ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ክልሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች እና ግጭቶች ቢያንስ 85 ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ያሰባሰበው መረጃ አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
በትግራይ ክልል ውጊያ እየተደረገባት ባለችው ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ብቻ በተለያዩ ክልሎች እና አካባቢዎች ውስጥ ጥቃት እና ግጭት ተካሂዷል። በኦሮሚያ ክልል የቀድሞው አርሲ ዞን ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት እና የሞያሌ ከተማ ግጭት በሳምንቱ ዘገባዎች ትኩረት አግኝተዋል።
ከዚህም ባሻገር ግን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በሌሎች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎችም ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቢቢሲ ያሰባሰባቸው መረጃዎች አመልክተዋል።
በሳምንቱ በርከት ብለው በታዩት ጥቃት እና ግጭቶች ቢያንስ 85 ሰዎች ተገድለዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ባለፈው ሳምንት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም ንብረት መውደሙን እና ነዋሪዎች መፈናቀላቸውም ቢቢሲ ከነዋሪዎች እና ምንጮች ያሰባሰበው መረጃ ያሳያል።
ባለፈው ሳምንት ውስጥ የሰው ሕይወት የተቀጠፈባቸው ክስተቶች በቅደም ተከተል እንዲህ ተጠናቅረዋል።
በፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ የተፈጸመው ጥቃት
ከዚህ ቀደምም ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ያስተናገደው ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ሰኞ ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም. ንጋት ላይ በታጣቂዎች በደረሰበት ጥቃት "ስምንት ሠራተኞቹ" እና የጸጥታ አካላት መገደላቸውን አንድ የአይን እማኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉላ ፊንጫ ወረዳ በሚገኘው የስኳር ፋብሪካ ላይ ጥቃት መድረሱን የተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ መንግሥቱ ኃይለማርያም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በደኅንነት ስጋት ምክንያት ማንነቱ እንዳይጠቀስ የጠየቁት የፋብሪካው ሠራተኛ፣ ታጣቂዎቹ ተኩስ የከፈቱት ወደ ፋብሪካው ከመድረሳቸው አስቀድሞ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህም "በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት" መገደላቸውን ጠቅሰዋል።
ቀጥሎ በፋብሪካ ውስጥ በተስፋፋው ጥቃት የሚሊሻ አባላትን ጨምሮ 8 የፋብሪካው ሰራተኞች መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, finchaa sugar Factory
"ሚሊሻን [ጨምሮ] አጠቃላይ የሞተው ወደ ስምንት ሰው ይሆናል። ጥቃቱ እኮ ፋብሪካው ላይ ብቻ አይደለም በሦስት አቅጣጫ ነው የጀመሩት። ሽቦ ግቢ የሚባል ሰፈር አለ። ኬላው ጋር ነው [ተኩስ] የጀመሩት፤ ፌደራል ፖሊስ ላይ [ነው]። የሞቱም አሉ የቆሰሉም አሉ" በማለት ክስተቱን አስረድተዋል።
በዚህ ጥቃት ሰራተኞች ላይ ከደረሰው ግድያ በተጨማሪ "አምስት የፋብሪካው ተሽከርካሪዎች፣ ትራንስፎርመር እና ማሽኖች መቃጠላቸው" እንዲሁም ስቶር ውስጥ የተቀመጠ ለሰራተኞች የመጣ ጫማ መዘረፉን ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት ሰኞ የተፈጸመው ይህ ጥቃት "ረገብ ያለው በድሮን ምክንያት ነው" ብለዋል።
"ወደ አራት ሰዓት ተኩል በድሮን ምክንያት ነው ትንሽ ረገብ ያለው እንጂ እነሱ ፋብሪካውን አቃጥለው ሰዎቹን አጥፍተው ሊሔዱ ነበር" ሲሉ ገልጸዋል።
ቢቢሲ የክስተቱን ዝርዝር መረጃዎች በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም። ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ መንግሥቱ፣ "ፋብሪካው በታጣቂ ኃይሎች ጉዳት ደርሶበታል" ሲሉ ማረጋገጫ ቢሰጡም፣ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አርሲ መርቲ ወረዳ
በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል መዋቅር አደረጃጀት ሥር አርሲ ዞን የሚል ስያሜ የነበረው አካባቢ የበርካቶችን ትኩረት ካገኘው የቅዳሜ ዕለቱ የሽርካ ወረዳ ጥቃት አስቀድሞ፣ ቢያንስ 14 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት አስተናግዷል።
ጥቅምት 10 ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ የደረሰው ይህ ጥቃት የተፈጸመው በመርቲ ወረዳ አንጋዳ ቀበሌ ነው። በዚህ ጥቃት ከ15 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አንድ የወረዳው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ በበኩሉ 14 ሰዎች መገደላቸውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ነዋሪው እንደሚያስረዱት በወረዳው ጎራ ሲሊንጎ በተባለው አካባቢ የተፈጸመው ጥቃት፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ቆይቷል። የቀበሌው ነዋሪዎች "ዙሪያቸውን ተከበው እና መሸሽ እንዳይችሉ ተደርገው" መገደላቸውን ተናግረዋል።
" [ታጣቂዎች] መጡባቸው፣ ዙሪያውን ከበቡ፤ መሸሽ አይችሉም፣ መውጣት አይችሉም አቅም ያለው እየሸሸ ዳነ። የፈረደበት አለቀ" በማለት የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Dhibaatada Mooyaale
ሞያሌ
የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በሚያስተዳድሯት የደቡባዊ ኢትዮጵያዋ ሞያሌ ከተማ ግጭት መቀስቀሱ የተሰማው እሑድ ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም ነው። ከክልል ባንዲራ ጋር ተያይዞ በተነሳው ውዝግብ የ13 ዓመት ልጅ መገደሏን ተከትሎ ለቀናት ወደ ዘለቀ ግጭት ተቀጣጥሏል።
ከሐሙስ ንጋት አንስቶ ደግሞ ከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መካሄድ መጀመሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህ ግጭት በሳምንቱ መጨረሻም ቀጥሎ ውሏል።
ቢቢሲ አርብ ዕለት ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ታጣቂዎችን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረው ነበር። ቢቢሲ ይህንን ቁጥር ከሌሎች ምንጮች ማረጋገጥ አልቻለም።
ሆኖም ሮይተርስ የዜና ወኪል፣ "ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች" መገደላቸውን አንድ የሞያሌ ሆስፒታል ምንጭን በመጥቀስ በዚያው ዕለት ባወጣው ዘገባ ጠቅሷል። 30 ገደማ የተጎዱ ሰዎች ወደ ጤና ተቋሙ መምጣታቸውንም ገልጿል።
በከተማዋ የተቀሰቀሰው ግጭት መንስኤ የሶማሌ ክልል "ባንዲራ ያልተገባ ቦታ ተተክሏል" መባሉ እንደሆነ በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ይህን ግጭት ተከትሎ "በከባድ መሣሪያ የታገዘ" የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ነዋሪዎች አክለዋል። በአካባቢው የነበሩ መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ መደብሮች ተቃጥለዋል ሲሉ ሦስት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቡርጂ እና ኮሬ ዞኖች የተፈጸሙት ጥቃቶች
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ሁለት ዞኖች ባለፈው ሳምንት ውስጥ በንጹኃን ላይ በደረሱ ጥቃቶች ቢያንስ 8 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በክልሉ በሚገኘው በቡርጂ ዞን ሐሙስ ጥቅምት 12/2019 ዓ.ም. እኩለ ቀን ገደማ ላይ በተፈጸመ ጥቃት "አምስት ገበሬዎች ማሳቸው ላይ ሳሉ መገደላቸውን" አንድ የዞኑ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቡርጂ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ በዞኑ በሶያማ ዙሪያ ወረዳ ነደሌ ቀበሌ በእርሻ ሥራ ላይ የነበሩ አርሶ አደሮች መገደላቸው አረጋግጧል። ጥቃቱን ያደረሱት አካላት "ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ በኩል የመጡ" እና "ጽንፈኛ" ሲል ገልጿቸዋል።
ቅዳሜ ጥቅምት 14 አጎራባች በሆነው ኮሬ ዞን ደግሞ አንድ ህጻንን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል። በሁለቱ ዞኖች ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚደርስ የገለጹት የኮሬ ዞን ጎርካ ቆሬ ቀበሌ ነዋሪ "ሕዝቡ መውጫ መግቢያ አጥቶ ነው ያለው" ብለዋል።
የተገደለው የስድስት ዓመት ልጅ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪው፣ ከአንድ ሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ገደማ ደግሞ ሁለት አርሶ አደሮች መገደላቸው አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ህጻኑ "ከሌሎች ሕጻናት ጋር ከብት እየጠበቀ ነበር፤ ጠና ጠና ያሉት በሩቁ [ታጣቂዎቹን] አይተው ሮጡ። እሱ ደግሞ መሮጥ አቃተውና እዚያው ቆሞ ቀረ።
[አብረውት የነበሩት] ግማሹ ጫካ ውስጥ ተደበቁ፤ ጩኸት አሰሙ። ከዚያ አካባቢው ላይ የነበረ ሰው ሮጦ ደረሰ። እነሱ ተረፉ እሱን ገድለው ሔዱ በጥይት የሚሞት ሕጻን አይደለም ሦስት ጥይት ነው የተኮሱበት" ሲሉ አስረድተዋል።
የኮሬ ዞን አስተዳደር ጥቃቱ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በጎርካ ወረዳ ጃሎ ቀበሌ ከብት በመጠበቅ ላይ የነበረ አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ ህፃን ልጅ እንዲሁም በቆሬ ቀበሌ በእርሻ ላይ የነበሩ ሁለት አርሶአደሮች መገደላቸውን አስታውቋል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ከጉጂ ዞን ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ "ፀረ-ሰላም ኃይሎች" መሆናቸውን ገልጿል።
ይህ ጥቃት ሰኞ ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም. ቀጥሎ፣ አሸዋ ጭኖ ወደ አማሮ ኬሌ ሲያሽከረክር የነበረ ሹፌር መገደሉን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ገልጸዋል።

አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ
በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን፣ ሽርካ ወረዳ ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ.ም. በተፈጸመው ጥቃት 46 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቢርቦ እና ጮሌ ቀበሌ ከንጋት 11 ሰዓት ገደማ ጀምሮ በተከፈተው ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል እንደገቡ ቢቢሲ ከነዋሪዎች ያገኘው መረጃ ያመላክታል።
በጥቃቱ የ75 ዓመት አዛውንት የሆኑ አባቱ የተገደሉበት አንድ ነዋሪ፣ "ሌሊት 11 ሰዓት ነው በአራት ማዕዘን ከበባ የተደረገብን። ምንም ባልተዘጋጀንበት እና በማናውቀው ሁኔታ ነው በአራቱም ማዕዘን ከበባ [ውስጥ] የጨመሩን" ሲል ሁኔታውን ገልጾታል።
ታጣቂዎቹ ጥይት እና ስለታማ መሣሪያዎችን መጠቀማቸውን የሚናገሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፣ "ቤት ውስጥ እንዳሉ፣ ሸሽተው ቤት ውስጥ ሲያመልጡ፣ ቤት ውስጥ ነው ፍጅት ያደረጓቸው። ቤት ውስጥ በር ዘግተው [ያሉትን] በር እየሰበሩ [ጥቃት ፈጽመውባቸዋል]" ብለዋል።
ከተገደሉት 46 ሰዎች ውስጥ ቢያንስ አምስቱ ህጻናት እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአይን እማኞች ገልጸዋል።
በሽርካ ወረዳ ሰዎች የተገደሉት ቢያንስ 14 ሰዎች የተገደሉበት የአጎራባቹ መርቲ ወረዳ ጥቃት በተፈጸመ በሦስት ቀናት ልዩነት ነው።

ከዚህ ጥቃት አስቀድሞ በነበረው ሳምንት በዚያው በሸርካ እና አጎራባች በሆነው ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በተፈጸሙ ተመሳሳይ ጥቃቶች ነዋሪዎች ተገድለዋል።
ከጥቅምት 2 እስከ 7/2019 ዓ .ም. ባሉት ቀናት በሁለቱ ወረዳዎች በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና ቢያንስ አምስት ሰዎች መታገታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ እና መርቲ ወረዳዎች በተፈጸመው ጥቃት በድምሩ 60 ምዕመኖቿ እንደተገደሉ አስታውቃለች።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ትላንት ሰኞ በሰጠው መግለጫ በዞኑ ጥቅምት 10 እና 14 በተፈጸመው ጥቃት በመርቲ ወረዳ 14 ምዕመናን መገደላቸውን በሸርካ ወረዳ 46 ምዕመናን "ግፍ በተሞላ ጭካኔ ተገድለው ሕይወታቸው ማለፉን" አስታውቋል።
በዚህ ጥቃት "የ20 ምዕመናን መኖሪያ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መቃጠላቸው፣ ከ 20 በላይ ወገኖቻችን ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል እንደሚገኙ" ምልአተ ጉባኤው በመግለጫው ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በሽርካ ወረዳ ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ ያደረገው "የፅምዶ አባላት" ሲል የገለጻቸውን አካላት እና "በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚንቀሳቀሰውን ሸኔ" ነው።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ፣ ጥቃቱ የተፈጸመው በሰሜን ኢትዮጵያ እርምጃ እየወሰደ ያለውን የፌደራል መንግሥት "አቅጣጫ ለማሳት" ነው ብለዋል።






























