አሜሪካ ለተመታባት ሄሊኮፕተር አጸፋ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ሠራዊቷ አስታወቀ
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቴህራን የአሜሪካ ሄሊኮፕተርን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መትታ ጥላለች በማለት ከከሰሱ በኋላ ሠራዊታቸው በኢራን ላይ ጥቃት ፈጸመ።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እንዳስታወቀው ለተመታው አፓቼ ሄሊኮፕተር አጸፋ ማክሰኞ ሌሊት በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም ጀምሯል።
ዕዙ "ዘመቻው በኢራን ለተፈጸመው ተቀባይነት የሌለው ጠብ አጫሪነት ተመጣጣኝ ምላሽ ነው" ያለ ሲሆን፣ በባሕረ ሰላጤው ዳርቻዎች እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተዘግቧል።
የተመታው ሄሊኮፕተር ሁለት አብራሪዎች በአሜሪካ የባሕር ላይ ድሮን አማካይነት መትረፋቸው እና ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ገልጸዋል።
ኢራን ሄሊኮፕተሩን በድሮን መምታቷን የአሜሪካ ባለሥልጣናት የተናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም ብለዋል።
ክስተቱ ማጋጠሙ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ቢዘገብም የአገሪቱ መንግሥት ግን ተመትቶ ለወደቀው የአሜሪካ ሄሊኮፕተር ኃላፊነቱን አለመውሰዳቸውን ሜህር የተባለው የኢራን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የአሜሪካው የዜና ድረ ገጽ አክሲዮስ እንደዘገበው በጥቃቱ ዒላማ የሆኑት የኢራን የአየር መከላከያ እና የራዳር ሥርዓቶች ናቸው። የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ፍንዳታዎች በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ በሚገኙ የአገሪቱ ግዛቶች ላይ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግበዋል።
ከኤቢሲ ኒውስ ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦራቸው ለፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርገው ከስሰዋታል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጥቃቱን ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ “አሜሪካ በጦር ሜዳው ላይ ሽንፈት ቢገጥማትም ቁርጠኝነታችንን እየተፈታተነች ነው” በማለት አገራቸውለሚፈጸምባት ጥቃት አጸፋ እንደምትሰጥ ዝተዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረውም "ሰላም የምትፈልጉ ከሆነ ቀጣናውን ለቅቃቸው ውጡ” በማለት ለአሜሪካ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተመትቶ የወደቀውን የሠራዊታቸውን አፓቼ ሄሊኮፕተርን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠታቸው ቀደም ብሎ የኢራን ዋነኛ ተደራዳሪ እና የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐመድ ባጊር ጋሊባፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
"እኛ የዲፕሎማሲ ቋንቋን ነው የምንርጠው፣ ነገር ግን ሌሎች ቋንቋዎችንም አቀላጥፈን እንናገራለን። ቃላችሁን የማታከብሩ ከሆነ በደምብ ወደምንችለው የንግግር መድረክ ፊታችንን እናዞራለን” በማለት አሜሪካን በምትፈልገው መልኩ እንደሚያስተናግዷት አስጠንቅቀዋል።