
የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, በሆርሙዝ ወሽመጥ በባንዳር አባስ አቅራቢያ መርከቦች ሲያልፉኦማን ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድታስተዳድር የሚያስችል ዕቅድ ማቅረቧን እና ምክረ ሃሳቡ
የባሕረ ሰላጤው አገራትን ድጋፍ ማግኘቱን ሮይተርስ ዲፕሎማቶችን እና ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።
በዕቅዱ መሠረትበወሽመጡ ላይ የሚያልፉ መርከቦች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ክፍያ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ ተብሏል።
ዕቅዱ አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ ጦርነት ማወጃቸውን ተከትሎ በወሽመጡ ላይ
የሚያልፉ መርከቦች እንቅስቃሴ መገታቱን ያስቀራል ተብሏል።
ለሁለት ሳምንት ሲካሄድ የነበረውን የአየር ድብደባ ያስቆሙት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ
ከኢራን ጋር “ጥሩ ንግግር እየተካሄደ” መሆኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን ኢራን ወደ ድርድር ጠረጴዛው የማትመለስ ከሆነ የአሜሪካ ጦር ድብደባውን
እንደሚቀጥል ዝተዋል።
ኢራን ግን ከአሜሪካ ጋር ንግግር ዳግም ለመጀመር ፍላጎት እነደሌላት በመግለጽ አስተባብላለች።
ዋሺንግተን በቴህራን ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።
አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 221 2018 ዓ.ም. በቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ
በኋላ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።
ባለፈው ወር በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ወሽመጡ በከፊል
ለመርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት ሆኖ ነበር።
ነገር ግን ከሁለት ሳምንት በፊት ኢራን በወሽመጡ በኩል ፈቃድ ያላገኙ መርከቦች እያለፉ
ነው በሚል ጥቃት በመፈጸሟ ስምምነቱ ፈርሷል።
ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ከኦማን ጋር በመሆን ማስተዳደር እና መርከቦችን ክፍያ ማስከፈል
እንደምትፈልግ ተናግራለች።
ዋሺንግተን በበኩሏ የሆርሙዝ ወሽመጥ ከጦርነቱ በፊት እንደነበረው ያለምንም ክፍያ
መርከቦች የሚተላለፉበት እንዲሆን ትፈልጋለች።
አክላም በግዴታ ቀረጥ ማስከፈል ሕገወጥ ነው ስትል አስጠንቅቃለች።
በኦማን ዕቅድ ዙሪያ ማብራሪያ የተሰጣቸው የባሕረ ሰላጤው አገር ባለሥልጣናት እና
ዲፕሎማቶች ለሮይተርስ እንደተናገሩት በምክረ ሃሳቡ መሠረት ኢራን ወሽመጡን ብቻዋን የማትቆጣጠር ሲሆን ክፍያም ቢሆን በፈቃደኝነት
ይሆናል ተብሏል።
ኦማን
ያቀረበችው ዕቅድ በኤዢያ የሚገኘው በማላካ ወሽመጥ ተግባራዊ ከሚደረገው ጋር ተመሳሳይ ነው። በማላካ ወሽመጥ ኢንዶኔዢያ፣ ማሊዢያ
እና ሲንጋፖር መርከቦች በፈቃደኝነት ክፍያ እንዲፈጽሙ ይጠይቃሉ። ገንዘቡ የመርከቦችን ፍሰት
ለማሻሻል፣ የአካባቢ ጥበቃ ለማካሄድ እና በአደጋ ጊዜ የሕይወት አድን ሥራዎችን ለመደገፍ ይውላል።
የባሕረ ሰላጤው ምንጮች እስከ ሰኞ ምሽት ድረስ ከኢራን የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ አለመኖሩን
ተናግረዋል።
የኦማን ባለሥልጣናት እና የኢራን ባለሥልጣናት በቴህራን በሳምንቱ መጨረሻ ተገናኝተው
ተወያይተው ነበር።