ትራምፕ የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ወደ ፓኪስታን የሚያደርጉትን ጉዞ ሰረዙ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ዶናልድ ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር ወደ ፓኪስታን ለውይይት እንደማይሄዱ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ "ሁሉም አማራጮች አሉን፤ በፈለጉት ጊዜ ሊደውሉልን ይችላሉ፤ ነገር ግን ምንም ነገር ላለመነጋገር ተጨማሪ የ18 ሰዓት በረራ አያደርጉም።" ብለዋል።
የፎክስ ኒውስ የዋይት ሐውስ ዘጋቢ ፕሬዚዳንት ትራምፕ "ሰዎቼን ነገርያቸዋለሁ፤ ከጥቂት ሰዓት በፊት ለመሄድ እየተዘጋጁ ነበር እና 'አይሆንም ወደዚያ ለመሄድ የ18 ሰዓት በረራ አታደርጉም' ብያቸዋለሁ” ማለታቸውን ጠቅሷል።
ትራምፕ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ የልዑካን ቡድኑን ጉዞ መሰረዛቸውን አረጋግጠዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የአሜሪካ ልዑካን ወደ ኢዝላማባድ የሚያደርጉትን ጉዞ የሰረዙት ”በጉዞ ብዙ ሰዓት ነው የሚጠፋው፤ ብዙ ሥራ ነው” በማለት ነው።
“ወኪሎቼ ወደ ፓኪስታን ኢዝላማባድ ኢራናውያንን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጉዞ ሰርዣለሁ።”
“ከዚህም በተጨማሪ በአመራሩ መካከል ከፍተኛ ክፍፍል እና ግራ መጋባት አለ። ማንም መሪው ማን እንደሆነ አያውቅም። እነርሱን ጨምሮ።
በተጨማሪም ሁሉም አማራጭ አለን። እነርሱ ግን ምንም የላቸውም! መነጋገር ከፈለጉ ማድረግ ያለባቸው መደወል ብቻ ነው!!!’’ ብለዋል



















