ኢራን፤ እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መቆም አለበት” አለች

የፎቶው ባለመብት, EPA/ Shutterstock
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ዛሬ ሰኞ ማለዳ ከቱርክ፣ ከኢራቅ እና ከግብፅ አቻዎቸው ጋር በስልክ መወያየታቸውን በቴሌግራም ገጻቸው ላይ አስታወቁ።
አራግቺ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ጋር እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መቆም እንዳለበት” መወያየታቸውን አስፍረዋል።
አራግቺ አክለውም ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የአሜሪካ ኃላፊነት እንደሆነም ገልጸዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ አገራቸው ጦሯን የደኅንነት ቀጣና ብላ ከከለለችው ደቡባዊ ሊባኖስ፣ ጋዛ እና ሶሪያ እንደማታስወጣ አስታውቀዋል።
ኢራን በሊባኖስ ባለው ሁኔታ የተነሳ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነም አገራቸው “ሙሉ ኃይሏን ተጠቅማ” ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቀዋል።
ካትዝ በደቡባዊ ሊባኖስ ያለው የደኅንነት ቀጣና ከአካባቢው ነዋሪዎች እና “ከሁሉም የሽብር መሠረተ ልማቶች፣ በመንደሩ ከሚገኙ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቤቶች” ነጻ እንደሚሆን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።









