የሰርቢያው አንጋፋ መሪ ቩቺች በተማሪዎች የአመጽ እንቅስቃሴ በመሸነፋቸው የአገሪቱ ዜጎች ደስታቸውን እየገለፁ ነው
ሰርቢያን ለረጅም ጊዜ የመሩት አሌክሳንደር ቩቺች የተማሪዎችን የተቃውሞ ንቅናቄ ተከትሎ በድንገተኛ የፓርላማ ምርጫ መሸነፋቸውን አምነው ተቀበሉ።
“የመጨረሻውን ውጤት እስካሁን ባይደርሰንም በምርጫው መሸነፋችን ግን ግልጽ ነው” ሲሉ የቀኝ ዘመሙ ሕዝበኛ መሪ እሁድ ምሽት ሽንፈታቸውን ተቀብለዋል።
የሰርቢያ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ያደረጋቸው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቶች፣ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የመራጮች ተሳትፎ እንደነበረ አመልክተዋል።
ቩቺች ሽንፈታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በሰርቢያ በርካታ አካባቢዎች ሰዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልፀዋል።
ቩቺች ድንገተኛ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት በኖቪ ሳድ ከተማ የባቡር ጣቢያ ጣሪያ ወድቆ 16 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ለሁለት ዓመታት የቀጠሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከተካሄዱ በኋላ ነው።
የባቡር ጣቢያው አደጋ በሰርቢያ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና እና የቸልተኝነት ምልክት ተደርጎ በመታየቱ ነው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው።
የሰርቢያ ፕሮግሬሲቭ ፓርቲ መሪው ቩቺች፣ ለሁለት የፕሬዚደንትነት ዘመናት ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደር የማይችሉ በመሆኑ፣ እአአ ከ2017 ጀምሮ ወደለቀቁት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የመመለስ ዓላማ ነበራቸው።
የተማሪዎችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ የተመሰረተው እና ምርጫውን ያሸነፈው የ’ስቱደንት ሊስት’ መሪ ኢሊያ ስርዳኖቪች “ነጻ መንግሥት ይመሰረታል” ሲሉ ለቢቢሲ ሰርቢያ ተናግረዋል።
በመላው ሰርቢያ የሚገኙ የመንግሥት ተቃዋሚ መራጮችን ያሰባሰበው የፀረ ሙስና ንቅናቄ “አገሪቱን ከግፍና ከጭቆ እና አገዛዝ ነጻ ያወጣል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።