ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ ከሥራ ቦታ፣ ከመንገድ እና ከመኖሪያ ቤት እየተካሄደው ያለው አፈሳ የፈጠረው ስጋት
- ፀሐፊ, ላየን ፅጋብ
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ትግርኛ
- ታትሟል
- የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ
የትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በትግራይ "የተመለመሉ" ወጣቶችን ለሠራዊት እያሰለጠነ መሆኑን ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጾ የምልመላው ሂደት ግን "በክልሉ መንግሥት እንደሚፈፀም" ተናግሯል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ወጣቶች ከሥራ ቦታቸው፣ ከመዝናኛ ስፍራ እንዲሁም ከሕዝብ ትራንስፖርት ላይ በግዳጅ ተወስደው ወደ ተለያዩ ካምፖች መላካቸውን ተናግረዋል።
ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ በበኩሉ የትግራይ ፀጥታ ኃይሎች በክልሉ መጠነ ሠፊ አፈሳ እና የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያካሄደ መሆናቸውን በመጥቀስ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጊቶቹ ይፈጸምባቸዋል በሚል ከዘረዘራቸው አካባቢዎች መካከል፣ ሰሜን ምሥራቅ ዞን፣ ማዕከላዊ ዞን እና ምሥራቃዊ ዞን ይገኙበታል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስ ከጦርነቱ በፊት የነበረው የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣን ከያዘ በኋላ በህወሓት መሪዎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ውጥረት ተፈጥሯል።
ተመልሶ ሥራ የጀመረው ፈርሶ የነበረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ሕጋዊ የፓርቲ ዕውቅናው የተሰረዘበትን የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤልን የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ የሾመ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ያሉበት ሁኔታ አስካሁን በይፋ አይታወቅም።
በዚህም የተነሳ በክልሉ ሌላ ዙር ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት የተፈጠረ ሲሆን፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመብት ድርጅት በመግለጫቸው አመለክተዋል።
በተጨማሪም በደብረፂዮን የሚመራው የክልሉ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ረቂቅ ሕግ ዕድሜያቸው እና የጤና ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ማንኛውም የትግራይ ተወላጆች የክልሉ መንግሥት የሚያቀርበውን "የክተት ጥሪ ተቀብሎ የመሳተፍ ብሔራዊ ግዴታ" እንዳለባቸው ይደነግጋል።
ይህንን የማይቀበል ማንኛውም ሰው "ከ10,000 እስከ 50,000 ብር ተቀጥቶ ግዴታውን እንዲፈጽም ይደረጋል" የሚል አንቀጽ በረቂቅ ሕጉ ላይ ተቀምጧል።
የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህወሓት በክልሉ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያደረገ መኾኑን በመግለጽ መግለጫዎችን አውጥተዋል።
ዓረና ትግራይ እንዲሁም ስምረት ፓርቲ ህወሓት የቀድሞ ተዋጊዎችን፣ ሚሊሻዎችን እና የትግራይ ወጣቶችን በግዳጅ ለወታደራዊ ሥልጠና በመመልመል በማፈስ ወዳልታወቁ ካምፖች እየወሰደ ነው ሲሉ ባወጡት መግለጫ ከስሰዋል።
ቢቢሲ ትግርኛ በታጣቂዎች በአስገዳጅ ለውትድርና የታፈሱ ሰዎችን፣ ከወታደራዊ ማሠልጠኛ ያመለጡ ወጣቶችን እና ቤተሰባቸውን አነጋግሯል።
ነገር ግን የአካባቢ መስተዳድሮች እና የሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤቶች ግን እየተካሄደ ያለውን ወታደራዊ አፈሳ አስተባብለዋል።
አፈሳ በወርቅ ማዕድን ማውጫ
በዓድዋ ከተማ የሚኖረው የአንዲት ልጅ አባት የሆነው ተስፋይ ገብረእግዚአብሄር በማዕከላዊ ዞን በሚገኘው አሕሰአ ወረዳ ልዩ ስሙ ዓዲፍታው በሚባል ቀበሌ በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ይተዳደራል።
በዚህ በወርቅ ማውጫ አካባቢ የተሰማሩ ወጣቶች ቀን ላይ ወርቅ ሲያወጡ ይውሉ እና ሌሊቱን በዚያው አካባቢ ትንሽ ድንኳን ዘርግተው ያድራሉ።
ግንቦት 13/2018 ዓ.ም. ከማለዳው 11፡30 ወደ ሥራቸው ለመሄድ ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ዙሪያቸውን በታጣቂዎች እና በፖሊሶች ተከብቦ 180 ወጣቶች ዓዲፍታው ወደሚባል ትምህርት ቤት ተወስደው በአንድ ክፍል ቤት ተቆልፎባቸው አደሩ።
ለደኅንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ እና ከታፈሱት ወጣቶች መካከል አንዱ በማግስቱ ግንቦት 14/2018 ዓ.ም. ሲቪል የለበሱ እና የታጠቁ ሰዎች በመምጣት "ወደ ግንባር፣ ወደ ትጥቅ ትግል እንድንሄድ እንዳፈሱን ነገሩን" ይላል።
ወጣቶቹ በሦስት አውቶብሶች ተጭነው በማዕከላዊ ዞን ነበለት አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ሰጉሕ ወደሚባል ወታደራዊ ማሠልጠኛ እንደተወሰዱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች አስረድተዋል።
ማርያም ሸዊቶ ከሚባል ቀበሌ እንደደረሱ ተስፋይ ከአፈሳው እና የሚጠብቀው ወታደራዊ ሥልጠና ለማምለጥ ከመኪና ከዘለለ በኋላ ጭንቅላቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል እንደሚገኝ ወንድሙ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ወጣቱ የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና ቢደረግለትም ተደርጎለት "እስከ አሁን ራሱን እንደሳተ ነው። መናገርም አይችልም...ሰባተኛ ቀኑ" ሲል ወንድሙ ገልጿል።
የአሕሰአ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤልያስ ገብሩ "ይህ ለራስ ፖለቲካዊ ጥቅም፣ ሕዝብ ለማደናገር እና ችግር ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር በዚያ ደረጃ የተካሄደ አፈሳ የለም" በማለት ጉዳት የደረሰበትም ሰው እንደሌለ አስተባብለዋል።
በተመሳሳይ ቀን ግንቦት 17/2018 ዓ.ም. በዓብይ ዓዲ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ሁለት የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች አባግባ እና ሩባኸዛ ከሚባሉ አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች አርሚ 60 አባላት እና ፊታቸውን የሸፈኑ ታጣቂዎች ከ700 ሰዎች በላይ ሰዎችን እንዳፈሱ ቢቢሲ ትግርኛ ከተጎጂዎች እና ከተጎጂ ቤተሰቦች መረጃ አግኝቷል።
የአራት ልጆች አባት የሆነው አቶ ሰለሞን ኃይለማርያም በዓብይ ዓዲ ከተማ ለሌሎች ሰዎች ድንጋይ እና አሸዋ በአህያ በመሸከም የቀን የጉልበት ሥራ ሠርቶ በሚያገኘው ገንዘብ ልጆቹን ያሳድግ ነበር።
ነገር ግን እንደተለመደው ለሥራ ከወጣ በኋላ ከዛ በኋላ እሱ እና የአጎቱ ልጅ ወደ ቤት ሳይመለሱ መቅረታቸውን ቤተሰቡ ለቢቢሲ ገልጿል።
ባለቤቱ ወይዘሮ መድረኽ ኪዳነማርያም "ሰኞ ዕለት ወደ ሥራ እንደሄደ ጥዋት 3፡00 ሰዓት ላይ ነው ወሰዱት።. . . የምሠራበት ቦታ መንገድ ዳር ስለሆነ በግዳጅ ታፍሰው በመኪና ሲያልፉ አየሁኝ። 'እዚህ መኪና ላይ አለ' ሲሉኝ 500 ብር ተበድሬ ስጡልኝ ብየ ሰጥኋቸው" ብላለች።
ከዚያም በኋላ ባለቤቷ ከማይቅነጣል አልፎ ወደሚገኝ ወታደራዊ ማሠልጠኛ እንደተወሰደ መረጃ እንዳገኘችም ትገልፃለች።
"በጣም ተጨንቀናል። ልጆቹ ናፍቀውታል። አባታችን እያሉ እያስቸገሩኝ ነው። ልጆቹን የሚረዳ አንድም የለም። ሰለሞንም ልጆቹን ትቶ እዚህ ውስጥ የመግባት ፍላጎት የለውም፤ በኃይል ነው የወሰዱት።"
ቢቢሲ ትግርኛ በዚህ ጉዳይ ከዓብይ ዓዲ ከተማ ከንቲባ አቶ ተኽላይ ተስፋይ እና ምክትል ከንቲባ አቶ ዘርዓይ ሐጎስ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
ዘካርያስ* ከወርቅ ማውጫ አካባቢ "ፊታቸውን በሸፈኑ ታጣቂዎች" በኃይል ከታፈሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው።
በአፈሳው ወቅት ድብደባ፣ ማንገላታት እና ተኩስ ጭምር እንደነበር የሚናገረው ዘካሪያስ ከጣንቋ አበርገለ፣ ቀይሕ ተኽሊ እና ዓብይ ዓዲ ወረዳዎች የመጡ 500 ሰዎች ወደ ዓብይ ዓዲ ከተማ ማዘጋጃ ቤት፤ ከቆላ ተምቤን የመጡ 200 ሰዎች ደግሞ በዓብይ ዓዲ ከተማ ነዳጅ ማደያ አቅራቢያ ወደሚገኘው ግንባታው ወዳላለቀ ሕንፃ በታጣቂዎቹ መወሰዳቸውን ይናገራል።
ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው ሌሎች ሰዎች ከታፈሱ በኋላ ለከተማው ፖሊስ እና ፀጥታ አካላት እንዲሁም ለዓብይ ዓዲ ከተማ እና ወረዳ አስተዳደር እንዳስረከቧቸው ይናገራሉ።
በዓብይ ዓዲ ከተማ ማዘጋጃቤት አዳራሽ የከተማዋ ከንቲባ እና ምክትሉ እንዲሁም የፀጥታ ኃላፊዎች በመምጣት 'ትዋጋላችሁ' እንዳሏቸው ጨምረው አስረድተዋል።
ከማዕድን ቁፋሮ የተያዙት ወጣቶች " 'ወድ ትግል ነው የምትሄዱት' አሉን። ልብስ ሳንለብስ ራቁታችን ነን ያለነው፣ እቃችን እና ሞባይላችን ሳንይዝ ከሥራ ላይ ነው ያፈሳችሁን፤ ልብሳችንን እንኳን እንልበስ አልናቸው። እነሱ ግን 'አያገባንም አትሄዱም አሉን" ብለዋል።
ዘካሪያስ በተለያየ ጊዜ በትግራይ ውስጥ በተካሄደ ጦርነት የቤተሰቡ አባላቱ መሰዋታቸውን ገልጾ ከተጣራ በኋላ መለቀቁን ተናግሯል።
ከዚያም በኋላ አውቶቡስ፣ ኦራል እና አይሱዙ መኪኖች አምጥተው ጭነው ወደ ሌላ ቦታ እንደወሰዷቸው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች ይናገራሉ።
የአርሚ 60 የትግራይ ኃይሎች ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ዘልዑል ማቲዮስ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ የሚመሩት ቡድን በአባግባ አካባቢ ተሰማርቶ "እርምጃ" እንደወሰደ ገልጸዋል።
"በአካባቢው ሰፊ የማዕድን ወረራ አለ። እዚያ የነበሩትን ወጣቶች 'ኦፕሬሽን' በማካሄድ በትነናቸዋል። . . . በሩባኸዛ እና በአባግባ የነበረ ወጣት ለሌላ የፀጥታ ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ስለነበር እርምጃ ወስደናል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ወጣቶቹ ማይቅነጣል እና ዕዳጋ ዓርቢ መካከል ወደሚገኘው ወታደራዊ ማሠልጠኛ እንደተወሰዱ ቤተሰቦቻቸው መናገራቸውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮሎኔሉ "... የማውቀው ነገር የለም" ሲሉ መልሰዋል።
አፈሳ ከመኖሪያ ቤት እና ከመንገድ ላይ
በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ብዙ ቀበሌዎች በሚያዝያ እና ግንቦት ወራት የትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ቤት ለቤት በመዞር በርካታ ወጣቶችን እንዳፈሱ ተጐጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአክሱም ከተማ ከመንገድ ላይ እና ከእግር ኳስ መመልከቻ ቤቶች በርካታ ወጣቶች መታፈሳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በመቀለ ከተማ በአንድ የግል ባንክ የሚሠራው የ24 ዓመቱ ወጣት ዳዊት ጉዕሽ የእረፍት ጊዜውን በአክሱም አካባቢ ከሚኖሩ ቤተሰቦቹ ጋር አሳልፎ ግንቦት 13/2018 ዓ.ም. በአውቶቡስ ወደ ሥራ ቦታው ሲመለስ በዓድዋ አካባቢ በታጣቂዎች እንደታፈሰ እህቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ታጣቂዎቹ በዕለቱ ከአክሱም- ዓድዋ- መቀለ መስመር ላይ ዳዊትን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚያልፉ መኪኖችን በማስቆም 16 ወጣቶች አፍሰው እንደወሰዱ የዐይን እማኞች አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ውቅሮ ከተማ 'ልጆቻችሁን ወይም ባሎቻችሁን ለውትድርና አሰልፉ' የሚለውን የአስተዳዳሪዎችን ቅስቀሳ ያልተቀበሉ ወደ 50 የሚጠጉ እናቶች ከግንቦት 13/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት እንደታሰሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተለይም በአግአዚ ጣቢያ (ቀበሌ) ወላጆች ስብሰባ ስላለ ወደ ቀበሌ እንድትመጡ የሚል የጥሪ ወረቀት ደርሷቸው ከሄዱ በኋላ "ልጆቻችሁ ለውትድርና አሰልፉ" እንደተባሉ ይናገራሉ።
ከታሰሩት እናቶች አንዷ የሆነችው ወይዘሮ ሃንሳ* "ይህ የሞት እና የሽረት ጉዳይ ነው። በላተኛ ኃይል እየመጣብን ስለሆነ ለትግራይ የድርሻችሁን አበርክቱ። ያልጀመረ ነው እያስጀመርን ያለነው (ከአሁን በፊት ወደ ውትድርና ያልገባ)፤ 'ልጆቻችሁን ባሎቻችሁን አሰልፉ' አሉን።
"'ለአቅመ አዳም የደረሰ ልጅ አለሽ ስለተባልሽ ልጅሽን ነው የፈለግነው!' አሉኝ። ከእኔ ጋር የለም ስላቸው 'ታመጪዋለሽ!' ብለው በአግአዚ ጣቢያ (ቀበሌ) ለስምንት ቀናት ያለ ምግብ ቆለፉብኝ።"
"'ልጆቻችሁን፣ ባሎቻችሁን አናመጣም ካላችሁ ፍተሻ መደረጉ አይቀሬ ነው' ብለውናል። ወላጅ ተጨንቋል፣ ወላጅ ተቸግሯል" ስትል እናቶች እና ሚስቶች ያሉበትን አስጨናቂ ሁኔታ አስረድታለች።
በጉዳዩ በቢቢሲ የተጠየቁት የውቅሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ገብረሚካኤል ገብረመድኅን እና የውቅሮ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረሚካኤል ተኽላይ ለቀረበው ክስ "በመሬት ላይ የሌለ ነጭ ውሸት እና የአካባቢውን ገፅታ ለማጠልሸት የሚቀርብ ነው" በማለት አስተባብለዋል።
'... የተሰጠንን እያሰለጠንን ነው'
የሰሜን ምዕራብ ዞን የሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋይ አባዲ ወጣቱ "ለመመከት" እየተዘጋጀ እንዳለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"ያለው እውነታ ጠላቶች አሁንም የተለያዩ ትንኮሳዎች እያደረጉብን ይገኛሉ። እስከ አሁን ተዘግተን በከበባ ውስጥ ነው ያለነው። ይህን እየታዘበ ያለው ወጣት እንዳይሞት፣ ራሱን መከላከል ስለላበት . . . ለመመከት ራሱን የማዘጋጀት እና የመከላከል ሥራ እየሠራ ይገኛል። 'በግድ ታፈሱ፣ ታፈኑ' የሚል ወሬ ግን. . . ሴራ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የዓድዋ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋይ ገብረሃዋርያ "በመላው ትግራይ በሌሎች አካባቢዎች እንዳለው እንቅስቃሴ ሁሉ" በከተማዋም በግድ የማፈስ ሳይሆን በማሳመን የማሰለፍ ፕሮግራም እንዳለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አፈሳ እና ማሰለፍ ይለያያሉ" ያሉት ኃላፊው "እንደ ተጋሩ አሁን በከባድ አደጋ ላይ እንገኛለን፣ መሬታችን ተወሯል፣ ሉዓላዊ ግዛታችን አልተመለሰም፣ ተፈናቃዮችም የረሃብ እና ሞት ሰላባ ሆነዋል። ስለዚህ እኛ ሉዓላዊነታችን ማስከበር አለብን። የአካባቢውን ፀጥታ ለመጠበቅ ወጣቱን አሳምነን እናስገባዋለን፤ ወደ ሠራዊት የሚገባ ከሆነ ወታደራዊ ሥልጠና የሚያስፈልገው ከሆነ ሊወስድ ይችላል" ብለዋል።
የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በትግራይ "ተመልምለው ለመጡ ወጣቶች" ወታደራዊ ሥልጠና እየሰጠ እንዳለና የምልመላው ሂደት ግን "በትግራይ መንግሥት እንደሚፈፀም" ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግሯል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ጄነራል ፍስሃ ኪዳኑ (ፍስሃ ማንጁስ) ጥያቄ አቅርቦላቸው የነበረ ሲሆን፣ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መብራህቱ ኃይሉ በጄነራሉ ፈንታ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ መብራህቱ "የሠራዊት ምልመላ የኛ ሥራ አይደለም። አሁን ከተቋቋመው መንግሥት ጋር ተነጋገሩ። የትግራይ መንግሥት ነው መልምሎ የሚሰጠን። እኛ መልምለው የሰጡንን ነው እያሰለጠንን እና እያበቃን ያለነው። [ወጣቱ] በምን ዓይነት ሂደት ነው ወደ ወታደራዊ ሥልጠና እየመጣ ያለው አናውቅም። ሂደቱ እንዴት እያካሄዱት እንዳለ ራሳቸው ይመልሱት" በማለት ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራ አዲስ 'ማዕከላዊ ዕዝ' አሁን በትግራይ ክልል እየተፈጸመ ያለውን ወጣቶችን በአስገዳጅ ወደ ውትድርና የማሰለፍ ዘመቻ እየመራው እንደሚገኝ ቢቢሲ ከምንጮቹ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቢቢሲ ትግርኛ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል እና ምክትላቸው አማኑኤል አሰፋን በቀጥታ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። በተለያዩ የመልዕክት ማስተላለፊያ መንገዶች ለቀረበላቸው ጥያቄም መልስ አልሰጡም።
*ለተጎጂዎች ደህንነት ሲባል አንዳንድ ስሞች ተቀይረዋል