድ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ዋጋውም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ይጠበቃል።
አሁን ያለው ወርሃዊ የሕክምና ወጪው ከፍተኛ ነው።
ኦዜምፒክ ከ95 አስከ 119 ዶላር ይሸጣል። ዌጎቪ ደግሞ ከ108 አስከ 173 ዶላር ሊያወጣ ይችላል። ውድድሩ ሲጠናከር ወርሃዊ ዋጋው ከ36 አስከ 54 ዶላር እንደሚወርድ ይጠበቃል።
ዝቅተኛ ዋጋ ሲኖር ደግሞ ገበያውን ሊለውጠው ይችላል።
የሕንድ ፀረ-ውፍረት መድኃኒት ዘርፍ (በመርፌ የሚወጉ እና በአፍ የሚወሰዱ መድኃኒቶችን ይጨምራል) በ2021 ከነበረበት 16 ሚሊዮን ዶላር ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር በፍጥነት አድጓል ሲል ፋርማክ ዘግቧል። በ2022 የራይቤልሰስ የመጀመሪያው በአፍ የሚወሰድ መድኃኒት መሠራት ከተጀመረ በኋላ ፍላጎቱ በፍጥነት ጨምሯል።
ሕንድ ውስጥ ከ77 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዓይነት 2 የስኳር በሽታ አለባቸው። በዓለም ላይ ካሉት ከፍተኛ ውፍረት ያለባቸው አዋቂዎች ካሉባት አገሮችም አንዷ ናት። የከተሜነት የአኗኗር ዘይቤ፣ ካርቦሃይድሬት የበዛባቸው አመጋገቦች እና ዘና ያሉ ልማዶች ለበሽታው እና ለውፍረቱ መጨመር ምክንያት ሆነዋል።
ርካሽ የጂኤልፒ-1 መድኃኒቶች መኖር ዶክተሮች ሕክምናውን እንዲያከናውኑ አዲስ አማራጭ ሊፈጥርላቸው ይችላል።
ክብደት መቀነሻ መድኃኒቶችም ከኢንዶክሪኖሎጂ ሕክምና በመሻገርም ላይ ናቸው። የልብ ሐኪሞች ታካሚዎች እንደ አንጂዮፕላስቲ ካሉ ቀዶ ሕክምናዎች በፊት ለውፍረት መቀነሻነት ይጠቀሙበታል። ከጉልበት ቀዶ ሕክምና በፊት በመገጣጠሚያዎች ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል ደግሞ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ይጠቀሙበታል።
እነዚህ መድኃኒቶች በሕንድ ውስጥ ላሉ በርካታ የስኳር በሽታ እና ከመጠን በላይ ውፍረት ላለባቸው ታካሚዎች ሕክምና ለመስጠት እንደሚያግዙ ሙምባይ ውስጥ መቀመጫውን ያደረገው የባሪያትሪክ ቀዶ ሕክምና ሐኪሙ ሙፋዛል ላክዳዋላ ተናግረዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተደራሽነቱ ውስን እንደነበርም ገልጸዋል። በመርፌ የሚወሰዱ የጂኤልፒ-1 መድኃኒቶች ውድ እና ለማግኘት አስቸጋሪ ነበሩ። በአፍ የሚወሰደው ራይቤልሰስ በስፋት የሚገኘው ብቸኛው አማራጭ ነበር።
"እነዚህ መድኃኒቶች ርካሽ በመሆናቸው የስኳር ህመምተኞች እና ከመጠን በላይ ወፍራም የሆኑ ሕንዳውያን ማግኘት ይችላሉ" ብለዋል።
"እዚህ የሚመረቱት መድኃኒቶች ጥራት በጣም ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ ዋጋ ካላቸው መድኃኒቶች ጀርባ ያለቸውን የሕንድን የመድኃኒት ኢንዱስትሪ እውነታ ያንጸባርቃል።
አገሪቱ በዓለም ላይ ትልቋ የጄኔሪክ መድኃኒቶች አቅራቢ ስትሆን ከ60 በላይ በሚሆኑ በሕክምና ምድቦች ውስጥ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ ብራንዶችን ታመርታለች። ይህም 20 በመቶ የሚሆነውን የዓለም አጠቃላይ አቅርቦት የሚሸፍን ነው።
ሕንድ "የዓለም የመድኃኒት ማምረቻ" በመባል የታወቀችበት ዝናዋን ያገኘችው ውድ መድኃኒቶችን ወደ ተመጣጣኝ የጅምላ ምርት በመቀየር ችሎታዋ ነው።
በጣም ታዋቂ የሆነችው እንደ ምሳሌ የሚነሳው ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ነው። የሕንድ ኩባንያዎች የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶችን ዋጋ በመቀነስ በአፍሪካ እና በማደግ ባሉ አገራት ህክምናውን በከፍተኛ ሁኔታ ማስፋፋት በቻለችበት ወቅት ነው።
ዛሬ ሕንድ ከ200 በላይ ለሚሆኑ አገራት መድኃኒቶችን ታቀርባለች። ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የአፍሪካ የመድኃኒት ፍላጎት ታሟላላች። በአሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚውሉት 40 በመቶ የሚሆኑት ጄኔሪክ መድኃኒቶችን እና በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆኑትን መድኃኒቶችም ታሟላለች።
"የሕንድ የክብደት መቀነሻ መድኃኒቶች የኤክስፖርት አቅም እጅግ በጣም ትልቅ ነው" ይላሉ የሕንድ የመድኃኒት ኤክስፖርት ፕሮሞሽን ካውንስል ሊቀመንበር ናሚት ጆሺ።
"በውፍረት መጠኑ ምክንያት የአሜሪካ ገበያ ብቻውን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ሊያድግ ይችላል።"
ይህ ለሕንድ የመድኃኒት ንግድ ትልቅ ዕድል ይሆናል። የአገሪቱ አጠቃላይ የመድኃኒት ኤክስፖርት 30.46 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ አሜሪካ ትልቋ የገበያ መዳረሻዋ ሆናለች።
ሆኖም በዶክተሮች ዘንድ ያለው ጉጉት ጥንቃቄ የተሞላበት ነው።
የጂኤልፒ-1 መድኃኒቶች ኃይለኛ ቢሆኑም ግን ከአደጋ ነፃ አይደሉም። እንደ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና የምግብ መፈጨት ችግሮችን ሊያስከትሉ የሚችሉ እና አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የሐሞት ጠጠር ወይም የፓንቻይተስ በሽታ ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሏቸው። በቂ ፕሮቲን ሳይወስዱ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሳይኖር ፈጣን ክብደት መቀነስ መኖሩ የጡንቻ መላላት ሊያስከትል ይችላል።
ዶክተሮች ብዙ ታካሚዎች የመድኃኒቶቹን ጥቅም በተሳሳተ መንገድ እንደሚረዱ ይናገራሉ። አንዳንዶች በሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ የክብደት መቀነስ እንደሚኖር ይጠብቃሉ። ይህም በማኅበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ግፊት እና በታዋቂ ሰዎች ተጽዕኖ የሚፈጠር ነው።
በሙምባይ መቀመጫቸውን ያደረጉት የስኳር በሽታ ባለሙያው ራሁል ባክሲ፤ ስኬት የሚወሰነው በመድኃኒቱ ላይ ብቻ ሳይሆን "በትክክለኛው የታካሚ ምርጫ" ላይ ነው ብለዋል።
ዶክተሮች ከቁመት እና ከውፍረት ምጣኔ በመነሳት እንደ ስኳር በሽታ ወይም ከፍተኛ ኮሌስትሮል ያሉ ተዛማጅ ሁኔታዎችን ይመለከታሉ። የአኗኗር ዘይቤም ወሳኝ ነው። የታካሚው አመጋገብ ጤናማ ካልሆነ መድኃኒቱ ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል።
ታካሚዎች ፈጣን መፍትሄ ለማግኘት ይመጣሉ። "ሰዎች በሦስት ወራት ውስጥ 10 ኪሎ ለመቀነስ ይጠይቃሉ" ብለዋል ባክሲ።
ፈጣን የክብደት መቀነስ ጉዳቶች ሊኖሩት ይችላሉ። በጣም ፈጣን ሲሆን ታካሚዎች ከፊት፣ ከአንገት፣ ከክንድ እና ከጭኖቻቸው ስብ ሊያጡ ስለሚችሉ የደከሙ እንዲመስሉ ያደርጋቸዋል።
"ቀስ በቀስ መቀነስ፣ በፕሮቲን አወሳሰድ፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና በጥንካሬ ሥልጠና ላይ ማተኮር ለጤናማ ውጤት ቁልፍ መሠረቶች ናቸው" ይላል ባክሲ።
ሌላው ተግዳሮት መድኃኒቶቹን ሲያቆሙ የምግብ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ሊመለስ ይችላል። ሰውነት ስብን ለመቀነስ ስለማይችል ከብደት መቀነስ አይኖርም።
"መድኃኒቶቹን ካቆሙ የምግብ ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይመለሳል" ብለዋል ባክሲ።
ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ መድኃኒቶቹን ያለአግባብ የመጠቀም ስጋቶች አሉ።
ታካሚዎች በአካል ብቃት አሠልጣኞች፣ በውበት ክሊኒኮች ወይም ይህን ለማድረግ ሥልጣን በሌላቸው የምግብ ባለሙያዎች ከፍተኛ መጠን እንደሚሰጣቸው ሐኪሞች ሪፖርት ያደርጋሉ። የበይነ መረብ ፋርማሲዎችም አንዳንድ ጊዜ መድኃኒቶቹን ከተወሰነ ምክር በኋላ ይሸጡታል። የውበት ባለሙያዎች ለሰርግ ወይም ለማኅበራዊ ዝግጅቶች ፈጣን የሰውነት መቀነሻ "ጥቅሎችን" ማስተዋወቅ ጀምረዋል።
ርካሽ መድኃኒቶች በስፋት ሲገኙ እንዲህ ያሉ ልማዶች ሊስፋፉ ይችላሉ።
"ርካሽ መድኃኒቶችን በብዛት ማግኘት ማለት የአላግባብ አጠቃቀም ዕድልን ይጨምራል" ይላሉ መቀመጫቸውን በሙምባይ ያደረጉት የደረት ሐኪም ባሁሚክ ካምዳር። "ተጨማሪ ኃላፊነትን እና ጥብቅ ቁጥጥርን ይጠይቃል። በእነዚህ መድኃኒቶች ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ተስፋ አለኝ።"
ይህ ማስጠንቀቂያ ላክዳዋላ ስለምርት ደረጃዎች ያላቸውን ስጋት የሚያስተጋባ ነው።
"እነዚህ በጣም ጠቃሚ መድኃኒቶች ናቸው። ከመድኃኒቶቹ የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሞለኪውሉን መጥፎ ስም እንዲያሰጡት አንፈልግም" ብለዋል።
መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ያለውን ጉጉት ለመቆጣጠር እየሞከረ ነው። የሕንድ የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ባለፈው ሳምንት በሰጠው ምክር የመድኃኒት ኩባንያዎች እንደ ጂኤልፒ-1 ያሉ የሚታዘዙ የክብደት መቀነሻ መድኃኒቶችን በቀጥታ ወደ ሸማቾች እንዳያስተዋውቁ ጠይቋል።
አስደናቂ ውጤቶችን የሚያመጣ ወይም የአመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አስፈላጊነትን የሚያቃልል ማስታወቂያ አሳሳች እንደሆነ ሊቆጠር እንደሚችል ባለሥልጣናት ተናግረዋል። እንዲህ ያሉት መድኃኒቶች በሐኪም ክትትል ስር ብቻ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥቶታል።
በመጪዎቹ ወራት ሕንድ የዋጋ መቀነስን ከቁጥጥር ጋር ማዛመድ መቻሏ ለተቆጣጣሪዎችም ሆነ ለሐኪሞች ፈተና ሊሆን ይችላል።
ለታካሚዎች ክብደት ለመቀነስ የሚረዱ መድኃኒቶችን ከማዘዛቸው በፊት የአኗኗር ዘይቤያቸውን እና አመጋገባቸውን እንዲያሻሽሉ እንደሚጠይቋቸው ባክሲ ተናግረዋል።
መድኃኒቱን ሲያዙም ከፍተኛ የፕሮቲን አመጋገብ እንዲኖራቸው በምግብ ባለሙያ እርዳታ ክትትል ይደረግላቸዋል ብለዋል።
አሁን ያሉት ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት መድኃኒቶቹን ለረጅም ጊዜ መወሰድ ሊያስፈልግ ይችላል። ብዙ ታካሚዎች ግን "የኢንስታግራም ልጥፎችን ካዩ በኋላ ፈጣን መፍትሄ" ለማግኘት በዶክተሮች ላይ ጫና ይፈጥራሉ።
ውጤቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በወር በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጣ መድኃኒት ከሕንድ ውጪ ላሉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ጭምር ተደራሽ ሊሆን ይችላል።