በዓለም ዋንጫ ተጠባቂ የሆኑት ሰባት አፍሪካውያን ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ 10 የአፍሪካ አገራት ይሳተፋሉ። በአጠቃላይ ለዓለም ዋንጫ ያለፉት አገራት 48 ናቸው። ዋንጫውን ለማንሳት ከፍተኛ ፉክክር እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ከአራት ዓመት በፊት ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር በመሆን በኳታር የዓለም ዋንጫ ታሪክ ሠርታለች።
ኬፕ ቬርዴ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ ከአውሮፓውያኑ 1974 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ይሳተፋሉ።
ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ሰባት ተጫዋቾችን መርጧል።
አንቶኒዮ ሴሜንዮ (ጋና)
የተወለደው ለንደን ነው። የሚጫወትበት ክለብ ማንችስተር ሲቲ ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ አልሆነም።
ባለፈው ወር ለኤፍኤ ካፕ ዋንጫ ከቼልሲ ጋር በነበረው ግጥሚያ ግን ተጫዋቹ ችሎታቸውን ማሳየት ችሏል።
የ26 ዓመቱ ተጫዋች ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያመራው በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ቆይታ ካሳለፈ በኋላ ነው። ከ17 የግብ ሙከራዎች ሰባቱን አሳክቷል።
ሌላኛው የጋና እና የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ የሆነው የቶትንሀም ተጫዋች መሐመድ ኩዱስ እና አንቶኒዮ ሴሜንዮ በዓለም ዋንጫ የአገራቸው ተስፋ ናቸው።
ሴሜንዮ ቀድሞ የበርንማውዝ ተጫዋች ነበር። በ2022 በጋና ብሔራዊ ቡድን ይጫወት ነበር።
ጋና በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ አልነበረችም። ስለዚህም ተጫዋቹ አገሩን ወክሎ ግብ የሚያስቆጥርበት መድረክ የሚሆነው የዓለም ዋንጫ ነው።
ጋና ከእንግሊዝ፣ ክሮሽያ እና ፓናማ ጋር በአንድ ምድብ ውስጥ ተካትታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያን ዲዩማንዴ (አይቮሪ ኮስት)
አይቮሪ ኮስት በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ቡርኪና ፋሶን ስትገጥም ግብ አስቆጥሮ አይቮሪ ኮስት ሦስት ለባዶ አሸንፋለች።
ብሐየራዊ ቡድኑ ዝሆኖቹ በሚለው ቅጽል ስሙ ይታወቃል። ከ2014 ወዲህ ለዓለም ዋንጫ ሲያልፉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ያን ዲዩማንዴ በጀርመን ቡንደስሊጋ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።
የ19 ዓመቱ ተጫዋች 12 ጎል አግብቶ ቡድኑ አርቢ ሌይፕዚግ በቡንደስሊጋ ሦስተኛ እንዲሆን እና ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ እንዲመለስ አስችሏል።
በዚህም ምክንያት በከፍተኛ ገንዘብ ወደ ሊቨርፑል ወይም ቼልሲ እንደሚዛወር ይጠበቃል።
በ2025 ከአምስት የአፍሪካ ዋንጫ (አፍኮን) ግጥሚያዎች በአራቱ ተሳትፏል። በዚሁ ዓመት በቡንደስሊጋው ከየትኛውም ተጫዋች በላቀ ሁኔታ ኳስ በማቀበል የላቀ ብቃት አሳይቷል።
በማጥቃት ረገድም ችሎታውን በጀርመን ተፎካካሪ ክለቦች አስመስክሯል። በዓለም ዋንጫ የሚወክላት አይቮሪ ኮስት ከኢኳዶር ጋር ትጋጠማለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሮንዌን ዊልያምስ (ደቡብ አፍሪካ)
ደቡብ አፍሪካ በአውሮፓውያኑ 2010 የዓለም ዋንጫ ካስተናገደች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ አልፋለች።
ባፋና ባፋና በሚለው ቅጽል ስማቸው ይታወቃሉ። በአውሮፓውያኑ 1988 እና በ2002 ከምድብ ሳያፉ ቀርተዋል። በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ዋና ግባቸው ከተመደቡበት ቡድን ማለፍ ነው።
የዓለም ዋንጫን ደቡብ አፍሪካ ስታስተናግድ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ያልቻለች የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
በደቡብ አፍሪካ ሊግ (ማሜሎዲ ሰንዳውንስ) ኮከብ የሆነው ግብ ጠባቂ እና አምበል ሮንዌን ዊልያምስ በተለይም ፍጹም ቅጣት ምት በማዳን ይታወቃል።
በ2023 የአፍኮን ሩብ ፍጻሜ ከኬፕ ቨርዴ ጋር በነበረው ግጥሚያ አራት ጎሎች እንዳይገቡ ማዳኑ አይዘነጋም።
የ34 ዓመቱ ሮንዌን ዊልያምስ አምበልነትን "እንደሚወደው" ይናገራል።
ቡድኑ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እንዲያሸንፍ ያደረገ እና ልምድ ያካበተ ተጫዋች ነው።
ደቡብ አፍሪካ ከዓለም ዋንጫ አዘጋጇ ሜክሲኮ ጋር ከምታደርገው ጨዋታ ቀጥሎ ከቼክ ሪፐብሊክ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ትጋጠማለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሮቤርቶ 'ፒኮ' ሎፔዝ
ኬፕ ቬርዴ ኢስዋቲኒን አሸንፋ እንድታልፍ ቁልፍ ሚና የተወጣው መሃል ተከላካይ ሮቤርቶ 'ፒኮ' ሎፔዝ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኬፕ ቬርዴ ብሔራዊ ቡድን ጎልቶ የሚታየው ተጫዋች ቡድኑን በ2023 አፍኮን የመጨረሻዎቹ ስምንት አገራት ውስጥ ማካተት ችሏል።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እንደ ካሜሩን ያሉ ስመ ጥር አፍሪካዊ አገራት ዝርዝር ውስጥ ኬፕ ቬርዴ መግባት ችላለች።
ሮቤርቶ 'ፒኮ' ሎፔዝ ለብሉ ሻርክስ እንዲጫወት የታጨው በሊንክድኢን ነበር። መጀመሪያ ላይ መልዕክቱ ከፖርቹጋል ስለደረሰው ችላ ብሎት ነበር።
አየርላንድ፣ ደብሊን የተወለደው የ33 ዓመቱ ተጫዋች በ2019 የመጀመሪያዎቹን ግጥሚያዎች አድርጓል።
በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለፈችው ኬፕ ቬርዴ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ከአንዱ በስተቀር በተቀሩት ተሳትፏል።
በቡድኑ የቀድሞ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ስፔን፣ ኡራጓይ እና ሳዑዲ አረቢያ ተደልድለዋል።
ሮቤርቶ 'ፒኮ' ሎፔዝ' ልምዱን እና የመሪነት ችሎታውን ተጠቅሞ ሰፊ ልዩነት እንደሚያመጣ ይጠበቃል።
ብራሒም ዲያዝ (ሞሮኮ)
የሪል ማድሪዱ ተጫዋች ሞሮኮ በአፍኮን 2025 ከነበሯት ኮከቦች አንዱ ነበር።
አዘጋጇ አገር ለመጨረሻው ዙር እስከምትደርስ በነበሩ ግጥሚያዎች አምስት ጎል አስቆጥሯል።
የ26 ዓመቱ ተጫዋች ሞሮኮ ከሴኔጋል ጋር በነበራት ግጥሚያ ቅጣት ምት መሳቱ የማይረሳ ነው። ግብ ጠባቂው ኤዱዋርድ ሜኒ በቀላሉ ነበር ኳሱን ያዳነው።
ሴኔጋላውያን ተጫዋቾች በተቃውሞ ሜዳውን ጥለው መውጣታቸው ይታወሳል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አሸናፊዋ ሞሮኮ ናት ማለቱን ተከትሎ ሴኔጋል ጉዳዩን ወደ ግልግል ፍርድ ቤት ወስዳዋለች።
ዘ አትላንስ ላየንስ በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ብሔራዊ ቡድን አምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚልን እንዲሁም ስኮትላንድ እና ሔይቲን ይገጥማል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢስማይላ ሳር (ሴኔጋል)
ኢስማይላ ሳር ከፔሩ ጋር በተካሄደ የወዳጅነት ጨዋታ ለሴኔጋል ግብ አስቆጥሯል።
የ28 ዓመቱ ተጫዋች ለክሪስታል ፓላስ ካስቆጠራቸው ግቦች ሰባቱ በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የተመዘገቡ እና ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ አሸናፊ እንዲሆን ያስቻሉ ናቸው።
ኢስማይላ ሳር በዓለም ዋንጫ ሲሳተፍ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ 2018 ሴኔጋል በእንግሊዝ ሦስት ለባዶ መሸነፏ አይዘነጋም።
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ዘ ታራንጋ ላየንስ የሚል ቅጽል ስም አለው። ሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ከሆነችው ፈረንሳይ ጋር ይጋጠማሉ።
በቡድኑ ውስጥ ኖርዌይ እና ኢራቅም ይገኛሉ።
በ2002 የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ሴኔጋል ፈረንሳይን አንድ ለባዶ ማሸነፏ አይዘነጋም። ኢስማይላ ሳር አገሩን በዓለም አቀፉ መድረክ ባለ ድል ለማድረግ የሚሰለፍ ይሆናል።
ኦማር ማርሙሽ (ግብፅ)
ኦማር ማርሙሽ በአፍኮን 2025 የናይጄሪያን ቅጣት ምት ማዳን ችሏል።
የ27 ዓመቱ ኦማር ማርሙሽን ማንችስተር ሲቲ የገዛው በ79.5 ሚሊዮን ዶላር ነው።
ዘንድሮ ክለቡ ሊግ ካፕ እና ኤፍኤ ካፕ እንዲያሸንፍ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ማንችስተር ሲቲ ካደረጋቸው ግጥሚያዎች በስምንቱ ብቻ ቢሳተፍም ግብፅ በብሔራዊ ቡድኑ በግንባር ቀደምነት ከምትጠቅሳቸው አንዱ ነው።
ግብፅ በአፍኮን 2025 አራተኛ ደረጃ ላይ ብታጠናቅቅም ተጫዋቹ ሁለት ግብ አስቆጥሯል።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያው ይሆናል።
ፈርኦኖቹ ቅጽል ስማቸው ነው። በዓለም ዋንጫ በመሳተፍ ቀዳሚ የአፍሪካ አገር ሲሆኑ፤ ሰባት ጊዜ ደግሞ አህጉራዊውን ዋንጫ አንስተዋል።
በዓለም ዋንጫ ታሪክ በአውሮፓውያኑ በ1934 በመጀመሪያ ዙር ሲሸነፉ በ1990 እና 2018 ከቡድናቸው አላለፉም።
አምበሉ መሐመድ ሳላህ በቅርቡ ከጉዳት ተመልሷል። አሠልጣኝ ሆሳም ሐሰን ተስፋ የጣሉት በኦማር ማርሙሽ ነው።















