የአሜሪካ ልዑካን የፈረንሳይን ንግግር በመቃወም የተመድ ጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባን አቋርጠው ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ልዑክ፤ የፈረንሳይ ተወካይ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር በመቃወም አዳራሹን ጥለው ወጡ። የፈረንሳዩ አምባሳደር በሰኞ ዕለቱ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር አሜሪካ በተመድ ጉባኤ የሰጠችውን ድምጽ ከአምባገነን መንግሥታት ጋር አነጻጽረዋል።
የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ የጀመረው ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ቮልከር ተርክን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ድምጽ በሰጠበት ወቅት አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ጋር በመሆን ተቃውሞዋን ካሰማች በኋላ ነው።
የፈረንሳይ የተባበሩት መንግሥተት ተልዕኮ ከአርብ ዕለቱ ድምጽ የመስጠት ሂደት በኋላ የአሜሪካን ውሳኔ ከሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ በማነጻጸር ተችቷል። ተልዕኮው በኤክስ ገጹ ባጋራው ልጥፍ “አሜሪካ የሰብአዊ መብቶች ምልክት ነበረች፤ ከአሁን ወዲህ አይደለችም” ብሏል።
ለዚህ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ዋልትዝ፣ ፈረንሳይ “ከዓለማችን የከፉ ጨቋኞች ጋር ሲወዳጅ” ለነበረው የሰብአዊ መብቶች ኃላፊ ድምጽ ሰጥታለች በማለት ከስሰዋል። አምባሳደሩ ምን ለማለት እንደፈለጉ አላብራሩም።
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ ከዚህ ቀደም ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ የምታካሂደውን ጦርነት እንዲሁም የእስራኤልን የጋዛ ዘመቻ ሲተቹ ነበር።
የአሜሪካ ልዑክ አባላት የሰኞ ዕለቱን ስብሰባ ጥለው የወጡት፤ የፈረንሳይ አምባሳደር ጀሮም ቦናፎንት ንግግር ሲያደርጉ ነው። አስቸኳይ ስብሰባው የተጠራው ሩሲያ የምታካሂደው ዩክሬን ጦርነት ላይ ለመምከር ነበር።
ፈረንሳይ ይህንን “አዋራጅ እና አክብሮት የጎደለው ንግግሯ ውድቅ” እስከምታደርግ ድረስ የዋሽንግተን ልዑካን ተመሳሳይ ተቃውሞ ማሰማት እንደቀሚጥሉ የአሜሪካ አምባሳደር ዳን ኔገሬ ተናግረዋል።
በ144 አገራት ድጋፍ፣ በ10 ተቃውሞ እና 13 ድምጸ ተዐቅቦ በጸደቀው የተርክ የኃላፊነት ዘመን ላይ የተነሳው ውዝግብ፤ በአሜሪካ እና በተባበሩት መንግሥታት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ያሳያል።
የትራምፕም አስተዳደር ለተመድ ተቋማት የሚያደርገው ድጋፍ ያቋረጠ ሲሆን አሜሪካ ከበርካታ ተቋማት አባልነት እንድትወጣም አድርጓል።













