ሳዑዲ አረቢያ አምስት ተጨማሪ ኢትዮጵያውያንን በሞት ቀጣች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሳዑዲ አረቢያ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አምስት ተጨማሪ ኢትዮጵያውያንን በሞት መቅጣቱን አስታወቀ።
ወደ ሳዑዲ አረቢያ አደንዛዥ ዕጽ በድብቅ ሲያስገቡ ተይዘዋል የተባሉት ኢትዮጵያውያን በሞት የተቀጡት ሰኞ ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም. በአሲር ግዛት መሆኑን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ገልጿል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሳዑዲ መንግሥት የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር 17 ደርሷል።
ከዚህ ቀደም ሰኔ 16 አምስት፣ ሰኔ 1 አራት፣ ሚያዚያ 13/2018 ዓ.ም. ደግሞ ሦስት ኢትዮጵያውያን የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል።
የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው "የፀጥታ አካላት ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር አውለው ባደረጉት ምርመራ ጥፋቱን መፈጸማቸው በመረጋገጡ ክስ እንዲመሠረትባቸው ተደርጓል" ብሏል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ብይኑን በማጽናቱ እና በሸሪዓ ሕግ መሠረት የንጉሣዊ ትዕዛዙ ተፈጻሚ አንዲሆን መደረጉ ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ የሞት ቅጣቱ ዓላማ "የዜጎችን ደኅንነት ለመከላከል እና ነዋሪዎችን ከአደንዛዥ ዕፅ አደጋ ለመጠበቅ እንዲሁም አደንዛዥ ዕፅን ለሚያዘዋውሩ እና ለሚያስፋፉ አካላት በሕግ የተደነገጉትን እጅግ ከባድ ቅጣቶች ተፈጸሚ ማድረግ" መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ከዚህ ቀደም ሂዩማን ራይትስ ዎች ሐሚስ ሙሻይት በተባለው እስር ቤት ቢያንስ 63 ኢትዮጵያውያን ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ የሞት ቅጣት እንደተጋረጠባቸው በማስጠንቀቅ መግለጫ አውጥቶ ነበር።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ይህንን መግለጫ ካወጣ በኋላ የ14 ኢትዮጵያውያን በሞት ተቀጥተዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን በሐሚስ ሙሻይት እስር ቤት የሞት ቅጣታቸውን እየተጠባበቁ መሆኑን ዘግበዋል።
ነገር ግን ይህ ቁጥር በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በገለልተኝነት አልተረጋገጠም።
እንደ ሳዑዲ ባለሥልጣናት ገለጻ ከሆነ ኢትዮጵያውያኑ ሞት የተፈረደባቸው ሃሺሽ ይዘው በመገኘታቸው ነው።
በሂዩማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ የስደተኞችና የስደተኞች መብቶች ተመራማሪ የሆኑት ናዲያ ሃርድማን "ሳዑዲ አረቢያ አመጽ ያልተቀላቀለባቸው ወንጀሎችን ፈጽመው የተገኙ የውጭ ዜጎችን ከፍርድ በኋላ መሠረታዊ የፍትህ ሂደትን በመከልከል በሞት ለመቅጣት የላት ቁርጠኝነት ለመብቶቻቸውና ለሕይወታቸው ከፍተኛ አክብሮት አለማሳየቷን ያስረዳል" በማለት ዓለም አቀፍ አጋሮች ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች እና መንግሥት የሳዑዲ መንግሥት ለስደተኞቹ ምህረት አድርጎ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንዲፈቅድ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ስደተኞች በሚመለከት ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ሐምሌ 6 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለከታቸው አካላት ጋር "የሕግ ሂደት ላይ ያሉ እና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው" ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ "ከሚመለከታቸው" የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር "በቅርበት እየተነጋገረ" መሆኑን አስታውቋል።
በተጨማሪም ሪያድ ውስጥ በሚገኘው ኤምባሲ እና በጅዳ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት አማካኝነት "አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለገጠሟቸው የኢትዮጵያውያን ዜጎች ሰብአዊነትን ከግምት ያስገባ" እርምጃ እንዲወሰድ የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ገልጿል።
በዲፕሎማሲያዊ ቢሮዎቹ አማካኝነት ኢትዮጵያውያኑ "የቆንስላ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እና ተገቢውን መፍትሔ ለማስገኘት ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር መደበኛ ግንኙነት እና ገንቢ ውይይት" እየተካሄደ መሆኑንም ጠቅሷል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚገልጸው፤ ጥረቶች ሳዑዲ ውስጥ ፍርድ የተላለፈባቸው በአጠቃላይ 1,971 ኢትዮጵያውያን ንጉሳዊ ምሕረት እንዲያገኙ አስችለዋል። እነዚህን ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የመመለስ ተግባር መጀመሩንም በመግለጫው አንስቷል።















