"ልጆቻችንን ትምህርት ቤት መላክ ያስፈራናል"- ፍልስጤማውያን ወላጆች

ፍልስጤማውያን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል። አል-ሙግሀይር የወንዶች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በጠዋት ተማሪዎችን ለመቀበል ተገኝቷል።
በይዞታ ሥር ባለው ዌስት ባንክ የሚገኘው ትምህርት ቤቱ በቅርቡ የብረት አጥር ተሠርቶለታል። በወይራ ዘይት ዛፍ መካከል ብረቱ ይታያል።
ባሳም አል አሲፍ "ፈርተናል። ተማሪዎችና ወላጆችም ፈርተዋል" ይላል።
በያዝነው ዓመት በአል-ሙግሀይር ሦስት ተማሪዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል። ሰፋሪዎች ፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት እየተባባሰ መጥቷል።
ከተገደሉት አንዱ የ14 ዓመቱ አውስ አል-ናሳን ነው። ከትምህርት ቤቱ ውጭ ከሰፋሪ በተተኮሰ በጥይት ተገድሏል።
የእንግሊዘኛ መምህር ዋህድ አቡ ናይም "ክፍል ውስጥ ነበርኩ። ሁለት ተማሪዎች እየሮጡ መጥተው ሰፋሪዎች የትምህርት ቤቱን አጥር እንደዘጉት ነገሩኝ" ሲል ያስታውሳል።
የመምህሩ ወንድም ጂሀድ በእስራኤል ወታደር ተገድሏል።
ዋህድ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በማስገባት ሕይወታቸውን ለመታደግ ሞክሯል።
ሰፋሪዎች ተማሪዎቹ ላይ እየተኮሱ ነበር። በስልክ የተቀረጸ ቩድዮ አውስ የተተኮሰበትን ቅጽበት ያሳያል።
"በጀርባው ሳዞረው ብዙ ደም እንደፈሰሰው አየሁ። ከአፉና አፍንጫው ደም ይፈስ ነበር። ጥይቱ ጭንቅላቱን ነው የመታው። አጥተነዋል።"
ተማሪዎች ከግድግዳ ጀርባ ሲደበቁ ሰፋሪዎች መተኮስ ቀጠሉ። አንዳንድ ተማሪዎች መሬት ላይ ተኝተው ከጥይት ለማምለጥ ሞክረዋል።
የእስራኤል መከላከያ "ንጹኃንን እና ወታደር" የጫነ መኪና ላይ ድንጋይ ሲወረወር ወታደሩ መተኮስ ጀመረ" ብሏል።
ወታደሩ ከሥራ ታግዶ ምርመራ እንደተከፈተ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከዚያን ቀን ጨምሮ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ወላጆችም ስጋት ገብቷቸዋል።

ትምህርት ተዘግቶ ሳለ ሁለት ታዳጊዎች በእስራኤል ኃይሎች ተገድለዋል።
በመንደሩ በተፈጸመ የሰፋሪዎች ጥቃት የ19 ዓመት ወጣት ከትምህርት ቤት ሲወጣም ተገድሏል።
የእስራኤል ጦር ሁለቱም ግድያዎች የተፈጸሙት "ለነውጠኛ አመጽ" ምላሽ ሲሰጥ ነው ብሏል።
ትምህርት ቤት ሲከፈት ወላጆች ልጆቻቸውን መላክ አስፈርቷቸዋል።
በራማላህ የሚገኘው አል-ሙግሀይር መንደር በአይሁዳውያን ሰፋሪዎች እየተከበበ ነው።
የእስራኤል ጦር እንቅስቃሴ በማገድ መግቢያ እና መውጫውን ይቆጣጠራል።
የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ባሳም አል አሲፍ ረዥም የብረት አጥር መዘርጋቱን ይናገራል። ይህም የወላጆችን ስጋት ለመቀነስ ነው።
መንገድ ላይ አምቡላንሶች ተሰማርተዋል። ወላጆች ቀኑን ሙሉ ከትምህርት ቤት ውጭ ሆነው ልጆቻቸውን እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።
ልጆቹ የአንደኛ እና ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች የሆኑት ሀሩን ሚሻራ "የመጣሁት ልጆቼ እየጠበቅኳቸው እንደሆነ ሲያውቁ ደኅንነት ስለሚሰማቸው ነው" ይላል።
"ዘንድሮ የበለጠ ለልጆቻቸውን ፈርተናል። ትምህርት ቤት ለአደጋ እንደሚጋለጡ እናውቃለን" ሲል ያክላል።
ከፍርሃት ባሻገር በጽናት መቆምም ይፈልጋሉ። የሰፋሪዎች ጥቃት ልጆቻቸውን እንዲያሰጋ አይሹም።
ተማሪዎቹ በመጀመሪያው የትምህርት ቀን ላይ ከአስተማሪዎቻቸው በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
ሰፋሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ከመጡ እንዲጮሁ፣ እንዳይጠጓቸው፣ እንዳያዋሯቸው ተነግሯቸዋል።
ትምህርት ተጀምሮ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሰፋሪዎች በመስኮት በኩል ይታዩ ጀመር።
ሁለት ወንዶች ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ማሳ በግ እየነዱ ይሄዳሉ። የእስራኤል ወታሮች በቅርብ ርቀት ይታያሉ።
"ከመጋቢት ጀምሮ ወደ መንደሩ እየጠጉ ነው። አሁን ወታደሮች ሰፋሪዎቹን ያመጧቸዋል" ይላል አኑ ናይም ነው።
ቢቢሲ ከእስራኤል ጦር አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
በዓለም አቀፍ መርሕ መሠረት በዌስት ባንክ ያለው ሰፈራ ሕገ ወጥ ነው። በእስራኤል ሕግም ሰፈራው ሕገ ወጥ መሆኑ ይገለጻል።
አምቡላንስ በቦታው የተሰማራው ሕገ ወጥ ሰፋሪዎችን ለማስወጣት ሳይሆን ድጋፍ ለመስጠት ነው።
ሀዲ አል ናሳን በመንደሩ የአምቡላንስ ሾፌር ነው። ባለፈው ዓመት የእስራኤላውያን ወታደሮች አካሄድ መለወጡን ይናገራል።
በመንደሩ የሚገደሉ እና ጉዳት የሚደርስባቸው ፍልስጤማውያን ቁጥር ጨምሯል።
በ2025 መባቻ የሰፋሪዎች ጥቃት ውስን ነበር። በ2026 ግን መለወጡን ይናገራል።
"ሰፋሪዎቹ በወራሪ ወታደሮች ይደገፉ ጀመር። ዘንድሮ የሰማዕታት ቁጥር ጨምሯል። ሆነ ብለው ልጆችን ዒላማ በማድረግ ወላጆች ቤታቸውን ሸሽተው እንዲወጡ ማስገደድ ይፈልጋሉ።"
የተባበሩት መንግሥታት አጣሪ ኮሚሽን ሰኔ ላይ ባወጣው መረጃ "ፍልስጤማውያን መሬታቸውን ጥለው እንዲሸሹ ለማድረግ ሰፋሪዎች ልጆች ላይ ጥቃት ማድረስን እንደ መሣሪያ እየተጠቀሙ ነው" ብሏል።
"ሰፋሪዎች ሆነ ብለው በስልታዊ መንገድ ፍልስጤማውያን ልጆች ላይ አነጣጥረዋል። ልጆቹ ቤታቸው አቅራቢያ እየተጫወቱ፣ ወደ ትምህርት እየሄዱ ወይም ከብት እየጠበቁ ሳለ ነው ጥቃት የሚደርስባቸው። የዕለት ከዕለት ሕይወታቸው በፍርሃት ተሞልቷል" ሲልም አክሏል።
እስራኤል ሪፖርቱን "ሐሰተኛ" ስትል አጣጥላለች።

አርሶ አደሩ ሳሚ አቡ ራህማ እንደሚለው ሰፋሪዎች ልጆችን ዒላማ እያደረጉ ነው።
ነሐሴ ላይ የዘጠኝ ዓመት ልጁ ሳሊም ተተኩሶበት ተጎድቷል። ከወንድሞቹ ጋር እየተጫወተ ሳለ ነበር ጥቃት የተፈጸመበት።
ጥይቱ አሁንም ክንዱ ውስጥ ይገኛል። ሳሊም ሰፋሪዎቹ መምጣታቸውን ለወላጆቹ እየተናገረ ሲሮጥ የሚያሳይ ቪድዮ ወጥቷል።
"በዛ ቅጽበት ማሰብ ታቆማለህ። በፍርሃት ትሞላህ። ጥቃት አድራሾች የሚተኩሱት ለመግደል ነው። በሕይወትህ ያለውን ውድ ነገር ማጣትን ነው የምታስበው" ሲል ሳሚ ቅጽበቱን ይገልጻል።
ልጁ ላይ የተኮሰው ሰፋሪ እዚያው አካባቢ ይኖራል። ሰኔ ላይም ሳሊም ላይ ተኩሷል።
"መንገድ ላይም ይሁን በትምህርት ቤት ልጆህን መጠበቅ እንደማትችል ይሰማሀል። ሰፋሪዎች እዚህ እንድንኖር አይፈልጉም። እዚህ የወደፊት ሕይወት የለንም።"
በአካባቢው ያለው የሰፋሪዎች ምክር ቤት ተጠርጣሪው ከሥራ ውጭ ሆኖ የተኮሰ ወታደር እንደሆነ አስታውቋል።
"አይሑዳውያን ወይም አረቦች የሆኑ ንጹኃን ላይ የሚደርስ ጉዳት ያሳዝነናል። ሕግ የሚጥስ ጥቃት እንቃወማለን" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
በአል-ሙግሀይር መንደር የሚታየው ጥቃት በይዞታ ሥር ባለው የተቀረው ዌስት ባንክም ይስተዋላል።
ሰፋሪዎች የፍልስጤማውያንን መንደሮች ይከብባሉ። የእስራኤል ወታደሮችም ከለላ ይሰጧቸዋል።
ሀዲ አል ናሲን "ልጆች ወታደሮች ሲገቡ ሲያዩ ምን ያህል የከፋ ሁኔታ እንዳለ አያውቁም። አዋቂዎች ምን እንደሚከሰት ይረዳሉ" ይላል።
ተመድ እንደሚለው በሰፋሪዎች ጥቃት የተጎዱ ፍልስጤማውያን ቁጥር ባለፈው ዓመት ጨምሯል። በአንድ ቀን በአማካይ ሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት ይደርሳል።















