ትራምፕ የካናዳውን አውሮፕላን አምራች የአሜሪካ ገበያ ለማቆም ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳው አውሮፕላን አምራች ቦምባርዲየር ተቋሙን ወደ አሜሪካ ካላዘዋወረ በስተቀር በአሜሪካ ምርቶቹን መሸጥ እንደማይችል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠነቀቁ።
“ከዚህ በኋላ ቦምባርዲየር በአሜሪካ አይሸጥም። ገበያችንን ከፈለጉ እዚህ መጥተው ማምረት ይችላሉ። አሜሪካ ላይ መንጠልጠል አቁሙ” ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ጽፈዋል።
በአሜሪካ እና ካናዳ መካከል ያለው የንግድ ጦርነት እየተባባሰ መጥቷል።
ትራምፕ አውሮፕላን አምራቹን እንደሚያግዱ የገለጹት ካናዳ በዋሽንግተን ለተጣለባት ታሪፍ የአጸፋ ታሪፍ ለመጣል ሰዓታት ሲቀራት ነው።
ካናዳ በአሜሪካ ምርቶች ላይ 20 በሊዮን ዶላር የሚያወጣ ታሪፍ ለመጣል አቅዳለች።
አውሮፕላን አምራቹ ባወጣው መግለጫ በሺህዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ሠራተኞች እንደቀጠረ አስታውቋል። ከአሜሪካ ተቋማት ጋር ላለው ትስስር ዋጋ እንደሚሰጥም ጠቅሷል።
ትራምፕ አውሮፕላን አምራቹን በምን መንገድ ከአሜሪካ ገበያ እንደሚያግዱ ግልጽ አይደለም።
መቀመጫው በካናዳ ሞንትሪያል ቢሆንም በአሜሪካ ካንዛስ ግዛት ፋብሪካ አለው።
በዚህ ፋብሪካ 3,500 አሜሪካውያን ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ያመርታል።
በቴክሳስ፣ አሪዞና፣ ፍሎሪዳ፣ ኮነትኬት፣ ኤልኖይስ፣ ዳላዌር፣ ካሊፎርንያ፣ ዲሲ እና ኒው ጀርሲም ይሠራል።
ቢቢሲ ከካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ቢሮ ምላሽ ጠይቋል።






