ፊፋ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ የተከለከለውን ሶማሊያዊ ዳኛ ሙሉ የዓለም ዋንጫ ደመወዝ ሊከፍል ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም ዋንጫን ለመዳኘት በአሜሪካ ክልከላ የተደረገበት ሶማሊያው ዳኛ ኦማር አርታን የውድድሩ ሙሉ ደመወዙን ያገኛል ተባለ።

ባለፈው ሰኞ በአሜሪካ የኢምግሬሽን ባለሥልጣናት የዲፕሎማቲክ ፓስፖርቱ እና ቪዛው ውድቅ የተደረጉበት ዳኛው በሚያሚ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለ11 ሰዓታት ተመርምሯል።

የአሜሪካ መንግሥት አርታን አገር ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለው "ከሽብር ድርጅት ተጠርጣሪ አባል ጋር ባለው ግንኙነት" እንደሆነ አስታውቋል።

አርታን በድንበር ባለሥልጣናት ከሶማሊያው አል ሸባብ ቡድን ጋር ባለው ግንኙነት ዙሪያ እንደመረመረ እና ስለ ቡድኑ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግሯል።

"ትክክለኛው ሰነድ እና ሁሉም ነገር ነበረኝ፤ ትክክለኛው ቪዛ ነበረኝ" ሲል አርታን ተናግሯል።

"እኔ ህልሙን ለመኖር እየሞከረ ያለ ተራ ዳኛ ነኝ፤ ለዓለም ዋንጫ መምጣት ትልቁ የሕይወቴ ህልም ነው" ብሏል።

ወደ ቱርክ እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ አርታን ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ከማምራቱ በፊት በኢስታንቡል ከፊፋ እርዳታ ተደርጎለታል።

ምንጮች ለቢቢሲ ምንም እንኳ አርታን በዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ባይሆንም ፊፋ ደመወዙን ለመክፈል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳኞች በዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ለዳኙበት ምን ያህል እንደሚከፈላቸው አያውቁም። ክፍያቸው ከውድድሩ ፍፃሜ በኋላ ነው የሚከፈላቸው።

የ2025 የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ካፍ) የዓመቱ ምርጥ ዳኛ የሆነው ኦማር አርታን፤ በሚቀጥለው ሐምሌ በፓሪስ ሴንት ዠርሜን እና አስቶን ቪላ መካከል በአውስትራሊያ የሚደረገውን የአውሮፓ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን እንዲዳኝ ተጋብዟል።

በሶማሊያ የጀግና አቀባበል የተደረገለት የ34 ዓመቱ ዳኛ አገሩን እና ሕዝቦቹን አመስግኖ የ2030ውን የዓለም ዋንጫ ለመዳኘት ቃል ገብቷል።

ለአርታን 2025 ታሪካዊ ዓመት የነበረ ሲሆን አህጉራዊውን የፍፃሜ ጨዋታ በመዳኘት መጀመሪያው ሶማሊያዊ ለመሆን በቅቷል።

በሰኔ 2025 የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታንም ዳንቷል።

ፊፋ በቺሊ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ኦማር አርታንን የሾመ ሲሆን፤ በዚህ ውድድር ሦስት ጨዋታዎችን መዳኘት ችሏል።

በዓመቱ ፍፃሜ በአፍሪካ ዋንጫ ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን የዳኘ ሲሆን፤ በ2024 በተመሳሳይ ውድድሩን ዳኝቷል።