ከ325 ሺህ ብር በላይ የሚያስወጣው አዲሱ የአይፎን ስልክ ምን ይዟል?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አፕል አይፎን ስልኮችን ለገበያ ካቀረበ ከ20 ዓመታት በኋላ በስልኩ ላይ የተደረገውን ትልቁን ለውጥ ይፋ አድርጓል።

ረቡዕ ዕለት በኩባንያው ዓመታዊ የምርት ማስተዋወቂያ ዝግጅት ላይ የመጀመሪያውን ታጣፊ የአይፎን ስልክን ማቅረቡን አስታወቋል።

እንደ መጽሐፍ በሚታጠፍ ቅርጽ የተዘጋጀው አዲሱ አይፎን "ዱዎ" ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ እስካሁን ከተመረቱት አይፎኖች ሁሉ በመጠኑ ትልቁ ነው።

አዲሱ ስልክ በአሜሪካ ዋጋው ከ1,999 ዶላር ጀምሮ እስከ 3,200 ዶላር (325 ሺህ አስከ 500 ሺህ ብር በላይ) የሚደርስ ሲሆን፣ እስካሁን ለገበያ ከቀረቡ የአይፎን ስልኮች መካከል ከፍተኛ ዋጋ የሚያስወጣ ነው።

አዲሱ የአፕል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆን ተርነስ አይፎን ዱዎ "አይፓድን መሠረት ያደረገ" መሆኑን ገልጾ፣ የመታጠፍ ባህሪያቱን "ቀላል፣ ለተጠቃሚው የሚገባ እና ሙሉ በሙሉ ቀልጣፋ" ሲል ገልጿል።

ይህን ተጣጣፊ ስልክ ለመሥራት በአፕል ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ጥናት እና ሙከራ ሲደረግበት የቆየ ፕሮጀክት ነው።

ስልኩ ሲከፈት አነስተኛ አይፓድ ይመስላል፤ በሁለት ታጥፎ ሲዘጋ ደግሞ ከተለመደው የበለጠ ሰፊ አይፎን ይመስላል።

ተርነስ እንዳለው፣ አፕል በገበያ ላይ ካሉ ሌሎች ተጣጣፊ ስማርት ስልኮች የተለየ ገጽታ እና አጠቃቀምን ለመፍጠር በማሰብ፤ እነዚህ ስልኮች "ሁለት ስልኮች ተለጥፈው አንድ የሆኑ ይመስላሉ፤ ትልቅ ስክሪን ቢኖራቸውም ከትንሽ ስክሪን የበለጠ ቦታ እንዳይወስድ ያደርጋል" ብሏል።

"ዱዎ የተፈጠረው እጅግ ልዩ ከሆኑ የቴክኖሎጂ ተከታታይ ፈጠራ ውጤት ነው፤ ተጣጣፊ ስልክን ለመጠቀም አዲስ ተሞክሮ እና ልምድ ይፈጥራል ብለን እናምናለን" ብሏል ዋና ሥራ አስፈጻሚው።

ተርነስ ወደ አፕል ከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ ከመድረሱ በፊት በኩባንያው የሃርድዌር ክፍል ውስጥ ለብዙ ዓመታት በከፍተኛ ቦታ ላይ ያገለገለ ሲሆን፣ ተጣጣፊውን አይፎን በማዘጋጀት ሂደት ውስጥም በቀጥታ ተሳትፎ ነበረው።

አሁን የታየው የአይፎንን ዲዛይን ማሻሻል አፕል በአውሮፓውያኑ 2007 ከተዋወቀው የመጀመሪያው አይፎን በኋላ ትልቅ ስኬታማ ምርት ነው እየተባለ ነው።

አፕል ረቡዕ ዕለት አዲሶቹን አይፎን 18 ፕሮ እና አይፎን 18 ፕሮ ማክስም በተጨማሪ አስተዋውቋል። እነዚህ ሁለት አዲስ የአይፎን ስልኮች በአሜሪካ ገበያ ዋጋቸው ከ1,199 ዶላር እና ከ1,299 ዶላር ይጀምራሉ።

አይፎን አሁን ለገበያ ያቀረባቸው አዳዲስ ስልኮች አስካሁን ከቀረቡት መካከል ከፍተኛ የመሸጫ ዋጋ የወጣላቸው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የነበሩት አይፎኖች ከፍተኛው የመነሻ ዋጋ 900 ዶላር (145 ሺህ ብር) ነበር።

አይፎን ስልክ የአፕል ከፍተኛ ሽያጭ ያለው ምርት ሲሆን፣ በየዓመቱ ከኩባንያው ጠቅላላ ገቢ ከግማሽ በላይ ድርሻ ይይዛል።

ባለፈው ሩብ ዓመት ውስጥ ኩባንያው የአይፎን ስልኮቹ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተፈላጊ መሆናቸውን እየገለጸ ሲሆን፣ በቅርቡ የተለቀቀው የአይፎን ስሪትም በታሪኩ በጣም ስኬታማ የምርት እንደነበር አስታውቋል።

ከአይፎን 18 ጀምሮ ያሉት ስሪቶች ተጨማሪ ገጽታን ይዘዋል፤ በዚህም አዲሱ የአፕል የኤአይ (AI) ረዳት በተጠቃሚው ስልክ ውስጥ ያሉ መረጃዎችን እንደ መልዕክቶች እና ኢሜይሎች በማጣራት መረጃ ማግኘት፣ ጥያቄዎችን መመለስ እንዲሁም በተጠቃሚው ስም አንዳንድ ተግባራትን ማከናወን ይችላል።

በተጨማሪም አንዳንድ የሲሪ ኤአይ ገጽታዎችንም በአዲሱ አፕል ዋች (የእጅ ሰዓት) ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ውይይቶችን መቅዳት፣ ማስታወሻ መያዝ እና ንግግርን ቃል በቃል ወደ ጽሑፍ የመቀየር የሚችል ነው።

እነዚህ አዳዲስ ገጽታዎች ግን መረጃዎችን ግላዊ ብቻ አድርገው እንደሚጠብቁ እና አብዛኞቹ የኤአይ ባህሪያት "በመሣሪያው ላይ" ብቻ እንደሚሠሩ በመሆናቸው መረጃዎችን ወደ ሦስተኛ ወገን አሳልፈው እንደማሰጡ ተገልጿል።