ሰሜን ኮሪያ አዲስ ባለ ሁለት ፎቅ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ጣቢያ መገንባቷ ተገለፀ

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን መድረክ ላይ ንግግር እያደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ኃይል ባለቤት ስለመሆኗ በ2022 በይፋ አውጇለች፤ ያሏትን የኒውክሌር መሣሪያዎች በፍጹም አሳልፋ እንደማትሰጥም በአጽንዖት ገልፃለች።
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ባለ ሁለት ፎቅ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ጣቢያ መገንባቷን የዓለም የኒውክሌር መሣሪያዎች ተቆጣጣሪ ተቋም አስታወቀ። ይህንን ድርጊትም "እጅግ አሳሳቢ" ሲል ገልፆታል።

አዲሱ ግንባታ የዋናው ኒውክሌር ማዕከል ዮንግብዮን አካል ሲሆን፣ ዩራኒየምን ለማበልጸግ የሚጠቅሙ እስከ 28 ሴንትሪፊዩጅ የሚባሉ የማሽን ስብስቦችን ማስተናገድ እንደሚችል ተነግሯል።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ባለፈው ወር መጨረሻ በወጣው ሪፖርት፣ ፒዮንግያንግ በሌላ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ቦታ ላይም አዲስ ማስፋፊያ ሰርታ ወደ ሥራ አስገብታለች።

እነዚህ ግኝቶች ሰሜን ኮሪያ በማዕቀብ የተገደበውን የኒውክሌር መሠረተ ልማቷን ቀስ በቀስ እያስፋፋች መሆኗን የሚያመለክቱ ናቸው። ተቆጣጣሪዎቹ ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ ከሰሜን ኮሪያ ከተባረሩ በኋላ በሀገሪቱ ውስጥ የክትትል ሰራተኞች የሌሉት ኤጀንሲው፣ በሳተላይት ምስሎች ላይ በመመስረት ነው ግምገማዎችን የሚያደርገው።

"የዴሞክራሲያዊት ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ኮሪያ የኒውክሌር ፕሮግራም መቀጠሉ እና እየተስፋፋ መሄዱ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን በግልጽ የሚጥስ እና እጅግ የሚያሳዝን ነው" ሲሉ የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው፣ ሰሜን ኮሪያ ዩራኒየም ለማበልፀግ አዲሱ ሕንጻ ስለመገንባቷ ለመጀመሪያ ጊዜ የገለፀው በሰኔ ወር ቢሆንም፣ ግሮሲ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ግንባታው ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተው ነበር።

ኤጀንሲው በሰኔ ወር ሪፖርቱ፣ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እአአ ሰኔ 3 ቀን "አዲስ የኒውክሌር ቁሳቁስ ማምረቻ ፋብሪካ" ጎብኝተው እንደነበር አስታውቋል። ተቋሙ "የዮንግብዮን ዩራኒየም ማበልጸጊያ ማዕከል" እንደሚባልም ጠቅሷል።

ኪም የሀገሪቱን "በእጅጉ የተስፋፋ የማምረት አቅም" አድንቀው፣ ይህም "የላቁ ዕቅዶችን ለማስፈጸም ዕድል ይፈጥራል" ማለታቸውን የኤጀንሲው ሪፖርት ያስረዳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምንም እንኳን ከዓለም ድሃ አገራት የአንዷ መሪ ቢሆኑም፣ ኪም ድብቅ የኒውክሌር መሳሪያዎችን ለመገንባት በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ያወጣሉ። የኒውክሌር መስፋፋትን የሚቃወም የባለሞያዎች ቡድን በ2022 ባወጣው ሪፖርት፣ ይህ ወጪ 640 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ አስታውቋል።

"የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር ፕሮግራም አሳሳቢ የሚያደርገው ብዙዎቹ ተቋሞች የማይታወቁ እና ድብቅ ስለሆኑ ዒላማ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆናቸው ነው" ሲሉ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ኤድዋርድ ሃውል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ከዮንግብዮን ባሻገርም ለምሳሌ እንደ ካንግሶን ያሉ ሌሎች ተቋሞች እንዳሏት እናውቃለን። የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጉዳይ በውጭ እና በአገር ውስጥ ፖሊሲዎቿ ውስጥ የተካተተ በመሆኑ፣ ተጨማሪ የተደበቁ የማምረቻ ቦታዎች እንደሚኖሩ ልናስብ ይገባል" ሲሉም አክለዋል።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ፣ ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ አቅራቢያ በሚገኘው በካንግሶን ያለ ሌላ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ተቋም ውስጥ ሥራዎች መጀመራቸውን የሚያመለክቱ ምልክቶች እንዳሉ ባለፈው ጥር ወር ገልጿል። በካንግሶን አዲስ ተጨማሪ ሕንጻ የተገነባው በ2024 እንደነበረም አስታውቋል።

ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ቦምቦችን የመሥራት አቅሟን እያጠናከረች እንደምትገኝ በገለፀበት የሚያዝያ ወር መግለጫው ደግሞ፣ በዮንግቢዮን የሚታየውን ማስፋፊያ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

የሚሳየል ሙከራ በማድረግ ክብረ ወሰን ያስመዘገቡት ኪም ወደ መሪነት ከመጡ በኋላ የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ፕሮግራም በፍጥነት ተስፋፍቷል። አገሪቱ በአውሮፓውያን 2017 የረዥም ርቀት ሚሳዔል ውጤቷን መሞከር ከጀመረች በኋላ፣ በርካታ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ተኩሳለች።

ከተለያዩ አይነት ሚሳዔሎች በተጨማሪ፣ አገሪቱ እስካሁን ድረስ ስድስት የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራዎችን አካሂዳለች።

ይህ ሁኔታ የሚያሰጋት ደቡብ ኮሪያ አዲስ ልዩነቶችን ለመፍታት አዲስ ንግግር የማድረግ ጥያቄ ነሐሴ ወር ላይ አቅርባ የሰሜን ክፋይዋን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ናት።