አሜሪካ እና ኢራን በአጸፋ በወሰዱት እርምጃ በርካታ መርከቦችን መምታታቸውን አስታወቁ

አሜሪካ እና ኢራን ቅዳሜ ዕለት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ በሚንቀሳቀሱ በመርከቦች ላይ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን አስታወቁ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ከአሜሪካ ጋር የሚኖረው “የጨዋታው ሕግ ተቀይሯል፤ የተመጣጠነ ምላሽ ዘመን አብቅቷል” - ኢራን

    መሐመድ ባገር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, Tabnak

    የምስሉ መግለጫ, አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ

    ኢራን ከአሜሪካ በኩል ለሚሰነዘርባት ጥቃት የምትሰጠው ተመጣጣኝ የአጸፋ ምላሽ ማብቃቱን እና ለሚፈጸምባት ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ ከባድ እንደሚሆን በኢራን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ተናገሩ።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ እና ዋነኛ ተደራዳሪ ጋሊባፍ ፓርላማ ውስጥ ሲናገሩ፣ በአገራቸው ላይ ለሚፈጸም ጥቃት “የተመጣጠነ ምላሽ ዘመን እንዳበቃ እና የጨዋታው ሕግ እንደተቀየረ” ገልጸዋል።

    መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ባደረጉት ንግግር፣ ኢራን “ከጠቃላይ የከሐዲያን ግንባር" ጋር ሁሉን አቀፍ ጦርነት ውስጥ ናት ብለዋል።

    ጨምረውም “ወታደራዊ ኃይሎቻችን በአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ በፈጸሙት ከባድ ጥቃቶች፣ የጠላት መሪዎች ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ገብተዋል፤ ከንቱ ቃላት እና መፈክሮችን በመጠቀም በጦር ሜዳ የተፈጠሩ መስለው የሚታዩ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት እያመረቱ ነው" ሲሉ ከስሰዋል።

    ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር የኢራን ዋና ተወካይ የሆኑት ጋሊባፍ፣ “አሁን አሜሪካውያን የተመጣጠነ ምላሽ ዘመን እንዳበቃ ሊረዱ ይገባል። በቅርቡ በጠላት ጦር ሰፈር ላይ ባካሄድነው ዘመቻ የፈጸምናቸው ጥቃቶች የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች ብቻ ናቸው” ብለዋል።

    "እስካሁን ካልተረዱ፣ ከመዘግየቱ በፊት ሊገነዘቡ ይገባል፤ የጨዋታው ሕግ ተቀይሯል። ከአሁን በኋላ በኢራን ጥቅም እና ደኅንነት ላይ የሚደረግ ማንኛውም ጥሰት ፈጣን፣ ከባድ እና የበለጠ አውዳሚ ምላሽ ያስከትላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  2. ኢራን አሜሪካ የጣለችባት ዕገዳ የበለጠ የሚጎዳው ዋሽንግተንን ነው አለች

    ቴህራን ውስጥ የሚታይ ትራምፕ የተሳሉበት ፖስተር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሃ ውስጥ ሰምጠው የሚያሳይ ግዙፍ ፖስተር ቴህራን ውስጥ

    አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችው የኢኮኖሚ እና የባሕር እንቅስቃሴ እገዳ በመጨረሻ ከኢራን ይልቅ ዋሽንግተንን በብዙ እጥፍ እንደሚጎዳት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዛሬ እሁድ ገለጸ።

    “አሜሪካ በኢራን ላይ የአንድ ዶላር የኢኮኖሚ ጉዳት ለማድረስ ስትነሳ፣ ራሷ በርካታ ዶላሮች ወጪ እና ኪሳራ ይደርስባታል” ሲሉ የአብዮታዊ ዘቡ ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጄነራል ሆሴይን ሞሂቢ መሄር ለተባለው የኢራን ዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በወታደራዊ ኃይሏ፣ በባሕር ኃይሏ እና በአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦቿ ታግዛ ኢራንን ማሸነፍ እንደምትችል አስባ ነበር። ነገር ግን ኢራን ለማዕቀብ እና ለጫና እንደማትሸነፍ በማሳየት የአሜሪካ ግምት የተሳሳተ መሆኑን አሳይታለች ብለዋል።

    ሞሂቢ አሜሪካ ከፍተኛ ዕዳ ተሸክማ እያለች ከቻይና እና ከሌሎች አገራት ጋር በኢኮኖሚ ውድድር ውስጥ በመሆኗ፣ ኢራንን “በኢኮኖሚ ጦርነት” ድል ማድረግ እንደሚከብዳት ተናግረዋል።

    በተጨማሪም በቀጣናው የተፈጠረው ሁኔታ በአሜሪካ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ላይ ጫና እያሳደሩ እንደሆነ እና የአሉሚኒየም ምርት ወደ ውጭ መላክን ጨምሮ የአንዳንድ ጥሬ እቃዎችን አቅርቦት እንደተጎዱ ገልጸዋል።

    እነዚህ ክስተቶች የኢኮኖሚ ጫና እና እገዳ ሁልጊዜ ድልን እንደማያረጋግጡ እንዲሁም ዕቀባውን በሚያስፈጽመው አገር ላይም ከፍተኛ ወጪ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ያሳያሉ ብለዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት እነዚህን ማዕቀቦች እና በባሕር ንግድ ላይ የተጣሉ ገደቦችን “የኢኮኖሚ ጦርነት” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

  3. የአውሮፓ አገራት የወርቅ ክምችታቸውን ከአሜሪካ እያስወጡ ነው

    ወርቅ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዚህ ሳምንት ከሰሜን አሜሪካ በቶኖች የሚቆጠር ከፍተኛ የወርቅ ክምችቱን ማስወጣቱን ያረጋገጠው የኔዘርላንድስ ማዕከላዊ ባንክ፣ ይህንን እርምጃ የወሰደው ከባድ ቀውሶች በሚከሰቱበት ጊዜ "የተሻለ ተዘጋጅቶ ለመጠብቅ" መሆኑን ገልጿል።

    በአሜሪካ እና ካናዳ ከሚገኘው የኔዘርላንድስ በድምሩ 313 ቶን የሆነ የወርቅ ክምችት ውስጥ 86 ቶኑ ወደ ለንደን ተዘዋውሯል። ባንኩ እንደገለጸው፣ ይህ የተደረገው "በዓለም የፖለቲካ ውጥረት መጨመርን ከግምት ውስጥ በማስገባት" ሲሆን፣ ከአሜሪካ እንዲወጣ የተደረገው ወርቅም "ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ በፍጥነት ለመጠቀም አመቺ እንዲሆን" ነው ተብሏል።

    ነገር ግን እርምጃው ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል። የኔዘርላንድስ መንግሥት ይህን ለምን አደረገ? በቅርቡ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ይከሰታል ብሎ እየጠበቀ ነውን? ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ የአውሮፓ አገራት የወርቅ ክምችታቸውን ከአሜሪካ እና ከካናዳ እያስወጡ ያሉት ለምንድን ነው?

  4. በኢንዶኔዥያ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት የአውሮፕላን በረራ ተቋረጠ

    በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዟቸው ተስተጓጉሏል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዟቸው ተስተጓጉሏል

    በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት በኢንዶኔዥያ ዋነኛ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአውሮፕላን በረራዎች ተሰረዙ።

    በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዟቸው ተስተጓጉሏል።

    አንክ ክራካቶ ከተባለው ተራራ በሚወጣው አመድ ምክንያት 209 በረራዎች መሰረዛቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    አመዱ በዋና ከተማዋ ጃካርታ ሱካርኖ ሀታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ተስተውሏል።

    እሳተ ገሞራው መፈንዳት የጀመረው አርብ ዕለት ነው። የእሳት ግግር ከተራራው እየወጣ ሲሆን ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽም በአካባቢው ተሰምቷል።

    ዛሬ እሑድ ሁለት ተጨማሪ ፍንዳታዎች ተከስተዋል።

    በረራዎች በመሰረዛቸው ከ22,000 በላይ ሰዎች መጓጓዝ አልቻሉም።

    የአገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስቴር እንዳለው በዋነኛነት ወደ ሲንጋፖር የሚደረጉ በረራዎች ተሰርዘዋል። ወደ ኳታር-ዶሃ፣ አውስትራሊያ-ሲድኒ እና ማሌዢያ-ኩዋላ ላምፑር የሚጓዙ አውሮፕላኖችም በረራ አቋርጠዋል።

    የኢንዶኔዥያ ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ እና የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ አሳስቧል።

  5. የኢራን አብዮታዊ ዘብ የአሜሪካን ሰርጓጅ መርከብ መምታቱን አስታወቀ

    መርከቦች በሆርሙዝ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል፣ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚንቀሳቀስ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰርጓጅ መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ።

    የኢራን የዜና ወኪሎች እንደዘገቡት፣ አብዮታዊ ዘቡ ባወጠው መግለጫ ሰርጓጅ መርከቡ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ወደሚገኝ “የተከለከለ ቀጣና” ለመግባት ሞክሮ ነበር ብለዋል።

    ቀደም ሲል ቅዳሜ ምሽት ላይ፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ “ፈቃድ ባልተሰጣቸው መስመሮች” ላይ እየተጓዙ የነበሩ ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ ሦስት የአሜሪካ መርከቦችን ዒላማ ማድረጉን ገልጿል።

    ይህም የተፈጸመው የአሜሪካ ኃይሎች በሦስት የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ምላሽ መሆኑን አስታውቋል። አሜሪካ እስካሁን ስለጥቃቶቹ አስተያየት አልሰጠችም።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቅዳሜ ጠዋት ባወጣው መግለጫ፣ የአሜሪካ ኃይሎች ሦስት የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማጥቃታቸውን ገልጿል።

    ከእነዚህም አንዱ የተመታው የኢራን ነዳጅ ለውጭ ገበያ የሚላክበት ዋነኛ ማዕከል በሆነው የኻርግ ደሴት ዳርቻ አካባቢ እንደነበር ገልጿል።

  6. አሜሪካ እና ኢራን በአጸፋ በወሰዱት እርምጃ በርካታ መርከቦችን መምታታቸውን አስታወቁ

    የአሜሪካ ጦር ያወጣው በአንደኛው የኢራን መርከብ ላይ የተፈጸመን ጥቃት የሚያሳይ ምሥል

    የፎቶው ባለመብት, Centcom

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ጦር ያወጣው በአንደኛው የኢራን መርከብ ላይ የተፈጸመን ጥቃት የሚያሳይ ምሥል

    አሜሪካ እና ኢራን ቅዳሜ ዕለት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን አስታወቁ።

    የአሜሪካ ጦር ከኢራን ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን "በዘላቂነት ከጥቅም ውጪ ማድረጉን" ገልጿል፤ ከእነዚህም አንዱ በኻርግ ደሴት አቅራቢያ የነበረ ሲሆን ሦስተኛውን በኦማን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ "ሙሉ በሙሉ ማውደሙን" አስታውቋል።

    የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ጥቃቶቹን አረጋግጦ፣ ቴህራን በምላሹ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሦስት መርከቦች ላይ እንዲሁም በሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ “ባልተፈቀደ መስመር” ላይ ይጓዙ ነበር ባለቻቸው ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አሳውቋል።

    ኢራን አዲስ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟ የተሰማው፣ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “ቀላል ነው፤ ኢራን በአሜሪካ መርከቦች ላይ ከተኮሰች፣ እኛ የእሷን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እናወድማለን (እናሰጥማቸዋለን)” ብለው ከጻፉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነበር።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እንዳስታወቀው አሜሪካ ሦስቱ ከኢራን ጋር የተገናኙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት ከመፈጸሟ በፊት ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች በኢራን ዒላማ ተደርገው ነበር።

    ማዕከላዊ ዕዙ ጨምሮም በዚያው ቀን መጀመሪያ ላይ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኃይል የሰነዘራቸው በርካታ ጥቃቶችን “በተሳካ ሁኔታ ማስወገዱን” ገልጿል።

    ጥቃቶቹ አንድ የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብን እና የሚሳዔሎች መከላከያ አውዳሚ መርከብን ዒላማ አድርገው የነበረ ሲሆን፣ በጥቃቶቹ በአሜሪካዊ ወታደሮች ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ አስታውቋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ የአሜሪካ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጠረው ሴንተኮም፣ የተመቱት ሦስቱ የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች “የኢራን አብዮታዊ ዘብን እና በቀጣናው ያሉ ቡድኖቹን በገንዘብ የሚደግፍ ብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስባቸው ድብቅ መረብ አካል ናቸው” ሲል ገልጿል።

    የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ተቋም ኢሪብ እንደዘገበው፣ ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ በኻርግ ደሴት አቅራቢያ በነበረ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ በፈጸመችው ጥቃት የሞተ ወይም የተጎዳ ሰው የለም።

    ኻርግ ደሴት ኢራን የነዳጅ ምርቷን የምትልክበት ማዕከል ሲሆን፣ የአገሪቱ 90 በመቶ ያህል ድፍድፍ ነዳጅ በቧንቧዎች ተጓጉዞ በዚህ ደሴት በኩል ወደ ውጭ ይላካል።

    በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የነበሩ መርከበኞች በነፍስ አድን ጀልባዎች ወደ ባሕር ዳርቻ መወሰዳቸው ተዘግቧል። ከእነዚህ መርከቦች አንዱ ምንም ጭነት ያልያዘ ሲሆን፣ ሌላኛው ነዳጅ ጭኖ እንደነበር ተገልጿል።

    ከሰዓታት በኋላ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአካባቢው በነበሩ ስድስት መርከቦች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሙን ኢሪብ ዘግቧል። እነዚህም በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የነበሩ ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እና “ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው” የተባሉ ሌሎች ሦስት መርከቦች ናቸው።

    እንደ ዘገባው፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሦስቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “ያልተፈቀዱ መስመሮችን” ሲጠቀሙ እንደነበር ገልጾ፣ ሌሎች መርከቦችም እንዲህ እንዳያደርጉ አስጠንቅቋል።

  7. አሜሪካ የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከብን በሚሳዔል መምታቷ ተዘገበ

    ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንቅስቃሴ ተገትቷል

    ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት አሜሪካ ከኢራን ኻርግ ደሴት አቅራቢያ በፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከብ መመታቱን የቴህራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    በሚሳዔል ተመትቷል የተባለው የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከብ “አነስተኛ” መሆኑን እና በጥቃቱ በሰው ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ አንድ የኢራን ዜና ወኪል ዘግቧል።

    ኻርግ ደሴት ኢራን ወደ ውጭ ለምትልከው ነዳጅ እጅግ ወሳኝ የማስተላለፊያ ስፍራ ሲሆን፣ ከምትልከው ድፍድፍ ነዳጅ ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆነው በዚህ ደሴት በኩል ያልፋል።

    አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ከጀመረች ወዲህ በተደጋጋሚ በደሴቱ ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ወሳኙን ደሴት ለመቆጣጠር ሲዝቱ ቆይተዋል።

    ኢራን የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ ምርት በሚያልፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ክልከላ ጥላ ትዕዛዟን በማያከብሩ መርከቦች ላይ እርምጃ ስትወስድ ቆይታለች።

    አሁንም የትኛውም መርከብ ከኢራን ፈቃድ በማግኘት በተፈቀደው መስመር ብቻ እንዲያልፍ ያዘዘች ሲሆን፣ በወሽመጡ ላይ በተጠመዱ አደገኛ ፈንጂዎች እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የባሕር ላይ እንቅስቃሴው ተስተጓጉሏል።

    አሜሪካም በበኩሏ ከኢራን ወደቦች እና ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ የመርከብ ጉዞዎች ላይ ዕቀባ ጥላ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ከልክላለች።

  8. የትራምፕ ልዑካን ሩሲያ እና ዩክሬንን ለማስማማት አዲስ ጥረት ጀመሩ

    ጃሬድ ኩሽነር እና ስቲቭ ዊትኮፍ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ቅዳሜ እና እሁድ ወደ ሞስኮ እና ኪየቭ የሚሄዱት የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር (ግራ) እና የፕሬዝዳቱ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ (ቀኝ)

    የአሜሪካ አደራዳሪዎች ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚደረገውን ጦርነት እንዲቋጭ የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን ቅዳሜ እና እሁድ ለጉብኝት ወደ ሁለቱ አገራት ሊጓዙ ነው።

    ልዑካኑ ቅዳሜ በሞስኮ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ወደ ኪዬቭ በማቅናት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር እሁድ ዕለት ጋር እንደሚገናኙ ተረጋግጧል።

    ትራምፕ ስለ ልካኖቸቻው ጉብኝት ሲጠየቁ “ጦርነቱን ለማቆም የቀረበ ሀሳብ ይዘው ሄደዋል” ብለዋል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መልዕክተኞች ስቲቭ ዊትኮፍ እና እና ጃሬድ ኩሽነር፣ ከዚህ ቀደም ሩሲያን ብዙ ጊዜ ጎብኝተዋል። በዩክሬን የሚያደረጉት ውይይት ግን የመጀመሪያው ይሆናል።

    ዜሌንስኪ በልዑካኑ ጉብኝት ወቅት የሩሲያ አየር ክልል ደኅንነት እንደሚጠበቅ ዋስትና ሰጥተው፣ ሩሲያም በተመሳሳይ መንገድ ለዩክሬን እንድታደርግ ጠይቀዋል።

    የሩሲያ መንግሥታዊ ዜና ወኪል ታስ አንድን ምንጭ ጠቅሶ፣ ዊትኮፍ እና ኩሽነር ቅዳሜ እና እሁድ ወደ ሞስኮ እና ኪየቭ ይጓዛሉ ብሏል።

    የፕሬዝዳንት ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔሽኮቭ “አሁን ምንም መግለጫ አላቀርብም፤ እነዚህ ግንኙነቶች ሲካሄዱ ግን መረጃ እንሰጣለን” ብለዋል።

    በሌላ በኩል ፑቲን ሐሙስ ዕለት በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር “የሰላም ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድል አለ” ነገር ግን “መጀመሪያ ሞስኮ እና ኪየቭ እርስ በርሳቸው መስማማት አለባቸው” ብለዋል።

    ሆኖም ግን ፑቲን ዩክሬን ተጨማሪ ግዛት ለሩሲያ እንድትለቅ ያላቸውን ፍላጎት እንደማይተዉ አሳይተዋል።

    የፑቲንን ቅድመ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርጉ የቆዩት ዩክሬን እና የአውሮፓ አጋሮቿ፣ የሩሲያ ፍላጎትን መቀበል እጅ መስጠት ነው ይላሉ።

    ሩሲያ ከአራት ዓመት በፊት ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከከፈተች በኋላ በአሁኑ ጊዜ ከዩክሬን ግዛት 20 በመቶ ያህሉን በቁጥጥሯ ስር አድርጋለች።

  9. አሜሪካ ለሳዑዲ አረቢያ የ5 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ሽያጭ አጸደቀች

    የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ቢን ሰልማን እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ቢን ሰልማን እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሳዑዲ አረቢያ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወታደራዊ መሣሪያዎች ለመሸጥ የቀረበው ስምምነት መጽደቁን አስታወቀ።

    ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ ሳዑዲ አረቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ቦምቦችን እና የረጅም ርቀት ሚሳዔሎች መምሪያ ሥርዓቶችን ለመግዛት ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ጸድቋል።

    ከጦር መሣሪያዎቹ በተጨማሪ ስምምነቱ “ደጋፊ መሣሪያዎችን፣ ተተኪ ክፍሎችን፣ መለዋወጫዎችን እንዲሁም የቴክኒክ፣ የምህንድስና እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ አገልግሎቶችን” እንደሚያካትት ተገልጿል።

    አሜሪካ ይህን ስምምነት “የቁልፍ አጋር አገርን ደኅንነት የሚያጠናክር” እና “በፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የፖለቲካ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ እድገትን የሚደግፍ ነው” በማለት ገልጸዋል።

    መግለጫው በተጨማሪም፣ ስምምነቱ “ሳዑዲ አረቢያ በቀጣናው የሚፈጠሩ ወቅታዊ ስጋቶችን ለመቋቋም ያላትን የአየር መከላከያ አቅም ያጠናክራል” ሲልም አብራርቷል።

  10. አሜሪካ እና አጋሮቿ የኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ለተመድ ፀጥታው ምክር ቤት እንዲቀርብ እንቅስቃሴ ጀመሩ

    ቴህራን

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የኢራን የኒውክሌር ጉዳይ በተባበሩት መንግሥተት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲታይ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ጀመሩ።

    አገራቱ ቴህራን የኒውክሌርን መስፋፋትን ለመከላከል መፈጸም የነበረባትን ግዴታዎች ስላልተወጣች ጉዳዩ ወደ ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲመራ የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ረቂቅ ለድርጅቱ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም የበላይ ቦርድ ለማቅረብ መዘጋጀታቸው ተዘግቧል።

    ኢራን በበኩሏ አሜሪካ እና ሦስቱ አገራት የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ የሚያደርጉትን ጥረት “የተስፋ መቁረጥ ሙከራ” ስትል አጣጥላዋለች።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ከደረሰ፣ ከ20 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢራን በዚህ ሂደት በምክር ቤቱ የምትቀርብበት ክስተት ይሆናል።

    በዓለም አቀፉ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መስፋፋትን መከላከያ ስምምነት መሠረት፣ ኢራን ሁሉንም የኒውክሌር ቁሶቿን እና እንቅስቃሴዎቿን ይፋ የማድረግ ግዴታ አለባት።

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ተቆጣጣሪዎችንም የትኛውም የኒውክሌር ቁስ ለሰላማዊ ጥቅም ከሚውልበት ሁኔታ ውጪ እንዳልተቀየረ እንዲያረጋግጡ የመፍቀድ ሕጋዊ ግዴታም ተጥሎባታል።

    አሁኑ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ ካለፈው ዓመት ሰኔ አስቶ ሊወሰድ ሲታሰብ የነበረ መሆኑን አሶሺዬትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ቦርድ በወቅቱ ባደረገው ግምገማ ኢራን የኒውክሌር መስፋፋት መከላከያ ግዴታዎቿን አላከበረችም ከ20 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ፈርጇት ነበር።

    ይህ ውሳኔ የተላለፈው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸው አንድ ቀን አስቀድሞ ነበር። በዚህ ጥቃት የኢራን ዩራኒየም ማበልጸጊያ ጣቢያዎች ወድመዋል ወይም ክፉኛ ተጎድተዋል።

    የኢራን ኒውክሌር እንቅስቃሴ ወደ ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የሚመራ ከሆነ፣ ጉዳዩ እንደ ማዕቀብ መጣል ወይም የሀብት ማገድ ያሉ አስገዳጅ ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ በሚችለው አካል እጅ እንዲሆን ያደርጋል።

    ይሁን እንጂ የኢራን አጋር የሆኑት ሩሲያ እና ቻይና በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ስላላቸው እንዲህ ዓይነቱ የቅጣት እርምጃ የመወሰድ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው።

    የውሳኔ ሀሳቡ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ “ይህንን የውሳኔ ሃሳብ እና ቀደም ሲል የጸደቁትን ውሳኔዎችን… ለሁሉም ተቋሙ አባላት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እና ለጠቅላይ ጉባኤው እንዲያስተላልፉ” እንደሚጠይቅ ኤፒ ዘግቧል።

    በቪየና የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢራን ቋሚ ተልዕኮ ግን የአራቱ አገራት እርምጃን “የተስፋ መቁረጥ ሙከራ” ሲል ገልጾታል። አገራቱ የኢራንን የኒውክሌር ጉዳይ “በኒው ዮርክ ወደሚገኘው የፀጥታው ምክር ቤት ለመምራት ማሰባቸውን” ተልዕኮው በኤክስ ገጹ ባሰፈረው ፅሁፍ ገልጿል።

    ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከዚህ ቀደምም ተሞክሮ እንደነበር የጠቀሰው ተልዕኮው “ይህ አዲሱ እርምጃም ምንም ዓይነት ጥቅም አያስገኝላቸውም” ብሏል።

  11. በኔፓል የጎርፍ አደጋ ለዘጠኝ ቀናት ዋሻ ውስጥ መውጫ አጥተው የነበሩ ሁለት ሰዎች በሕይወት ተገኙ

    ከዘጠኝ ቀናት በኋላ በሕይወት ከተገኙት ሁለት ሰዎች አንዱ ከነፍስ አድን ሠራተኞች ጋር

    የፎቶው ባለመብት, NEA

    የምስሉ መግለጫ, ከዘጠኝ ቀናት በኋላ በሕይወት ከተገኙት ሁለት ሰዎች አንዱ ከነፍስ አድን ሠራተኞች ጋር

    በኔፓል እና ቲቤት ድንበር አካባቢ ድንገተኛ ጎርፍ ከተከሰተ ከአንድ ሳምንት በላይ በኋላ በዋሻ ውስጥ መውጫ አጥተው የነበሩ ሁለት ሰዎች በሕይወት ተገኙ።

    ሁለቱ ሰዎች በአደገኛው ጎርፍ እና በመሬት መንሸራተት ምክንያት በትሪሹሊ ሸለቆ ውስጥ በሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ዋሻ ውስጥ በግንባታ ላይ ሳሉ መውጫ አጥተው ከቆዩ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ነው በሕይወት የተገኙት።

    በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአደጋው በኋላ የደረሱበት ሳይታወቅ ለማግኘት ፍልጋ እየተካሄደ ሲሆን የሁለቱ ሰዎች መገኝት ለነፍስ አድርን ሠራተኞች ተስፋን ሰጥቷል።

    ከሳምንት በላይ በዋሻ ውስጥ መውጫ አጥተው በሕይወት ከተገኙት ሰዎች በተጨማሪ የሦስተኛ ሰው አስክሬን ተገኝቷል፤ የጠፉ ሰዎችን ፈልጎ ነፍስ የማዳን ሥራው አሁንም እንደቀጠለ ነው።

    አንድ ባለሙያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የትሪሹሊ 3ኤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሚገኝበት ይህ ዋሻ ለሰዎቹ በሕይወት ለመቆየት አመቺ ሁኔታዎች ያሉበት ቦታ ሊሆን ይችላል።

    የነፍስ አድን ሠራተኞች በውስጥ ያሉ ሰዎች በአየር እጥረት ታፍነው እንዳይሞቱ ለማገዝ ወደ ዋሻው ኦክሲጅን ሲረጩ ቆይተዋል፤ እንዲሁም መውጫ ላጡት ሰዎች እነሱን ለማዳን እየጣሩ መሆናቸውን ማሳወቅ ችለዋል።

    ዛሬ ጠዋት በሕይወት ከተገኙት ሰዎች አንዱ ካቢር ማሃርጃን በአስከፊ የጤና ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሆስፒታል ተኝቷል። ሁለተኛው ግለሰብ ሳንጃያ ሻህ በሄሊኮፕተር ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ቢሆንም፣ በቦታው ላይ የሕክምና እርዳታ ሲደረግለት እየተናገረ እንደነበር ታይቷል።

    የኔፓል የአደጋ መከላከል አስተዳደር ተቋም ዓርብ ዕለት እንዳስታወቀው፣ ከአደጋው ጋር በተያያዘ በመላዋ አገሪቱ እስካሁን የ1,287 ሰዎች አስከሬኖች ተገኝተዋል፤ ነገር ግን 5,083 የሚጠጉ ሰዎች የደረሱበት ሳይታወቅ አሁንም እንደጠፉ ነው።

    ከዘጠኝ ቀናት በኋላ በሕይወት ከተገኙት ሁለት ሰዎች አንዱ የነፍስ አድን ሠራተኞች በቃሬዜ ሲያጓጉዙት

    የፎቶው ባለመብት, NEA

    የምስሉ መግለጫ, ከዘጠኝ ቀናት በኋላ በሕይወት ከተገኙት ሁለት ሰዎች አንዱ የነፍስ አድን ሠራተኞች በቃሬዜ ሲያጓጉዙት
  12. ኢራን ለማንኛውም ዓይነት ፍልሚያ ዝግጁ መሆኗን አንድ ወታደራዊ ባለሥልጣን ተናገሩ

    ሚሳዔሎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ኢራን አሁን የገጠማትን እና ወደፊት ለሚከሰት የትኛውም ዓይነት ወታደራዊ ፍልሚያ ዝግጁ መሆኗን የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ማዘዣ ማዕከል ኻታም አል-አንቢያ አዛዥ አሊሬዛ ኤልሃሚ ተናገሩ።

    ከፍተኛው ወታደራዊ ባለሥልጣን “ዛሬም ሆነ ወደፊት ለሚያጋጥም ማንኛውም ዓይነት ፍጥጫ ራሳችንን አዘጋጅተናል፤ ይህንም ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ሲሉ የአገራቸውን አቋም አስታውቀዋል።

    አሊሬዛ ኤልሃሚ እንዳሉት፣ ከኢራን ዕይታ አንጻር የገጠማት አደጋ "ገና አልተወገደም” በማለት ሠራዊታቸው በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

    ከአሜሪካ ጋር እየተካሄደ ባለው ጦርነት የኢራን ጦር ሠራዊት የተለያዩ የጥቃት እና የመከላከያ ጦር መሻሪያዎችን የበለጠ እየተጠቀመ መሆኑንም አመለክተዋል።

    “በቅርቡ በነበረው ጦርነት የሠራዊቱ እና የእስላማዊው አብዮታዊ ዘብ የአየር መከላከያ ኃይሎች የአየር መከላከያ ሥርዓት አዘጋጅተው፣ አሻሽለው፣ በማሰማራት በተግባር ላይ አውለዋል።”

    በተጨማሪም “የአገሪቱ የአየር መከላከያ ሥርዓት በአገር ውስጥ ባሉ አቅሞች፣ በወጣት ሳይንቲስቶች፣ በዕውቀት ላይ በተመሠረቱ ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና በታጠቁ ኃይሎች ከተገኘ የተግባር ልምድ ላይ በመመሥረት በሚያስፈልጉ ሙሉ በሙሉ ራስን መቻል ተችሏል” ሲሉ ተናግረዋል።

  13. በየመን ቀይ ባሕር አካባቢዎች በተካሄዱ ውጊያዎች ከ80 በላይ ተዋጊዎች ተገደሉ

    የሁቲ ታጣቂዎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በየመን ሁቲ አማጺያን እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና በተሰጠው የአገሪቱ መንግሥት ኃይሎች መካከል ከሐሙስ ጀምሮ በቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች እና በታይዝ አውራጃ በተካሄዱ ውጊያዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ።

    የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ሁለት የጦር ኃላፊዎችን እና የሕክምና ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተካሄደው ውጊያ 41 የሁቲ ታጣቂዎችን ጨምሮ ቢያንስ 81 ተዋጊዎች ተገድለዋል።

    በቀይ ባሕር ዳርቻ ያለ አንድ ወታደራዊ ባለሥልጣን 24 ወታደሮቹ መሞታቸውን ሲገልጽ፣ ታይዝ በሚባለው አካባቢ በሚገኝ ስፍራ የሚገኝ ባለሥልጣን ደግሞ 15 ሰዎች መገደላቸውን ተናግሯል።

    በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የሕክምና ምንጮች እንዳሉት፣ ቢያንስ 42 የሁቲ ተዋጊዎች በውጊያው ተገድለዋል።

    ውጊያው የተቀሰቀሰው ሐሙስ ዕለት የሁቲ ኃይሎች በቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች እና በታይዝ ዙሪያ በሮኬቶች እና በድሮኖች የታገዘ የእግረኛ ተዋጊዎች ጥቃት ከከፈቱ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።

  14. አሜሪካ ስለ የኢራን የሳይበር ዘመቻዎች ከፍተኛ አዛዥ መረጃ ለሚሰጥ 10 ሚሊዮን ዶላር ልትከፍል ነው

    አሚር ያሪያብ
    የምስሉ መግለጫ, አሚር ያሪያብ

    አሜሪካ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሳይበር እና ኤሌክትሮኒክስ ዘመቻዎች ዕዝ ውስጥ ከፍተኛ አዛዥ የሆነው አሚር ያሪያብን ማንነት ወይም አድራሻውን የሚጠቁም መረጃ ለሚሰጥ ሰው እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት እንደምትሰጥ አስታወቀች።

    የአብዮታዊ ዘቡ ዕዝ ከፍተኛ አዛዥ ላይ የመረጃ ጥያቄ የቀረበው፣ “ሽልማት ለፍትህ” በሚባለው እና የአሜሪካ መንግሥት በወንጀል ስለሚፈልጋቸው ሰዎች ጥቆማ ለሚሰጡ የገንዘብ ሽልማት የሚያቀርብበት መርሃ ግብር አካኝነት ነው።

    በዚህም “በውጭ መንግሥታት ቁጥጥር ወይም መመሪያ ሥር ሆነው በአሜሪካ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ ጎጂ የሳይበር ጥቃቶችን የፈጸሙ ግለሰቦችን ለመለየት ወይም ለማግኘት የሚያስችል መረጃ ለሚያቀርብ ሰው እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ሽልማት ይሰጣል” ብሏል።

    የአሜሪካ መንግሥት አሁን ዝርዝር መረጃውን ለማግኘት ጥሪ ያቀረበበት አሚር ያሪያብ፣ በኢራን አብዮታዊ ዘብ ሥር የበይነ መረብ እና ኤሌክትሮኒክስ ወታደራዊ ጉዳዮችን በሚከታተለው ዕዝ ውስጥ "የበይነ መረብ ዘመቻዎች" ምክትል አዛዥ እንደሆነ ተገልጿል።

    ዋሽንግተን እንደምትለው ያሪያብ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ በመከላከያ፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በባሕር ትራንስፖርት፣ በጉዞ እና ቱሪዝም (ሆቴሎችና አየር መንገዶች)፣ በኃይል፣ በፋይናንስ እና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች ላይ የተፈጸሙ አደገኛ የበይነ መረብ ጥቃቶችን ይመራ እንደነበር አሳውቃለች።

    ከሁለት ዓመታት በፊትም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተፈላጊዎችን የሚመለከት መረጃ ለማግኘት የኢራን አብዮታዊ ዘብ የበይነ መረብ ጥቃት የዕዝ ማዕከል ስድስት ከፍተኛ ኃላፊዎችን በሚመለከት ጥቆማ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

    በዚህም የስድስቱን አዛዦች ፎቶግራፎች በማውጣት እነዚህ ግለሰቦች የት እንደሚገኙ ወይም ማንነታቸውን ለማጋለጥ የሚያስችል ዝርዝር መረጃ ለሚሰጥ ሰው 10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለማቅረብ ቃል ገብቶ ነበር።

  15. ብሪታኒያ ገንዘብ መቆጠብ እንዲቻል ወሳኝ ያልሆኑ ወታደራዊ ልምምዶች እንዲቆሙ አዘዘች

    ሥልጠና ላይ ያሉ ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የብሪታኒያ ሠራዊት ወጪን ለመቀነስ ሲባል “ወሳኝ ያልሆኑ” ወታደራዊ ልምምዶች እንዲቆሙ ትዕዛዝ መተላለፉን የመከላከያ ምንጮች ገለጹ።

    ነገር ግን እንደ ኢስቶኒያ፣ ፎክላንድ ወይም ቆጵሮስ ባሉ ግዛቶች ለመሰማራት የሚዘጋጁ ወይም ለተሰማሩ ወታደሮች የሚሰጠው ሥልጠና እንደሚቀጥል ተገልጿል።

    ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ የሚገኙ እና ለአንዳች ተልዕኮ ዝግጀት የማያደርጉ የጦር ክፍሎች ግን በፋይናንስ ጫና ምክንያት የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን እንዲቀንሱ ተነግሯቸዋል።

    ይህ ትዕዛዝ የተላለፈው አዲሱ ዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ለመከላከያ የሚያዘውን በጀት እንዲያሳድጉ ግፊት እየተደረገባቸው ባለበት ወቅት ነው።

    የአገሪቱ መንግሥት እስከ በሚቀጥለው ዓመት ለመከላከያ ወጪ የሚመደበው በጀት ከአገራዊ ጠቅላላ ገቢ ውስጥ 2.5 በመቶ ድርሻ እንዲይዝ የማድረግ ዕቅድ አለው። ነገር ግን ይህንን በጀት እስከ 2030 ድረስ 3 በመቶ የማድረስ ግብ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ የሚደረገው ጫና ጨምሯል።

    የአሁኑ ውሳኔ “ቢደረጉ ጥሩ የሆኑትን” እንደ ትላልቅ የቀጥታ ተኩስ ልምምዶች እንዲሁም በዊልትሻየር እና ዌልስ በሚገኙ የሥልጠና ስፍራዎች እንደሚደረጉ የማጥቃት ዝግጅቶችን የመሳሰሉ ሥልጠናዎች እንዲታጠፉ እንደሚያደርግ አንድ የመከላከያ ምንጭ ተናግረዋል።

    ሊካሄዱ ታቅደው የነበሩ ልምምዶች አሁን እንደተቋረጡ ቢቢሲ ተገንዝቧል። ከተሰረዙት ዕቅዶች መካከል የሮያል ታንከኛ ክፍለ ጦር በዌልስ የሚያካሂደው የቀጥታ ተኩስ ልምምድ እንዲሁም ታንኮችን እና አፓቺ ሄሊኮፕተሮችን ያካተተ ሌላ ልምምድ ይገኙበታል።

    እንድ ምንጭ እንደሚናገሩት፣ ይህ ውሳኔ ሠራዊቱ የሚፈልገው ዓይነት አይደለም። ልምምዶች ላይ የተጣለው ገደብ የተያዘው አውሮፓውያን ዓመት እስከሚጠናቀቅ እንደሚቆይ ይጠበቃል።

    ጦሩን የማዘመን ግብ ያላቸው እና የድሮን እና የፀረ ድሮን ውጊያ ልምምዶችን የመሳሰሉ ልዩ ሥልጠናዎች ግን እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።

  16. አሜሪካ በኢራን ሰርግ ላይ ተፈጽሟል የተባለውን የሚሳዔል ጥቃት እየመረመረች መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ተናገሩ

    በጥቃት የተጎዳው ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Iranian Red Crescent Society

    በደቡባዊ ኢራን እየተካሄደ በነበረ ሰርግ ላይ በተፈጸመ የአሜሪካ የሚሳዔል ጥቃት ሁለት ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ አራት ሰዎች ተገድለዋል ስለመባሉ የአሜሪካ ጦር ምርመራ እያደረገ መሆኑን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ አስታወቁ።

    ማክሰኞ ዕለት ሰርግ እየተደረገበት በነበረ በሲሪክ ከተማ የሚገኝ መኖሪያ ቤት በሚሳዔል ስብርባሪዎች መመታቱን የሰብአዊ ድርጅት የሆነው የኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር ገልጿል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋኢ ድርጊቱን “የጦር ወንጀል” ሲሉ ጠርተውታል።

    በዕለቱ ኢራን የአሜሪካ ኃይሎች ላይ “የጥቃት ሙከራ” በማድረጓ፤ ዋሽንግተን ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን አስታውቃ ነበር። ይሁን እንጂ የአሜሪካ ጦር ዕዝ ቃል አቀባይ ሠራዊታቸው “መቼም ሲቪሎችን ዒላማ እንደማያደርግ” ተናግረዋል።

    ትናንት ሐሙስ መግለጫ የሰጡት ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ስለጥቃቱ በሚወጡ ዘገባዎች ላይ “እጅግ ከፍተኛ ጥርጣሬ” እንዳላቸው ገልጸዋል። ነገር ግን አሜሪካ ስለ ጉዳዩ ምርመራ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

    ቫንስ “እስካሁን በግጭቱ የተፈጠሩ ክስተቶችን በትክክል መከተብ ላይ የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጥሩ አልነበሩም። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ” ሲሉ በዋይት ሀውስ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

    ክስተቱን “እየመረመርነው እንደሆነ አውቃለሁ” ሲሉም አክለዋል።

    ኢራን ተፈጽሟል ለተባለው ለዚህ ጥቃት በሰጠችው ምላሽ፣ በኩዌት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ አዲስ ጥቃት ከፍታለች።

    የኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር እንደገለጸው በቤተሰብ የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ ባረፈው የሚሳዔል ስብርባሪ ምክንያት አራት ሰዎች ሲገደሉ 67 ሰዎች ቆስለዋል። አንዲት የ22 ዓመት ወጣት ሆስፒታል ውስጥ መሞቷት የገለጹት የኢራን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር ወደ አምስት ከፍ አድርገውታል።

    በጥቃቱ የተገደሉት አራቱ ሰዎች የአራት ዓመቱ አሚራሊ ካሪሚ፣ የ16 ዓመቱ መሐመድ ማላሂ፣ የ46 ዓመቷ ኮልሱም ማላሂ ናዝድኒያ፣ እና የ50 ዓመቱ ዛርካቱን ታሄሪ እንደሆኑ ተገልጿል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ ማክሰኞ ዕለት በኩሄስታክ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ የተቀረጸ ቪዲዮ እና ሁለት ፎቶዎች ያደረገው ምርመራ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ማማ ሲወድም አሳይቷል። ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት የተቀረጹ ሌሎች ቪዲዮዎች ደግሞ ከማማው በስተሰሜን 130 ሜትር ርቀት ላይ እጅጉን የተጎዱ ቤቶችን ያሳያሉ።

    በተጨማሪም ቢቢሲ ፐርሺያን ፎረንሲክስ ባደረገው ምርመራ ሰርጉ ሲካሄድበት ከነበረው ቤት 112 ሜትር ርቀት የቴሌኮሙኒኬሽን ማማ መኖሩን ደርሶበታል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት መጨረሻ ኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃት የተጀመረው ይህ ጦርነት ከስድስት ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ እየተካሄደ ነው።

  17. የኬንያው ፕሬዝዳንት በአነስተኛ ንግድ ላይ በተሰማሩ የውጭ ዜጎች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ አዘዙ

    ፕሬዝዳንት ዊሊያን ሩቶ

    የፎቶው ባለመብት, State House Kenya

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዊሊያን ሩቶ

    የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ አገራቸው ውስጥ በአነስተኛ ንግዶች ላይ የተሰማሩ የውጭ አገራት ዜጎችን ለመቆጣጠር እርምጃ እንዲወሰድ አዘዙ።

    ፕሬዝዳንቱ “ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በእነዚህ አነስተኛ ንግዶች ላይ የተሰማሩ ሁሉም የውጭ አገራት ዜጎች ሥራቸውን ማቆም አለባቸው” ብለዋል።

    በተጨማሪም የውጭ ዜጎች በተወሰኑ የንግድ ዘርፎች ላይ እንዳይሰማሩ የሚያግድ ረቂቅ ሕግ እንዲፀድቅ ትኩረት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ኬንያ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መሆኗን አረጋግጠው፣ ነገር ግን ቻይናውያን ነጋዴዎችን ጨምሮ ባለሀብቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እና ምርት ማሳደግ እንጂ በአነስተኛ ንግድ ላይ ከኬንያውያን ጋር መወዳደር አይገባቸውም ብለዋል።

    በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ የውጭ ዜጎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ወይም በዚህ እርምጃ ምን ያህሉ ተጎጂ እንደሚሆኑ ግን ግልጽ አይደለም።

    ኬንያ በርካታ ስደተኞችን የምታስተናግድ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ከስደተኞች ማቆያ ካምፖች ውጪ በመኖር እና በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

    የመንግሥት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ በኬንያ 857 ሺህ የሚጠጉ የተመዘገቡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 14 በመቶ የሚሆኑት በከተሞች አካባቢ ይኖራሉ።

    የኬንያ ሕግ ለስደተኞች የመሥራ እና የመነገድ መብት ይሰጣል፤ ሆኖም አስፈላጊውን ምዝገባ እና ሰነድ ማግኘት እንዲሁም ልዩ ፈቃድ ሊጠይቁ ይችላሉ።

    በናይሮቢ እና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች፣ ከአካባቢው አገራት የመጡ ስደተኞች በፀጉር ቤቶች እና በውበት ሳሎኖች፣ በግንባታ፣ በሞተር ሳይክል ታክሲ አገልግሎት፣ በጎዳና ላይ ንግድ እንዲሁም ልብስ፣ ምግብ እና የቤት ቁሳቁሶች በመሸጥ ላይ ተሰማርተዋል።

  18. ኢራን ከዚህ በኋላ ለአሜሪካ ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ ከሚጠበቀው በላይ የከፋ ይሆናል አለች

    የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሬዛ አሬፍ

    የፎቶው ባለመብት, IRIBNEWS

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሬዛ አሬፍ

    አሜሪካ በዚህ ሳምንት በኢራን ዒላማዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት መልሳ መጀመሯን ተከትሎ ከዚህ በኋላ ኢራን ለሚፈጸምባት ጥቃት የምትመልሰው አጸፋ ከሚጠበቀው በላይ እንደሚሆን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ተናገሩ።

    የኢራን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሬዛ አሬፍ፣ አሜሪካ ባለፉት ቀናት በኢራን ላይ የፈጸመቻቸውን ጥቃቶች “ወንጀል” ሲሉ ገልጸው፣ “ከእንግዲህ በኋላ የእኛ ምላሽ ሚዛናዊ አይሆንም” ብለዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “አሜሪካ በኢራን ሕዝብ ላይ የፈጸመቻቸው አዳዲስ ወንጀሎች የእኛን የደኅንነት ስሌቶች እና የመከላከያ መርኅን ቀይረውታል” ሲሉ ጽፈዋል።

    ይህንንም ተከትሎ በአሜሪካ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች “ከዚህ በኋላ የምንሰጠው ምላሽ ሚዛናዊ ያልሆነ፣ በበርካታ ደረጃዎች የሚፈጸም እና የአጥቂውን ደኅንነት የሚያሳጣ ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።

    የኢራኑ የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት በመጨረሻም “አሜሪካውያን ቤንዚን እና ሌሎች ነዳጆችን ስለማከማቸት ማሰብ ይኖርባቸዋል” በማለትም አስጠንቅቀዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን ፓርላማ የብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊ ኢብራሂም አዚዚ፣ ኢራን እስካላፈቀደች ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ለመርከቦች እንቅስቃሴ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ተናገሩ።

    የአገሪቱ ምክር ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣኑ “የሆርሙዝ ወሽመጥ ያለ እስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን ፈቃድ አይከፈትም፤ ይህም በግልጽ የሚታይ ነው” በማለት በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ ጠቅሰዋል።

    አዚዚ እንዳሉት፣ አሜሪካ ባለፉት ስድስት ወራት ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ለማስከፈት ያደረገቸው ጥረት ስላልተሳከ በአሁኑ ጊዜ “ክፉ ድርጊቶችን እየፈጸመች ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

    አሜሪካ በወታደራዊ ጥቃት በኢራን ላይ ጫና ለማሳደር ከምደታርገው ዘመቻ በተጨማሪ ሌሎች ማዕቀቦች እና እገዳዎችን ተግባራዊ በማድረግ ኢራንን በምጣኔ ሀብት ለማዳከም አዲስ ዘመቻ ጀምራለች።

    እንዲሁም ባለፉት ቀናት አሜሪካ፣ በተለያዩ የኢራን ግዛቶች ውስጥ ጥቃቶችን ስትፈጽም ኢራንም በአጸፋው በዮርዳኖስ፣ በኩዌት እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ዒላማ በማድረግ ጥቃት አድርሳለች።

  19. አገራት ከኢራን እንዲርቁ አሜሪካ ያወጣችውን ማስጠንቀቂያ ሩሲያ ውድቅ አደረገች

    ዲሚትሪ ፔስኮቭ

    የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ

    አገራት ለኢራን የሚሰጡትን ድጋፍ እና የንግድ ግንኙነታቸውን በማቆም እራሳቸውን ከቴህራን እንዲያርቁ አሜሪካ የሰጠችውን ማስጠንቀቂያ ሩሲያ ውድቅ አደረገች።

    የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት በቅርቡ፣ “በኢራን ላይ ከዚህ በፊት ያልታዩ ቅጣቶችን እየጣልን ነው። ግጭቱን በፍጥነት ለማቆም የሚረዳውን መንገድ በሚያደናቅፍ ሁኔታ ማንም ለኢራን አገዛዝ እንዳያደርግ” ሲሉ አሳስበው ነበር።

    ስድስት ወራት በሞላው ጦርነት አሜሪካ በኢራን ላይ ከምትወስደው ወታደራዊ እርምጃ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማሳደር ያላትን ዕቅድ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጋለች።

    በዚህም በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እና ዕገዳዎችን መጣል እንዲሁም ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸው አገራት እና ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰድን ዓላማ አድርጋለች።

    አገራትም ከኢራን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ አሜሪካ በይፋ ጥሪ ብታቀርብም ኃያላኑን ቻይናን እና ሩሲያን ጨምሮ ከአንዳንድ አገራት ጠንካራ የተቃውሞ ምላሽ ገጥሟታል።

    አሁን ሩሲያ በይፋ እንዳስታወቀችው በአሜሪካ ጫና ከኢራን ጋር የሚኖራት ግንኙነት ላይ ለውጥ እንደማይኖር ገልጻለች።

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ እንደሉት “አጋሮች እና ወዳጆች አሉን፤ እነዚህን የወዳጅነት እና የሽርክና ግንኙነቶች ጠብቀን እናስቀጥላለን፣ ከዚያም በላይ እናጠናክራቸዋለን” ሲሉ ኢንተርፋክስ ለተባለው የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ፔስኮቭ አክለውም፣ አሜሪካ “ከሌላ አገር ጋር ያሉ ግንኙነቶችን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ወይም ለመጠቅለል የምትችል አይደለችም” ሲሉ የአሜሪካንን ማስጠንቀቂያ አጣጥለውታል።

  20. የኢራን ጦር በኩዌት በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ

    የኢራን ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

    የኢራን ጦር ሠራዊት በኩዌት የሚገኙ የሳተላይት መገናኛ ሥርዓቶችን፣ የመሳሪያ ማከማቻ ቦታዎችን እና የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች ማቆሚያ መጠለያዎችን ዒላማ አድርጎ መምታቱን አስታወቀ።

    የኢራን ጦር ሐሙስ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ፣ በኩዌት በሚገኘው አህመድ አል ጃበር የጦር ሰፈር ውስጥ ያሉ ቁልፍ ወታደራዊ ዒላማዎችን በሚሳኤሎች እና ከፍተኛ የፍንዳታ አቅም ባላቸው ድሮኖች መምታቱን ገልጿል።

    የኢራን ጦር በፈጸመው ጥቃት በጦር ሰፈሩ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት “በመገናኛ ሥርዓቶች እና በተዋጊ አውሮፕላኖች መጠለያ ላይ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።

    በተመሳሳይ መግለጫው የኢራን ጦር፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሚገኘው አል ሚንሃድ የጦር ሰፈር ውስጥ ያሉ “የአሜሪካ ጦር ኃይሎች መገኛ እና የራዳር ሥርዓቶችም” መምታቱን አስታውቋል።

    የኢራን ሠራዊት መግለጫውን ከማውጣቱ ከአንድ ሰዓት ቀደም ብሎ የኩዌት ጦር ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ ከኢራን የተነሱ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን ለመከላከል የአየር መከላከያ ሥርዓቶቿን በተጠንቀቅ ማቆሙን አሳውቆ ነበር።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ በኢራን ላይ መፈጸም የጀመረችውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በአጸፋው በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት እየፈጸመች መሆኗን አስታውቃለች።