ናይጄሪያዊቷ ደራሲ ቺማማንዳ በልጇ ሞት ላይ የሚደረገውን ምርመራ በማደናቀፍ ሌጎስ የሚገኝ ሆስፒታልን ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂዋ ናይጄሪያዊት ደራሲ ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቼ በሕንፃን ልጇ አሟሟት ላይ የሚደረገውን ምርመራ በማደናቀፍ በሌጎስ የሚገኝ ሆስፒታልን ከሰሰች።
ቺማማንዳ እንዳለችው ጥር ወር ላይ በኤውራኬር ሆስፒታል ውስጥ በድንገት ሕይወቱ ያለፈው የ21 ወር ልጇ አሟሟት ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ ሚያዚያ ወር ላይ መጀመር ነበረበት።
ነገር ግን ሆስፒታሉ ምርመራውን በማደናቀፉ በጊዜው እንዳልተጀመረ ገልጻለች።
"ምርመራውን በማዘግየት፣ በመሸፋፈን እና በማደናቀፍ" እንዲሁም የናይጄሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርመራውን እንዲያግድ በመጠየቅም ሆስፒታሉን ወንጅላለች።
ቢቢሲ ኤውራኬር ሆስፒታል በቀረበበት ክስ ላይ አስተያየቱን ጠይቋል።
ቀደም ብሎ በናይጄሪያ ሜዲካል እና በጥርስ ሕክምና ምክር ቤት የተቋቋመው የምርመራ ኮሚቴ በሆስፒታሉ የሕክምና አሰጣጥ ላይ "ግድየለሽነትን" ሊያሳይ የሚችል ኬዝ ማግኘቱን ገልጿል።
ቺማማንዳ ሚያዚያ ወር ላይ ለሆስፒታሉ የላከችውን ደብዳቤ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያዋ ላይ አጋርታለች።
ይህም በ2024 በማሕፀን ኪራይ ከተወለዱት መንትያ ልጆቿ አንዱን ካጣች በኋላ በይፋ ለሕዝብ የሰጠችው አስተያየት ነው።
"ኤውራኬር ስለ እውነት የሚጨነቅ ከሆነ ምርመራው ለምን እንዲዘገይ እና እንዲደናቀፍ ያደርጋል? እንዲቆምስ ለምን ይጠይቃል? ብላለች ባጋራችው ልጥፍ።
"ሃዘንን እና የተስፋ መቁረጥን ጥልቅ ስሜት ማወቅ የሚችለው የደረሰበት ብቻ ነው" ስትልም እያለፈችበት ያለውን ጥልቅ ሃዘን ገልጻለች።
"ቢያንስ በሰላም ሃዘኔን መወጣት ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን ኤውራኬር ሆስፒታል ይህንን እንኳን ነጥቆኛል።"
በደብዳቤዋ ላይ እንደገለፀችው ሆስፒታሉ ልጇ የሞተው በባክቴሪያ በሚመጣ ማጅራት ገትር እንደሆነ ገልጾላታል። ሆኖም ይህንን የሚያስረዳ ምንም ዓይነት የሕክምና ማስረጃ እንደሌለ ገልጻለች።
ቺማማንዳ እና ቤተሰቦቿ የሕክምና ባለሙያዎች ኦክስጅን ስለከለከሉት እና የልብ ችግር ያስከተለበትን ከልክ ያለፈ የሚያረጋጋ መድሃኒት በመስጠት ሆስፒታሉን በግድየለሽነት ከስሰዋል።
ሆስፒታሉ በሕጻኑ ሞት የተሰማውን ሃዘን የገለጸ ቢሆንም "ምንም ዓይነት ስህተት አልፈፀምኩም" ብሏል።
የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎትም ዓለም አቀፍ የሕክምና ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ እንደሆነ አክሏል።
ሆኖም ቺማማንዳ ሆስፒታሉ ያልተሟላ የሕክምና ማስረጃዎች በመስጠት የከሰሰች ሲሆን " ከሙያ ያፈነገጠ እና አንደኛው ጭራሽ ትክክል ያልነበረ ነው" ብላለች ።
በቺማማንዳ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ለፍርድ ቤት የቀረበው ሰነድ እንደሚያስረዳው ከሆነ ንካኑ ቀላል ሕመም አጋጥሞት መጀመሪያ ላይ በሌጎሰ በሚገኘው አትላንቲስ ሆስፒታል ገብቶ ነበር።
ከዚያም ለተሻለ ሕክምና በአሜሪካ ባልቲሞር ወደሚገኘው ጆንስ ሆፕኪንስ ሆስፒታል ለማዛወር ታቅዶ ነበር።
ሆኖም ለቅድመ በረራ ምርመራ ወደ ኤውራኬር ሆስፒታል ተወስዷል።
ንካኑ በሆስፒታሉ የተለያየ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ በአውሮፓውያኑ ጥር 7 ሕይወቱ አልፏል።
ቺማማንዳ 'ሃፍ ኦፍ ኤ የሎው ሰን' እና 'አሜሪካናህ' የተሰኙ መጽሐፍትን ጨምሮ በርካታ ሽልማት ያገኘችባቸውን ልብ ወለድ መጽሐፍት ለንባብ አብቅታለች።
በቅርቡም ግለ ታሪክ መጽሐፋቸውን ሲያስተዋውቁ የነበሩት የቀድሞ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሃሪስ እና የጀርመን የቀድሞ መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርክል የተገኙበት ውይይቶችን አዘጋጅታለች።
ቺማማንዳ ነዋሪነቷ በአሜሪካ ሲሆን ለገና በዓል ናይጄሪያ ነበረች።














