ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዘውዱ ሃፍቱ ግድያ የዕድሜ ልክ እስር የተፈረደባቸው ግለሰቦች እንዴት በነጻ እንዲሰናበቱ ተወሰነ?
ከሦስት ዓመት በፊት በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ በአሰቃቂ ሁኔታ በተገደለችው ዘውዱ ሃፍቱ ግድያ ተጠርጥረው የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተላልፎባቸው የነበሩት ሁለት ፍርደኞች በነጻ እንዲሰናበቱ ተወስኗል።
ውሳኔው በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ነቀፌታ ገጥሞታል። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም ቁጣቸውን ገልጸዋል።
የመቀለ ከተማ መካከለኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ትናንት ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓ. ም. በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ ያሬድ ገብረሥላሴ እና ሁለተኛ ተከሳሽ አንገሶም ኃይለማርያም የተባሉት ፍርደኞች በነጻ እንዲሰናበቱ ውሳኔ አሳልፏል።
እዚህ ብይን ላይ የተደረሰው "በፍርድ ቤት በማስረጃነት ቀርቦ የነበረ ዲጂታል ማስረጃ ከመዝገብ ቤት ጠፍቷል መባሉን ተከትሎ" መሆኑን የዘውዱ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህ "ወሳኝ ዲጂታል ማስረጃ" ከዘውዱ ሃፍቱ ስልክ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል።
በአክሱም ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር እና የዘውዱን ግድያ በተመለከተ የነበረውን የፍርድ ሒደት በቅርበት ሲከታተል የነበረው ኪሮስ ኃይለሥላሴ፣ "ማስረጃ ከመዝገብ ቤት ጠፍቷል" የሚለው በስፋት ቢሰራጭም፤ ከፍርድ ቤት ያገኘው መረጃ ከዚህ የተለየ መሆኑን ለቢቢሲ አስረድቷል።
የመቀለ ከተማ ነዋሪ የነበረችው ዘውዱ ነሐሴ 13/2015 ዓ. ም. የአሸንዳ በዓል እንዲሁም የጓደኛዋን ልደት ለማክበር በወጣችበት በከተማዋ አዲ ሓውሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ምሽት ላይ ተገድላለች።
የመቀለ ከተማ መካከለኛ ፍርድ ቤት ሐምሌ 4/2017 ዓ. ም. በዋለው ችሎት ግድያውን ፈጽመዋል በተባሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወስኖም ነበር።
የዘውዱ ግድያ እና የፍርድ ሒደት ከፍተኛ ትኩረት ስቦ ነበር። ጉዳዩን አነጋጋሪ ካደረጉት መካከል አንደኛው ተከሳሽ ያሬድ ገብረሥላሴ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የአርሚ 22 አዛዥ እና አሁን የትግራ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ኮለኔል ገብረሥላሴ በላይ ልጅ መሆኑ ነው። ኮሎኔል ገብረሥላሴ የሁለተኛ ተከሳሽ አንገሶም ኃይለማርያም ዘመድም ነው።
የችሎት ውሎዎች የተረበሸባቸው ጊዜያትም ነበሩ።
በፍርድ ሒደቱ ወቅት ዳኞች ላይ "ጫና እየተደረገ" እንደሆነ ሲገለጽ የነበረ ሲሆን ዳኞች በአንድ ወቅት ላይ ሥራቸውን ለማቋረጥ እንደተገደዱም ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ከመጀመሪያው ውሳኔ በኋላ ፍርደኞቹ ባለፈው ዓመት ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም "ይግባኝ አያስጠይቅም" ብሎ የመካከለኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲጸና አዝዟል።
ፍርደኞቹ ከዚህ በመቀጠል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ማለታቸውን ኪሮስ ይናገራል። ሰበር ሰሚ ችሎትም ጉዳዩን አምና ውሳኔ ወደሰጠው ፍርድ ቤት መልሶ "ማስረጃ እንዲጣራ" ትዕዛዝ ሰጥቷል።
"ሰበር ሰሚ ችሎት በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ኦሪጅናል ማስረጃው ቀርቦ እንዲጣራ" እንዳዘዘም ይገልጻል።
ዋነኛው (ኦሪጅናሉ) ዲጂታል ማስረጃ በፌደራሉ መሥሪያ ቤት እንዲቀርብ፣ ከዚያም እንዲጣራ እንዲሁም ባለሙያ ቀርቦ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ተላልፏል።
"የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ማስረጃ እንዲያመጣ ተጠይቋል። ነገር ግን ከፌደራል ተቋም ጠይቆ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም" ሲል ኪሮስ ይናገራል።
ለዚህም ምክንያቱ "አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ከፌደራል ተቋም ዲጂታል ማስረጃውን የሚተረጉሙ እና ሙያዊ አስተያየት የሚሰጡ ባለሙያዎች ወደ መቀለ መምጣት አይችሉም" መባሉ መሆኑን ያስረዳሉ።
የዘውዱ ታናሽ እህት ብርቱካን ሃፍቱ፤ ትናንት ስለተላለፈው ብይን ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ ተከሳሾቹ ይግባኝ ማለታቸውን ተከትሎ "ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ የሚለውን ለመወሰን" ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር።
በትናንቱ የፍርድ ቤት ቀጠሮ "ስለ ሞባይሉ የሚያስረዳ ፖሊስ ኮሚሽነር ይምጣ ተብሎ ነበር" ያለችው ብርቱካን፤ "ጭራሽ የሚያስጠረጥር ነገር የለም ተብሎ በነጻ እንዲወጡ ወስኗል" ስትል የተሰጠውን ትዕዛዝ ታስረዳለች።
ኪሮስ እንደሚለው፤ የተከሳሾቹ ጠበቃ "ባለው ማስረጃ ጉዳዩ እንዲታይ" ተከራክረዋል።
"ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ማጥራት ካልቻሉ ባለው ማስረጃ ጉዳዩ ይታይ ብለው ተከራከሩ። ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ መቅረብ አለበት፣ ማጣራቱ መቀጠል አለበት ብሎ በይበልጥ መከራከር ነበረበት። ግን በነበረው በቂ ያልሆነ ማስረጃ ፍርድ ተሰጠ" ብሏል።
የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከፌደራሉ መሥሪያ ቤት ኦሪጅናል ማስረጃ እንዲያመጣ ቢታዘዝም "አለማምጣቱን" ይገልጻል።
"ፍትሕ ለማስፈን የተቻለውን ያህል ጥረት ሳይደረግ፤ አምና እንዲቀጡ ያደረጋቸውን ማስረጃ ብቻ በማየት ተቃራኒ ውሳኔ ላይ ተደረሰ።ተጨማሪ ማስረጃ አልቀረበም" ይላል ኪሮስ።
ኪሮስ እንደሚያስረዳው ከሆነ፤ የትናንቱን ውሳኔ ያስተላለፉት ሁለቱ ዳኞች ተከሳሾቹ "ምንም መከላከል ሳይጠበቅባቸው ነጻ እንዲሆኑ ሲወስኑ" አንደኛው ዳኛ "የቀረበውን ማስረጃ መከላከል አለባቸው፤ ያስጠረጥራቸዋል" የሚል ተቃውሞ አስመዝግቦ ውሳኔው ተላልፏል።
ብርቱካን እንደምትለው፤ ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት "ኦሪጅናሉ ማስረጃ" እንዲቀርብ ቢታዘዘም "አሁን ባለው ሁኔታ መሠረት ከአዲስ አበባ ወደዚህ መምጣት አይችሉም" በመባሉ ፍርድ ቤቱ የመቀለ የፖሊስ ኮሚሽን ቀርቦ ጉዳዩን እንዲያስረዳ አድርጓል።
አምና በነበረው ሒደት "የዘውዱ ስልክ ወደ አዲስ አበባ ተልኮ በተደረገው ምርመራ ኮዱ ወጥቶ ከሷ በኋላ የማን ሲም ካርድ እንደገባ ከእነቁጥሩ እና ፎቶው ወጥቷል" ስትል ታስታውሳለች።
ዘውዱ ስልኩን "እስከ ነሐሴ 13/2015 ዓ. ም. ይዛው እንደነበር" እና ከዚያ በኋላ ግን "ተጠርጣሪዎቹ ይዘውት እንደነበር" መገለጹንም ለቢቢሲ ተናግራለች።
በትናንቱ የፍርድ ቤት ውሎ "ሞባይሉ ካቀረባችሁት ማስረጃ ጋር ኮዱ አይገናኝም" እንደተባለ እና የመቀለ የፖሊስ ኮሚሽነር "ከእኔ በኋላ ተቀይሮ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ትገልጻለች።
'ሁለተኛ ሞት ነው የሆነብን'
ኪሮስ ዲጂታል ማስረጃ የተባለው "ሲም ካርዱ ያለው ኮድ እና ከዚህ በፊት የዘውዱ ስልክ ነው ተብሎ እንደ ማስረጃ የቀረበው 'የሚምታታ' ስለሆነ ለማረጋገጥ የፌደራል ተቋም ማስረጃም፣ የባለሙያ ምስክርነትም እንዲያቀርብ" መባሉን ይጠቅሳል።
አክሎም "ይሄ ሳይሆን፤ አምና በቀረበው ማስረጃ ተጠርጣሪዎቹ ወንጀለኛ ተብለው ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸው፤ አሁን ግን መከላከያ አያስቀርብም ተብሎ በነጻ ተለቅቀዋል" በማለት ያስረዳል።
ኪሮስ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌደራሉ መሥሪያ ቤት "በደንብ ትብብር አልጠየቀም" ብሎ እንደሚያምን ይናገራል።
ብርቱካን በበኩሏ "ከአንድ ዓመት በኋላ ኮዱ የሚቀየርበት ምክንያት ሊኖር አይችልም" ብላ ታምናለች።
ስለ ሞባይሉ የሚያሳይ ፋይል "ጠፍቷል" ተብሎ እንደነበር ጠቅሳ፤ "ከክልል ፍርድ ቤት ነው የጠፋው ነው ያሉት። እኛ እንዴት እንደጠፋ አናውቅም፤ እኛ ሕግ አምነን ነው ያለነው" ብላለች።
ኪሮስ እንደሚለው "ተጠርጣሪዎቹ ሲም ካርዱን ዘውዴ ከመሞቷ ከወራት በፊት ከገበያ ነው የገዛነው" ብለው ተከራክረዋል።
እንደ ሕግ ባለሙያ "ከባድ ጥያቄ የሚያስነሳው ተጨማሪ ማስረጃ ሳይመጣ እና ሳይጣራ እንዲሁም ባለሙያ ሳይመጣ በተመሳሳይ ማስረጃ" የተለየ ውሳኔ መተላለፉ መሆኑን ያስረዳል።
"ተጠርጣሪዎቹን ነጻ ለማውጣት ካልሆነ ለምን ይደገማል? አምና ውሳኔ ተሰጥቶበታል። ለምን ይደገማል? ብዙ ጥያቄ ያስነሳል። በትዕዛዙ መሠረት ተጨማሪ [ማስረጃ] ባልታየበት ሁኔታ በተመሳሳይ ማስረጃ የተለየ ውሳኔ መሰጠቱ በሒደቱ ፍትሐዊነት ላይ ጥርጣሬ ያስነሳል።"
በቀጣይም ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።
ብርቱካን የትናንቱ የፍርድ ቤት ውሳኔ "ለቤተሰቡ ከባድ ጫና" መፍረጠሩን ትናገራለች።
"ሁለተኛ ሐዘን፣ ሁለተኛ ሞት ነው የሆነብን። አዲስ ሐዘን ነው የሆነብን" ብላለች።
"ለእኛ ለምንቀረው እንጂ ለሷ ምንም የሚልላት ነገር የለም። እኛ እዚህ ለምንቀረው ግን ትንሽ የአእምሮ እረፍት አግኝተን ነበር" ስትልም በሐዘን በተዋጠ ድምጽ ቤተሰቡ ያለበትን ስሜት ገልጻለች።
"አሁን ተመልሶ ነጻ ሲባሉ ቤተሰቡ ሁለተኛ ሐዘን ነው የዋለው። በጣም ነው የሚያስጠላው። [ትናንት] እንደ አዲስ ሐዘን ስናለቅስ ነበር።"
ባለፈው ዓመት የመቀለ ከተማ መካከለኛ ፍርድ ቤት የመጨረሻውን ውሳኔ ሲሰጥ የቤተሰብ አባላት ወደ ችሎት እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበር እህቷ ብርቱካን ለቢበሲ ገልጻ ነበር።
በወቅቱ በተሰጠው ብይን ቤተሰቡ "ደስተኛ እንዳልሆነም" ተናግራለች።
የተፈጸመው "የጭካኔ ግድያ በመሆኑ የሞት ፍርድ ያሰጥ ነበር" ስትልም ብርቱካን ገልጻለች።
ሃፍቱ ከተገደለች በኋላ ቤተሰቧ ለሁለት ዓመታት በቆየው የፍርድ ሒደት ሲጠብቅ የነበረው የሞት ቅጣት እንደነበር መናገሯም ይታወሳል።
ዘውዱ ተወልዳ ያደገችው በመቀለ ከተማ ማይ አንበሳ በሚባል አካባቢ ነው። ቤተሰቧ ካሏቸው ሦስት ልጆች መካከልም የበኩር ልጅ ነበረች።
የዘውዱ ግድያ ለቤተሰቦቿ ከባድ እና መሪር ሐዘንን ከማስከተሉ ባሻገር በመቀለ ከተማ እና ከዚያም ባሻገር ባለው ሕዝብ ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል።
አባቷ በጥበቃነት ተቀጥረው እናቷ ደግሞ ጠላ ጠምቀው እየሸጡ ነው ልጆቻቸውን ያሳደጉት። ዘውዱ ከሼባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች።
የዘውዱን ግድያ ተከትሎ አባቷ በሐዘን መሞታቸውን እህቷ ብርቱካን ለቢቢሲ ተናግራለች።
የትናንቱ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ቢቢሲ ያነጋገራት ብርቱካን ". . . ስቃይዋ፣ ሲጎትቷት ምን ዓይነት ስቃይ ተሰምቷት ይሆን? የሚለው አእምሮዬ ላይ ይመጣል። አገዳደሉ እንደ ቆሻሻ ነው የጣሏት። በጣም ከባድ ነው" ብላለች።