ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በካናዳ የአሜሪካ ቆንስላ ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ጥቃት ተፈጸመ
በካናዳ፣ ቶሮንቶ በሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በተከፈተው ተኩስ ላይ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው።
ክስተቱ ያጋጠመው ሰኞ ጠዋት ሲሆን ከቆንስላው ውጭ የነበረ የፖሊስ መኮንን አንድ ጊዜ ተኩስ መስማቱን እና ታርጋ የሌላት ነጭ መኪና ከአካባቢው ስትሸሽ መመልከቱን ገልጿል።
ፖሊስ መኪናዋን በፈጣን መኪና ለመከታተል ሞክሮ ነበር። ሆኖም በአደጋ ስጋት ምክንያት ክትትሉን አቋርጧል።
እስካሁን ከክስተቱ ጋር በተያያዘ የተገለጸ ጉዳት የለም። በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተሳተፉም ግልጽ አይደለም።
ሰኞ ዕለት የተከፈተው ተኩስ ያጋጠመው የቶሮንቶ ፖሊስ መጋቢት ላይ ካጋጠመው ተመሳሳይ ክስተት ጋር ተያይዞ ሦስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ነው።
ፖሊስ አሁን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ከሮያል ፖሊስ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕግ አስፈፃሚ አጋራት ጋር በመሆን እየመረመረ እንደሆነ ገልጿል።
የሮያል ፖሊስ ክስተቱን " ሌላ አስጨናቂ አደጋ" ያለው ሲሆን የከተማዋ ከንቲባ ኦሊቪያ ቾውም "አሳፋሪ" ብለውታል።
" ጥቃቱን ለፈፀመው ግለሰብ ወይም ለፈፀሙት ግለሰቦች እናገኛችኋለን ማለት እፈልጋለሁ" ብለዋል ከንቲባው።
ጥቃቱ ሲፈፀም በቆንስላው ውስጥ ቢያንስ ሁለት ግለሰቦች ነበሩ ተብሏል።
የቶሮንቶ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ፍራንክ ባሬዶ፣ " ሕንፃው በጣም ጠንካራ ስለሆነ" ውስጥ የነበሩ ሰዎች ተኩሱን ላይሰሙት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ባሬዶ በክስተቱ ላይ ምርመራ እየተካሄደ እና በከተማዋ ያሉ ፖሊሶች ተጠርጣሪዎችን እያሰሱ እንደሆነ ገልጸዋል።
" እነዚህን ሰዎች ለሕግ እናቀርባለን" ብለዋል።
በቶሮንቶ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላም በኤክስ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ ፖሊስ ለሰጠው ምላሽ ምስጋናውን አቅርቧል።
የቶሮንቶ ፖሊስ 'አል ሳዲ' የተባለ ቡድን የምርመራው አካል እንደሆነ ያለው ነገር የለም። አሁን ላይ በቆንስላው ላይ የተፈፀመው ጥቃት ምክንያት ምን እንደሆነም አልገለፀም።
ባለፈው መጋቢት ላይ ፖሊስ "ብሔራዊ የደኅንነት አደጋ" ሲል ከገለጸው ከቆንስላው ውጭ የተከፈተ ተኩስ በኋላ በአካባቢው የፀጥታ አባላትን አስፍሯል።
ሰኔ ላይም ፖሊስ ከተኩሱ ጋር በተገናኘ አሰሳ ያካሄደ ሲሆን በዘመቻው ወቅት የ43 ዓመቱ የፖሊስ መኮንን ማርክ ፒኒዞቶ ተገድሏል።
ፖሊስ፣ የመጋቢቱን ጥቃት ጨምሮ ከተኩሱ ጋር በተያያዘ 18 እና 19 ዓመት የሆናቸው በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የሁለት አይሁዳውያን ዳቦና ኬክ መጋገሪያ ቤቶች ዒላማ የሆኑ ሲሆን ፖሊስ ከሰኞ ዕለቱ የቆንስላው ጥቃት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ገልጿል።
የኦንታሪዮ ግዛት አስተዳዳሪ ዶግ ፎርድ " ባለፉት ቀናት በቶሮንቶ በተፈፀሙት ጥቃቶች አዝኛለሁ" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ በበኩላቸው "ምርመራ እየተካሄደ ነው፤ ሕግ ማስከበር ሙሉ ኃላፊነቴ ነው። ይህን ያደረጉ አካላት ተጠያቂ ይደረጋሉ" ብለዋል።