የሱዳን የጤና ሥርዓት የውድቀት አፋፍ ላይ መድረሱን አንድ የሕክምና በጎ አድራጎት ድርጅት ገለፀ

አንድ ወንድ ታማሚ ከተኛበት አልጋ ፊት ለፊት አንዲት አስታማሚ ሴት ተቀምጣለች። ከእነርሱ ቀጥሎ ያሉ አልጋዎችም በታማሚዎች ተሞልተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሱዳን ሆስፒታሎች እና ሌሎች የጤና ማዕከላት በገንዘብ ድጋፍ እጥረት ምክንያት እየተዘጉ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ዓለም አቀፍ ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት በመላው ሱዳን በርካታ የጤና ተቋማት እየተዘጉ መሆናቸውን እና ቀድሞውንም የተዳከመው የሱዳን የጤና ሥርዓት የውድቀት አፋፍ ላይ እየተጠጋ እንደሆነ ሜዲሲን ሳን ፍሮንቲየርስ (ኤንኤስኤፍ) አስጠነቀቀ።

የሕክምና በጎ አድራጎት ድርጅቱ እንዳለው፣ የሱዳን ከፍተኛ እርዳታ ለጋሽ የነበረችው አሜሪካ የውጭ እርዳታ የሚያቀርበውን ኤጀንሲ ዩኤስኤአይዲን ባለፈው ዓመት ከዘጋች በኋላ፣ በርካታ ድርጅቶች ተለዋጭ የገንዘብ እርዳታ ምንጭ ማግኘት አልቻሉም።

በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የተሰበሰቡ የዓለም መሪዎች ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ ኤንኤስኤፍ ጥሪ አቅርቧል።

በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በሚያዝያ ወር 2015 ዓ. ም. የተጀመረው ጦርነት፣ ዓለም ላይ ካሉት እጅግ አስከፊ ሰብአዊ ቀውሶች አንዱ እንዲፈጠር አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ በሱዳን ከ33 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሕክምና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

አሁንም ቢሆን የሱዳን ከፍተኛ ለጋሽ አሜሪካ ብትሆንም፣ በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅር (ዩኤስኤአይዲ) የሚደገፉ ብዙ ድርጅቶች ያላቸው የድጋፍ አቅርቦት በሰኔ ወር ማብቃቱን ኤንኤስኤፍ ገልጿል። የአውሮፓ መንግሥታትም ዓለም አቀፍ እርዳታቸውን እየቀነሱ መሆኑን አክሏል።

በፓሪስ የሚገኘው የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (ኦኢሲዲ) መረጃ እንደሚያሳየው፣ በአውሮፓውያኑ 2025 የነበረው የዓለም አቀፍ እርዳታ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ21.3 በመቶ ቀንሷል።

"በጦርነቱ የሱዳንን ፍላጎት እየጨመረ ነው፤ የድጋፍ መቀነስ ደግሞ የሚሰጠውን ምለሽ እያሟሸሸ ነው" ሲሉ የተራድኦ ድርጅቱ መሪ የሆኑት ሙሃመድ ኢብራሂም ተናግረዋል።

"ኤምኤስኤፍ በሱዳን የሚያከናውነው ሥራ በግል ለጋሾች ድጋፍ የሚሠራ ነው። ነገር ግን ለሌሎች የጤና አገልግሎቶች የሚሰጥ ድጋፍ ሲጠፋ፣ ክሊኒኮች ይዘጋሉ፣ ሕመምተኞችም የሚሄዱባቸው ቦታዎች ይቀንሳሉ። በዚህም የሚፈጠረው ጫና የእኛን ጨምሮ በቀሪ የጤና ተቋማት ላይ ይወድቃል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ሁኔታ ታካሚዎች ሕክምና ለማግኘት ረዥም እና አደገኛ ጉዞዎችን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። ታካሚዎች ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ረዥም ጉዞ በማድረግ ወደ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ደግሞ የሚገጥማቸው ጉዳይ እጅግ የከፋ እንደሆነ ይነገራል።

ብዙ ጊዜ ሆስፒታሎች "በሌሎች ታካሚዎች ሞልተው ይጠብቋቸዋል" ሲሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት አብዛኛውን ውጊያ ያስተናገደው የምዕራብ ዳርፉር የኤምኤስኤፍ የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ሴባስቲያን ትራፊካንቴ ገልጸዋል።

ኤምስኤፍ እንዳለው፣ በማዕከላዊ ዳርፉር የሚደግፋቸው የሕክምና ተቋማት ከጥር እስከ ሚያዝያ 2026 ድረስ ያስተናገዷቸው ታካሚዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ22.5 በመቶ ጨምሯል።

በግንቦት ወር ብቻ በአካባቢው የሚገኙ 45 የጤና ማዕከላት የሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ መቆሙን ድርጅቱ አመልክቷል።

ለጤና ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ ካልጨመረ "ተጨማሪ ታካሚዎች የሕክምና ተቋም ለመድረስ ረዘም ያለ ጉዞ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ የሕክምና አማራጮቻቸውም ይገደባሉ፤ በተጨማሪም ዘግይተው ስለሚደርሱ ለከፋ አደጋ ይጋለጣሉ" ሲሉ የኤምኤስኤፍ የዩናይትድ ኪንግደም የሰብዓዊ ድጋፍ ተወካይ ሊዝ ሃርዲንግ ተናግረዋል።

ኤምኤስኤፍ እንደሚለው፣ የጤና ሥርዓቱ በገንዘብ እጥረት እየተፈተነ ባለበት በዚህ ወቅት በጤና ባለሙያዎችና ተቋማት ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችም ቀጥለዋል።

በ2025 በሱዳን በሕክምና ተቋማት ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች 1,620 ሰዎች ተገድለዋል። ይህም በዓለም ዙሪያ በጤና ተቋማት ላይ በሚደረጉ ጥቃቶች ምክንያት ከሚሞቱት ሰዎች 82 በመቶውን እንደሚሸፍን ድርጅቱ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከ19.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በ"አደገኛ ደረጃ" የምግብ እጥረት ውስጥ ሲገኙ፣ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ "አስቸኳይ ደረጃ ረሃብ" እየተጋፈጡ ነው።

የሱዳኑን የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የሚሳተፉ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ወደ ዋና ከተማዋ ካርቱም ይገባሉ ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት ውጊያው የመቀነስ አዝማሚያ አላሳየም።

ማክሰኞ ዕለት ከሰሜን ኮርዶፋን ግዛት የወጡ ዘገባዎች፣ በጦር ኃይሉ ቁጥጥር ሥር ባለችው ኡም ሩዋባ ከተማ በድሮን ጥቃት ቢያንስ 11 ሰዎች መገደላቸውን አመልክተዋል።