በኬንያ ዋና ከተማ በተደረመሰ ባለ12 ፎቅ ሕንፃ ስር የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት ጥረት እየተደረገ ነው

በኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ አርብ ዕለት የፈረሰው በግንባታ ላይ የነበረ ሕንጻ
የምስሉ መግለጫ, በኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ አርብ ዕለት የፈረሰው በግንባታ ላይ የነበረ ሕንጻ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አርብ ዕለት በኬንያ ዋና የገበያ ስፍራ በሆነው ኢስሊ በግንባታ ላይ የነበረ ባለ 12 ፎቅ ሕንጻ ተደረምሶ ሰባት ሠዎች ሳይቀበሩ አልቀረም ተባለ።

አደጋው የደረሰው ጥቅምት 13 2019 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ሲሆን አካባቢው በገበያተኞች የተጨናነቀ ነበር።

የናይሮቢ ካውንቲ አስተዳዳሪ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ሰዎች በፍርስራሹ ስር ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች መኖራቸውን ገልጿል።

ሕንጻው እንዲደረመስ ያደረገው ምክንያት ግልጽ አልሆነም።

በኢስሊ የፈረሰው ሕንጻ ምድር ቤት ለንግድ ስራ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደነበር የአስተዳዳሪው ጆንሰን ሳካጃ ጽሕፈት ቤት በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

የኬንያ አገር ውስጥ ሚኒስቴር በበኩሉ በፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው ሊሆን ይችላል የተባሉ ሰባት ሰዎችን ለማግኘት አደጋ ጊዜ ሠራተኞች ፍለጋ እያካሄዱ መሆናቸውን አስታውቋል።

"ሕንጻው በፈረሰበት ወቅት በምድር ቤት እና በታችኛው ወለል ላይ የሚገኙ አስራ አንድ ሱቆች ተከፍተው ስራ ጀምረው ነበር። ሰባት ሰዎች መጥፋታቸው ተገልጿል" ሲሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪፕቹምባ ሙርኮመን አርብ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ሙርኮመን እንደተናገሩት፣ በቦታው ላይ ከነበሩት 67 ሰዎች መካከል 66ቱ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ሲያመልጡ፣ አንዱ ግን ጉዳት ደርሶበታል።

የናይሮቢ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኢሳ ሞሐሙድ ሕንጻው በግንባታ ላይ የነበረ እና ከ10 በለይ ወለሎች የነበሩት እንደነበር ተናግረዋል።

በአካባቢው የሕይወት አድን ሠራተኞች ሲደርሱ አካባቢው በሰዎች ተጨናንቆ የነበረ ሲሆን በዘረፋ ላይ የተሰማሩትን እንዲሁም ቆመው የሚመለከቱትን ገለል ለማድረግ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ ለመተኮስ ተገድዷል።

በግንባታ በነበረው ሕንጻ አምስተኛ ፎቅ ላይ እየሰራ እንደነበር ለፈረንሳይ ዜና ወኪል የተናገረው ጆሴፍ ካኡላ ጩኸት ሰምቶ ለማጣራት ሲሞክር ሰዎች ሕንጻው 'እየተደረመሰ ነው' እያሉ እየጮኹ ሲሮጡ መመልከቱን እና ሕይወቱን ለማዳን በፍጥነት መውጣቱን ተናግሯል።

"ሕንጻው ሙሉ በሙሉ ከመደርመሱ በፊት የወጣሁት የመጨረሻው ሰው እኔ ነበርኩ፤ ከዚያም አካባቢው በሙሉ በአቧራ ተሞላ" ሲል ካውላ ተናግሯል።

ካውላ፣ ጥቂት የሥራ ባልደረቦቹ ከመሬት በታች ባለው የሕንጻው ክፍል ውስጥ ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል ይገምታል።

አንድ ከአደጋው የተረፈች ሴት ወደ ሆስፒታል የተወሰደች ሲሆን ሌላ እርዳታ እንዲደረግለት እየጠየቀ የነበረ ግለሰብ ድምጹ መጥፋቱን የፖሊሱ አዛዥ አስታውቀዋል።

በናይሮቢ በግንባታ ላይ የነበረ ሕንጻ ተደርምሶ
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሞሐሙድ የተደረመሰው ሕንጻ ከሌላ በግንባታ ላይ ካለ ሕንጻ ጎን የቆመ ስለነበር ሌላኛውም ሊደረመስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል።

የግንባታ ተሽከርካሪዎች በስፍራው ደርሰው የተከመረውን አርማታ ለማንሳት ጥረት እያደረጉ የነበረ ሲሆን በሕንጻው ወለል ተቀብረው ያሉ ሠራተኞች ካሉ እነርሱን በፍጥነት ለማውጣት ጥረት እያደረጉ ይገኛል።

በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች በሕንጻው ውስጥ ይሰሩ ነበር ላሏቸው ሰዎች መጀመርያ ላይ ደውለው ማነጋገራቸውን እና በኋላ ግን ኔትወርክ በመቋረጡ ስልካቸው መስራት ማቆሙን ይናገራሉ። በአካባቢው የጠፉ ሰዎችን ለማስመዝገብ እንዲረዳ ድንኳን ተዘጋጅቷል።

በፍርስራሹ ውስጥ ተቀብረው ያሉት ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

በናይሮቢ ግንባታ ላይ ያለ ሕንጻ ሲደረመስ ይህ የመጀመርያው አይደለም። የከተማው የሕንጻ ግንባታን ፈቃድ የሚሰጠው መሥሪያ ቤት ተገቢውን ቁጥጥር እና ክትትል አያደርግም የደህንነት መመሪያዎችን እና የግንባታ ደረጃዎችን አይከታተልም በሚል ይከሰሳል።

"ምርመራዎች ይካሄዳሉ" ያሉት የፖሊስ አዛዡ መሀሙድ "ለማንኛውም ቸልተኝነት ተጠያቂዎች በሕግ ፊት መቅረባቸውን እናረጋግጣለን" ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የናይሮቢ አስተዳዳሪ ሕንጻው የግንባታ ፈቃድ እንደነበረው ገልጸው ነገር ግን በሕንጻው ምድር ቤት ሱቆች ተከፍተው ሥራ እንዲጀምር የሚያስችል ምስክር ወረቀት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል።

የኬንያ ካውንቲ አስተዳደሮች ሕጎችን የማስከበር ጠንካራ ሥልጣን ሊኖራቸው ይገባል ያሉት አስተዳዳሪው፣ ደንቦችን ለሚጥሱ አልሚዎች የሚሰጡት ቀላል ቅጣቶች፣ ማስጠንቀቂያዎእ ወይም "እጅን ቸብ የማድረግ" ያህል ቀላል ተደርገው የሚቆጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ኮንትራክተሮች እና መሐንዲሶች፣ ሥራዎቹ በባለሙያዎች ክትትል የሚደረግባቸው መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ይህንን አያደርጉም፣" ሲሉ የኬንያ የምህንድስና ቴክኖሎጂ ተቋም ፕሬዚዳንት ቢቢዬ ማህሙድ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

"እነዚህን አደጋዎች የምናየው ለዚህ ነው... ተጠያቂነት የለም፣" ሲሉም አክለዋል።

የኬንያ ብሔራዊ የግንባታ ቁጥጥር ባለሥልጣን ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ ባለፈው ዓመት በመላ አገሪቱ ከተገመገሙት ሕንፃዎች መካከል 87 በመቶ የሚሆኑት ደረጃውን ያላሟሉ ወይም አስፈላጊው ፈቃድ የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል።

የኬንያ መሐንዲሶች ተቋም ምክትል ፕሬዚዳንት ጆን ኦጋሎ፣ ሕንጻው ከመውደቁ በፊት የማስጠንቀቂያ ምልክቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።

ትናንት በአደጋው ስፍራ ለተገኙ ጋዜጠኞች እንደገለጹት "እዚህ ያሉ ሰዎች እንደ ስንጥቆች ያሉ የጉዳት ምልክቶች እንደነበሩ እየተናገሩ ነው" ብለዋል።

ተገቢ ያልሆኑ የግንባታ ቁሳቁሶችን መጠቀም፣ የሚገነባውን ሕንጻ " ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ" ሊያደርገው እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።