ከዌስት ሃም ባለቤቶች አንዱ ዴቪድ ሱሊቫን ሴቶችን ለወሲብ በማጥመድ ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢሊየነሩ እና ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለብ ዌስት ሃም ባለቤቶች አንዱ የሆኑት ዴቪድ ሱሊቫን ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም በርካታ ሴቶችን ለወሲብ በማጥመድ ክስ ቀረበባቸው።
ከእነዚህ ሴቶች መካከል የተወሰኑት ጥቃቱ የደረሰባቸው በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎች ሳሉ ነው።
በሰባት ሴቶች የቀረበው ክስ የተጋለጠው የቢቢሲው ፓናሮማ እና ታይም በጋራ ባካሄዱት ምርመራ ነው። ምርመራው ከአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ጀምሮ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል።
ሁሉም ክሶች የቀረቡት በወቅቱ በአስራዎቹ እና በ20ያዎቹ መጀመሪያ ላይ በነበሩና በሱሊቫን ዴይሊ እና ሰንደይ ስፖርት ጋዜጣ ሥራ ሲፈልጉ በነበሩ ወጣት ሞዴሎች ነው።
እነዚህ ሴቶች በወሲባዊ ብዝበዛ እና በሥራ ግንኙነቶች ወቅት "ወሲብ እንዲፈፅሙ ማስገደድን" ጨምሮ ትንኮሳ በመፈፀም በሱሊቫን ላይ ክስ አቅርበዋል።
ከእርሳቸው ጋር "ወሲባዊ ግንኙነት" ወይም "ተፈጥሯዊ ባልሆነ መልኩ" ወሲብ ከፈፀሙ የሥራ እድገት እንደሚሰጣቸው ሲገፋፋቸው እንደነበርም ተጎጂዎቹ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው እና ለዚህ ዘገባ ፍሎረንስ እያልን የምንጠራት ሴት ያለ ፍላጎቷ ከእርሳቸው ጋር ግንኙነት ለመፈፀም መገደዷን ተናግራለች።
የ77 ዓመቱ ሱሊቫን ከወሲብ ፊልሞች፣ ጋዜጦች እና እግር ኳስ ሃብት ባካበቱባቸው ጊዜያት የቀረቡባቸውን ክሶች ውድቅ አድርገዋል።
ቅዳሜ ዕለት ቢቢሲ ፓናሮማ እና ታይምስ የምርመራ ሪፖርት ሰኞ እንደሚታተም ካረጋገጡ በኋላ ሱሊቫን ከዌስት ሃም አመራርነታቸው ለቅቀዋል።
ሱሊቫን "በግል ሕይወቴ ላይ ያተኮሩ አስርት ዓመታት የቆዩ፣ ከሐቅ የራቀ እና ሙሉ በሙሉ ሐሰት የሆኑ ክሶችን" መከላከል ላይ ማተኮር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ምርመራውንም "በመሠረታዊነት ፍትሃዊ ያልሆነ" ሲሉ ገልጸውታል።
ሱሊቫን በ1990ዎቹ 16 ወይም 17 ዓመቷ እንደሆነ ለገለጿት ታዳጊ ለወሲብ እንደከፈሏት አምነዋል።
በዚያን ወቅት ሱሊቫን የ40 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ። 16 ወይም 17 ዓመት ለሚሆናት ሴት የወሲብ ክፍያ መፈፀም ሕገ ወጥ የሆነው በ2003 ነው።
በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ ሱሊቫን በሞደሊንግ ዘርፍ ሥራ የሚፈልጉ ሴቶችን ሲያጠምዱ ነበር።
ፍሎረንስ እንደምትለው በመኖሪያ ቤቱ ለሥራ በተገናኙበት ወቅት ከእርሳቸው ጋር ግንኙነት ካደረገች በጋዜጣው ላይ በመደበኛነት እንደምትወጣ እንደነገራት ገልጻለች።
በዚያን ወቅት የ20 ዓመት ወጣት የነበረችው ፍሎረንስ፣ ምንም እንኳን "የወር አበባዬ ላይ ነኝ" ማለትን ጨምሮ ምክንያቶችን ብትደረድርም ወደ አልጋ ጎትቶ በመውሰድ በግድ ግንኙነት እንደፈፀሙባት ተናግራለች።
የሱሊቫን ጠበቆች ግን ይህንን "አሳማኝ ያልሆነ" ብለውታል።
ሌሎች ሁለት ሴቶችም የወደፊት የሞዴሊንግ ሥራቸውን ላለማጣት ከእርሳቸው ጋር ከመተኛት ውጭ ምንም ምርጫ እንዳልነበራቸው ገልጸው፤ ሱሊቫንን ሥልጣናቸውን እና ሃብታቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ከሰዋል።
አንዷ ሴት "ወጣቶችን መጠቀሚያ እያደረገ ነበር" ብላለች።
ሌላ የቀድሞ ሞዴል በበኩሏ ሱሊቫን ለወሲብ ከጠየቋት በኋላ ስብሰባውን ጥላ ለመውጣት ብትሞክርም በሩ እንደተቆለፈ እና ስትጮህ እንድትሄድ እንደፈቀዱላት ገልጻለች።
ሱሊቫንን በመፍራት እና የበቀል እርምጃን በመስጋት አብዛኞቹ ሴቶች ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈለጉም።
ሴቶቹ የሰጡትን ምስክርነት ከማስታወሻዎች፣ ከፖሊስ እና ሌሎች የድምጽ ቅጂዎች እና ጉዳዩን ከሚያውቁ ጓደኞቻቸው፣ ከቤተሰብ ጋር ከተደረጉ ቃለ ምልልሶች ዘጋቢዎች ያሰባሰቧቸው ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ በምርመራው ስምንት ሴቶች ሱሊቫን የፈፀሟቸውን ጥቃቶች ለከተማዋ እና ኢሴክስ ፖሊስ አጋልጠዋል። ከእነዚህ መካከል አንዷ የምርመራው አካል ናት።
ሱሊቫን የቀረቡባቸውን ሁሉንም ክሶች ውድቅ ያደረጉ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል።
የቀድሞው የዌስት ሃም ሰብሳቢ ዴቪድ ሱሊቫን በአንድ ወቅት ራሳቸውን " ልክ አንዳንድ ሰዎች ቴምብር እንደሚሰበስቡት የሴቶች ሰብሳቢ" ሲሉ ገልጸው ነበር።
"በቀን ሦስት የሚደርሱ ሴቶች ሊኖሩኝ ይችላሉ፤ አንዳንዴ ደግሞ ምንም አይኖረኝም። ይህ በሚኖረኝ ስሜት እና ባሉ ሁኔታዎች ይወሰናል። ከአብዛኞቹ ሴቶች ጋር ፍቅር የመስራት ፍላጎት አለኝ" ሲሉ በ1989 ለአንድ ጋዜጣ ተናግረዋል።
ቢሊየነሩ ሃብታቸውን ያካበቱት ኢንተርኔት ከመምጣቱ በፊት በነበረው በአዋቂዎች ጋዜጣዎች ፣ ፊልሞች፣ የስልክ የግንኙነት መስመሮች እና ጋዜጦች ዘመን ገላቸው የተራቆተ ውብ ሞዴሎችን እና 16 ዓመት የሆናቸውን ታዳጊዎች ለወሲብ በማቅረብ ነው።
በኢንደስትሪው ውስጥ ባሉ አንዳንድ ሰዎች "የወሲብ ፊልም ንጉስ" የሚባሉት ሱሊቫን በአገሪቱ ካሉ ቱጃሮች አንዱ ናቸው።
ሚዲያ፣ በርካታ ንብረቶች እና 14 መኝታ ክፍሎች ባሉት ቅንጡ መኖሪያ ቤታቸው የሕትመት ቢሮ አላቸው።















